ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው አስታውቀዋል።

አቶ ደመቀ ይህን ያሉት በቅርቡ አዲስ ከተሾሙት የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተጠሪ ዳይሬክተር ክላዉድ ጂቢዳር ጋር በተወያዩበት ወቅት ነው።

አቶ ደመቀ የዓለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የተሻሉ ሥራዎችን ማከናወኑን ለዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ያሉት አቶ ደመቀ፤ እንደ ዓለም ምግብ ፕሮግራም ያሉ ድርጅቶች ደግሞ ሁሉን አቀፍ ተደራሽ የኾነ ሰብአዊ እርዳታ በማድረግ የተጠናከረ ድጋፍ እንዲያደርጉ እንፈልጋለን ነው ያሉት።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በአማራ እና በአፋር ክልልሎች እንዲሁም ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሰብአዊ ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

አቶ ደመቀ መንግሥት ያልተገደብ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደረግ ያሳለፈውን ውሳኔ በማክበር የተሻለ ድጋፍ እንዲደረግ እየሰራ መሆኑን አንስተው፣ የህወሓት ቡድን ግን አሁንም ሰብዓዊ እርዳታውን ለማስተጓጎል እየሞከረ ነው ብለዋል። ዓለም አቀፍ ለጋሽ አካላትም የቡድኑን አካሄድ ማውገዝ አለባቸው ነው ያሉት።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተጠሪ ዳይሬክተር ክላዉድ ጂቢዳር በበኩላቸው የመንግሥትን ቁርጠኝነት በማድነቅ በቀጣይም አብሮ ለመሥራት በሙሉ ቁርጠኝነት እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ከችግር ውስጥ ወጥቶ ወደ ተሻለ መንገድ እና እድገት መስመር መግባት ከራሷም በላይ ለሌሎች ሀገራትም ትልቅ ሚና ስላለው ከመንግሥት ጎን ኾነን ችግሩን ለማለፍ እንሰራለን ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች የውስጥ መፈናቀል ካጋጠማቸው ዜጎቿ በተጨማሪ ከ9መቶ ሺህ በላይ ስደተኞችን እያስተናገደች መሆኗን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል።

የምግብ አቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍ ኢትዮጵያ ስንዴን በከፍተኛ መጠን የማምረት አቅም ያላት ሀገር በመሆኗ ለዚህ ተግባር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም የሚያደርገውን የሰብአዊ ድጋፍ በድርቅ ወደ ተጎዱ አካባቢዎችም እንደሚያስፋፋ ተናግረዋል።

መረጃው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው።

Leave a Reply