በምዕራብ ጎጃም ዞን በሕዝብ ስም የቀረበን 13 ሺህ 140 ሊትር የምግብ ዘይት ለግል ጥቅማቸው በማዋል የተጠረጠሩት የሰሜን ሜጫ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የመራዊ ከተማ ፖሊስ አስታወቀ።

የከተማው ፖሊስ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ይንገስ ጌትነት ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቡ የተያዙት ስልጣንን ተገን በማድረግ ከግብረ አበራቸው ጋር በመሆን የምግብ ዘይቱን ለግል ጥቅማቸው ለማዋል ሲሞክሩ ተደርሶባቸው ነው።

ተጠርጣሪው የንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤትን ጨምሮ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት እውቅና ውጭ በሆነ መንገድ አነስተኛ ገቢ ላላቸውና ለነዋሪዎች በሚል በፃፉት ደብዳቤ የምግብ ዘይቱን ”ሪች ላንድ” ከተባለ ፋብሪካ እንዲቀርብ ማድረጋቸው በማስረጃ መረጋገጡን ገልጸዋል።

የምግብ ዘይቱ ለዚሁ ተግባር ሲባል በተጭበረበረ መንገድ የንግድ ፈቃድ ባወጣ የንግድ ባለሙያ ስምና የገንዘቡ ምንጭ ከየት እንደሆነ ለጊዜው ባልታወቀ ሁኔታ ተገዝቶ የቀረበ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዋና ኢንስፔክተር ይንገስ እንዳሉት ከ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመተው የምግብ ዘይት የተያዘው ተጠርጣሪዎቹ ሁለት ኮንቴነር ተከራይተው ደብቀው ካስቀመጡበት ነው።

ከኅብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት ፖሊስ ባደረገው ክትትልና ማጣራትም ተጠርጣሪዎቹ የሰሜን ሜጫ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪና በተጭበረበረ መንገድ የንግድ ፈቃድ ያወጣው የንግድ ባለሙያ በህግ ቁጥጥር ስር ውለዋል።

ተጠርጣሪዎቹ በጊዜ ቀጠሮ ወደ ማረሚያ ቤት ተልከው አግባብ ካላቸው አካላት ጋር በመሆን ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ዋና ኢንስፔክተር ይንገስ ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡ በወንጀል የተሰማሩ ግለሰቦችን በማጋለጥ የጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንዲቀጥል ዋና ኢንስፔክተር ይንገስ ጠይቀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply