ጫማ በመጥረግ የሚተዳደረው ወጣት 975 መጻህፍትን አበረከተ

በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆነውና ጫማ በመጥረግ የሚተዳደረው ወጣት 975 መጻሕፍት ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት እንዲደርስለት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አበርክቷል፡፡

ወጣት ታሪኩ ወዬሳ ይባላል ተወልዶ ያደገው ወሊሶ ዲላለ የምትባል አካባቢ ሲሆን የአንዲት ሴት ልጅ አባትም ነው።

ታሪኩ እስከ አስርኛ ክፍል የጉልበት ስራ እየሰራ የተማረ ሲሆን ከልጅነቱ ጀምሮ ከፍተኛ የማንበብ ፍላጎት ስለነበረው ሲኖረው እየገዛ ሳይኖረው ደግሞ ተከራይቶ ያነባል።

በአሁኑ ወቅት ታሪኩ ካዛንቺስ መለስ ፋውንዴሽን አካባቢ በቋሚነት ጫማ በመጥረግና (በሊስትሮ) የተለያዩ የጉልበት ስራዎችንም በመስራት በመተዳደር ላይ ይገኛል። በዛሬው እለትም ላለፉት ስድስት አመታት እየገዛ ሲያነባቸው የነበሩ 975 በላይ መጻህፍትን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አበርክቷል።

“መጻህፍቱ አሁን ትክክለኛ ቦታቸውን አግኝተዋል” የሚለው ታሪኩ “ከእኔ ጋር በማስቀመጫ እጥረት ምክንያት ከፍተኛ ችግር ገጥሞኝ ነበር። ከየትኛውም የቤት እቃዎቼ በላይ ለመጻህፍቱ ቅድሚያ እሰጣለሁ” ይላል ወጣቱ።

“በአንድ ወቅት የማስቀምጥበት ቦታ አጥቼ እናቴ ጋር ቦሌ አራብሳ የጋራ መኖሪያ ቤት (ኮንዶሚኒየም) ወስጂያቸው ነበር። ነገር ግን ቤቱ ስቱዲዩ ስለነበርበና ለእናቴ ስለጠበባት እዛ ማቆየት ስላልቻልኩ ወደተከራየሁበት ቤት መለስኳቸው። አምና ደግሞ በቁጥር የማላስታውሳቸውን መጻህፍቶች ወንዝ ወስዶብኛል። አሁንም በሁለት ሺ ብር የተከራየሁት ቤት ያለበት ቦታ ለጎርፍ የተጋለጠ በመሆኑ የአምናው እንዳይደገም ትልቅ ስጋት አለኝ። በመሆኑም መጻሕፍቱ ለህዝብ ይሁኑልኝ ብዬ አስረክቤያለሁ” ብሏል ወጣት ታሪኩ ወዬሳ።

በራስወርቅ ሙሉጌታ – (ኢ.ፕ.ድ)

See also  በአንድ ዓመት 20 ድሮኖችን የሠራው ኢትዮጵያዊ

Leave a Reply