ጦርነትም ሰላምም በደጅ ናቸው! ሰላምለትግራይም ለሌሎችም እናቶች ሲባል!!

tigray mother

“ለሁሉም የሚበጀው ሰላም ነው። ሰላም ከጦርነት በላይ ዋጋ ያስከፍላል። ለሰላም ሲባል ማናቸውም መስዋዕትነት ቢከፈል መልካም ነው። ሰላም ብቻ ነው ያለው አማራጭ። የትግራይ እናቶችም ሆኑ ሌሎች እኩል ሰላም ይሻሉ። የአንድ እናት ሃዘን የሌሎች እናቶችም ሃዘን ነውና” ደጀኔ ዋርዳ

የኤርትራ ሰራዊት ላይ ከትህነግ በኩል በራማና በባድመ አቅጣጫ ተኩስ መከፈቱ የተሰማው ከቀናት በፊት ነው። ምን እንደነካው በግልጽ መረጃ ያተሰጠበት ቢቢሲ ” የትግራይ እናቶች እየታሰሩ ነው” ከሚለው ዜናው በማስከተል “ሚስጥረኞች ነገሩኝ” ሲል በማህበራዊ ሚዲያ የተበተነውን ዜና እውነት ስለመሆኑ ጽፏል። የትህነግ ሃይል ማጥቃት ሞክሮ ማፈግፈጉን ተናግሯል።

ይህ ዜና ከመሰማቱ ቀደም ብሎ የጦር ሃይሎች ዋና አዝዥ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ፋቲካቸውን ለብሰው መታየትና ውሏቸውን ጦር ሜዳ ማድረግ አብዝተዋል። ኢሳያስም ከኢትዮጵያ ጋር የትፈጠረ ችግር እንደሌለ፣ ነገር ግን የፖሊስ ልዩነት መኖሩን ይፋ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ሰራዊት ከኤርትራ ሲወጣ እንደማያውቁ ቀድመው የተናገሩትና ውሳኔው ትክክል ነው በለው እንደማያስቡ ያስታወቁት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፣ አሁን ላይ ትህነግን አስመልክቶ ቁርጥ ያለ ነገር ባይናገሩም ” ትህነግ ኤርትራን ለመውረር ዝግጅት ላይ መሆኑንን የደህንነት ክፍሉ ማስረጃ አግኝቷል” በሚል የኤርትራ ፕሬስ ጽፎ ነበር።

የሰላም ዜናና የድርድር መረጃዎች በሚሰሙበት ወቅት የትህነግ ወታደር ምላመላ ከፈቃደኛነት አልፎ በግድ መሆኑ፣ በጦርነት የሞት ልጅ አምጡ እስከማለት መድረሱ፣ ዶክተር ደብረጽዮን ከበባው ከላተነሳ ሌላ ማራጭ እንከተላለን ማለታቸው …. ሁሉም ተጋምደው ትህነግ በክረምት ጦርነት ሊከፍት እንደሚችል የሚሰነዘረውን መላ ምት ያጎላዋል የሚሉ አሉ።

“ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ሰፊ ሃይል ገንብታለች፣ ዘመናዊ መሳሪያና ቴክኖሎጂ ይዛለች እናም ትህነግ ደፍሮ ሊያጠቃ አይችልም” የሚሉ ቢኖሩም በመንግስት በኩል ግን ዝግጁነቱ በጣምራ ልምምድ ታግዞ እየተከናወነ መሆኑ በይፋ በምንግስት ሚዲያዎች እየተገለጸ ይገኛል።

“ሰራዊታችን እንደሀገር ሊቃጣብን የሚችልን ማንኛውም ትንኮሳና ጥቃት በብቃት መመከት በሚያስችል የዝግጁነት ደረጃ ላይ ይገኛል ሲሉ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ጀኔራል ጌታቸው እንዳረጋገጡት፣ በወልደያ በኩልም ያለው ሰራዊት አዛዥ ” ዝግጁ መሆናችንን ለኢትዮጵያ ህዝብ አርጋግጣለሁ” እንዳሉት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኢትዮጵያ መከላከያ አሁን ላይ ያለው አቋም ኦፕሬሽንን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ የሚችል መሆኑንን አደባባይ መናገራቸው እንዲሁ ለፉከራ እንዳልሆነ የሚናገሩ አሉ።

በትግራይ ህወሓት እናቶች ላይ እያደረገ ያለውን ፍጹም ብርሀነ ከትግራይ በዚህ መልኩ ገልጾታል። ጥሎብን ነው እንጂ የትግራይ እናት ትታሰር ነበር? ስለተንከባከበ ? ስለ ታገለ ? እናቶች ምንጣፍ ተሸክመው በታጣቂ ሲዋከቡ ብታዩ ምን ልትሉ ነበር? እኛ እሱን ነው ያየነው

“ትህነግ እንደ በፊቱ ባዶ ቤት ዝም ብሎ መውረር እንደማይችል፣ እንዲያውቅና እጁን እንዲሰበስብ ማስጠንቀቂያ ነው” የሚሉ ” ይህን ሰራዊት እጅህን ለትግራይ ሃይሎች ስጥና በሰላም ወደ ቤትህ ግባ” በሚል ዳግም አፍርሰውት ለልመና ሊዳርጉት ለሚመኙ ሃይሎች የሚፋጅ እንደሆነ ማስጠንቀቂያ እንደሆነም የሚገልጹ ጥቂት አይደሉም።

አሸባሪው የትህነግ ቡድን ከጀሌዎቹ ጋር በማበር የከፈተውን ሀገር የማፍረስ እቅድ መከላከያ ሰራዊታችን በውስብስብ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ማክሸፍ መቻሉን ያስታወሱት ጀኔራል ጌታቸው ጉዲና ከዘመቻ በኋላ የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም በመጠቀም ተቋሙ በሞራል፣ በሰውሃይል፣ በብቃትና በማቴሪያል የተሟላና ግዙፍ ኃይል እንዲሆን ማድረግ እንደተቻል አዛዡን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።

ሰራዊታችን እያንዳንዷን ሰዓት በስልጠና ላይ በማዋል መቺና ድልን በአስተማማኝ መልኩ ማምጣት በሚችል ቁመና ላይ እንዲደርስ ማድረግ መቻሉን የገለፁት ጄነራል መኮንኑ ሀገራችንን ለመድፈር በሚያስቡ አካላት ላይ መንግስት በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሰረት የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ አሳስበዋል።

ተቋሙ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰራዊት የመገንባት ሂደቱን ያሳካና ሀገራዊ ፍቅርና ስሜት ያለው ሰራዊት የገነባ በመሆኑ ለቀጣይ የግዳጅ አፈፃፀም ስኬታማነት ድርሻው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል ። በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ የሚነሳ እሳት እያንዳንዳችንን እንደሚያቃጥለን መረዳት ከሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን ጄነራል ጌታቸው ጉዲና ገልፀው የተለያዩ ምክንያቶችን መነሻ በማድረግ ለጁንታውና አጋሮቹ ድጋፍ በመስጠት ሀገራችን አደጋ ላይ እንድትወድቅ የሚሰሩ አካላት ቆም ብለው ማሰብ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

እንግዲህ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር እንኳን ማንሳቱ ባያስፈልግ ላለፉት ሁለት ወራት መከላከያ የተቀናጀ ልምምድና ዝግጅት ያደረገው ለምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ በስፋት እየተነሳ ባለበት በአሁን ወቅት ትህነግ ” ከናድ ቤት አንድ ልጅ” በሚል በግድ ልጆችን አምጡ ዘመቻው ተቃውሞ እየበረታበት ነው።

ባለፈው ውጊያ የትህነግ ወጣቶች ክንፍ 300 ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች የት እንደገቡ እንደማያውቅ ቢጠቅስም የደረሰው ሰብአዊ ቀውስ አቶ ጌታቸው ረዳ እንደሚሉት አይነት እንዳልሆነ በርካታ መረጃዎች እየወጡ ነው። ይህን ያህል ኪሳራ የተሸከሙ እናቶች ዛሬ ዳግም ሎቻቸውን ለጦርነት እንዲሰጡ መተየቃቸውን፣ “አዛዝኝ” ሲል ፍጹም ብርሃኔ ብቻ ሳይሆን ሌላው የክልሉ ተወላጅም ኮንኖ በማህበራዊ ገጹ እንዲህ ሲል አሰራጭቷል።

ፅሑፉ ልጃቸውን አምጡ ተብለው ስለታሰሩ አንድ አባት የሚያትት ነው።የሰውዬው ልጅ ግን የወያኔ ታጣቂ ሆኖ ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ሲዋጋ ሞቷል።ሰውየው አሁን ፈረስማይ ውስጥ ታስረዋል ።የወረዳዋ አስተዳዳሪ ነጋሲ ገረንችኤል ነው።ሰውዬው ልጃቸው ሲዋጋ መሞቱን ቢናገሩም አስተዳዳሪው ግን “ልጁን ደብቃችሁታል። እንኳንስ ሊሞት ጭራሽ አልታገለም” ብሎ እንዳሰራቸው ፀሐፊው አዝኖ ይገልፃል ።

በሌላ መልኩ በትዊተር አካውንቱ Dinlas የተባለ ሰው “የወያኔ ሰዎች በመቀሌ የሚገኙ መጋዘኖችን እየዞሩ ጣራዎቻቸው ላይ “UN” የሚል ቃል እየፃፉባቸው ነው” ብሏል። መረጃውን ያጋራው ይህ ሰው “በእነዚህ መጋዘኖች ውስጥ ተሽከርካሪዎችን እና የጦር መሳሪያዎችን እየደበቁባቸው እንደሆነ አውቃለሁ” ያለ ሲሆን በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎችም መጠነ ሰፊ የሆነ የቁፋሮ እየተካሄደ መሆኑንንም አምለክቷል።

የመረጃው ባለቤት ከላይ በጠቀሰው የቁፋሮ መረጃ ላይ የራሱን አስተያየት ሲያስቀምጥ ሁለት የቢሆን ግምቶቹን አስቀምጧል አንደኛው የተቀበረ መሳሪያ እያወጡ ሊሆን ይችላል።……ካልሆነ ደግሞ ፤ አዳዲስ ያስገቧቸውን መሳሪያዎች እየቀበሩም ሊሆን ይችላል ብሏል። አዳዲስ መሳሪያ ከየት? በ፣ማን በኩል? እንዴትና መቼ ወደ ትግራይ ገባ? የሚለውን ጉዳይ እጅግ መነጋገሪያ ያደረገው ይህ ሃሳብ በሌላ አባባል ይዳብራል።

“ከትግራይ ወደ ሱዳን የሚደረገው የአውሮፕላን በረራ መደበኛ እስኪመስል ድረስ መደጋገሙን የሚያነሱ ጸሃፊ አሁን ለምሳሌ ከ5 ቀን በፊት አማኑኤል ተስፋይ ከትግራይ ወጥቶ ካርቱም ውስጥ ታይቶ ነበር።ከሁለት ቀናት በፊት ደግሞ ወደ ትግራይ ተመልሷል። በያን ሰሞን የወያኔ ሰዎች ለድርድር ካርቱም እንደገቡ አንድ የሱዳን የመረጃ ምንጬ ጠቁሞኝ ነበር።መረጃው ዝርዝር ነገር ስላልነበረው ችላ ብዬ ተወኩት።አሁን ግን መረጃው እውነትነት ሳይኖረው አይቀርም” ሲሉ መላ ምት ያቀርባሉ። “የእርዳታ እህል የጫኑ አንቶኖቭ አውሮፕላኖችም ከሱዳን ወደ ትግራይ የሚያደርጉትን በረራ መቀጠላቸውን የCrisis ግሩፑ ዊሊያም ዴቪሰን መናገሩ ለትህነግ ካለው ቅርበት ጋር ተያይዞ መላምቱን ወደ ጭብጥ ያመራዋል። ምን አልባትም “የለንም” ያሉትን በትከሻ የሚጫነውን አየር መቃወሚያ አድርሰዋቸው እንዳይሆንም ያሰጋል።

“የህወሓት ፅ/ቤት ሃላፊው አለም ገብረዋህድ ከግምባር የተመለሱትም(ቁስለኛውም ፤የሸሸውም) ቢሆን አስር ቀን ሰልጥነው በድጋሚ መዝመት አለባቸው። አሃድ(ጓድ) የነበረው ቀድሞ ወደ ነበረበት አሃድ(ጓድ) ይመደባል።አሃድ የሌለው ወደ አዲስ አሃዱ ይመደባል።እነሱን መልሰን እንዲዘምቱ ካላደረግን አዳዲስ ልጆችን እንዲዘምቱ ማድረግ አንችልም።አንድ ሰው መቅረት የለበትም።ይሄን የማያደርግ አመራር ካለ እንዳናየው ፤ከፊታችን ዞር ይበል” ሲሉ የሚናገሩትበትን ቪዲዮ በማስረጃነት በማቅረብ ትርጉሙን ቀንጭበው ካጋሩት ላይ አይተናል።

አሁን ያለው ጉዳይ አሜሪካ የትጋር ናት የሚለው ነው። አሜሪካ በሩሲያና በዩክሬን ጉዳይ የችግሩ ጠማቂ ነችና ስራ በዝቶባታል። እናም የትህነግን ጉዳይ እንደወትሮዋ ትይዘዋለች? የምል ጥያቄ የሚያነሱ አሉ። ሰሞኑን አሜሪካ ወደ ግምጃ ቤት የመለሰቸው ረቂቅ ህግ አለመጽደቁ፣ ከዓለም ባንክና የዓለም የፋይናንስ ተቋማት ጋር የተፍታታ ግንኙነት መጀመሩ፣ የሰላም ተስፋና ጭላንጭል መታየቱን ማድነቋ፣ አንዳንድ ሚዲያዎች አቋማቸው ባይቀየርም እንደወትሮው የኢትዮጵያን ጉዳይ የሙሉ ስራቸው አለማድረጋቸው፣ ወዘተ ከአውሮፓ ህብረት አገራት ጋር ግንኑነቱ መቀጠሉና ” ቲዎድሮስ አድሃኖም ” ተስፋ ቆርጫለሁ” ማለታቸው የሆነ ነገር አመላክች እንደሆነ ስምምነት አለ።

በሌላ በኩል ደግሞ ኤርትራ ለሩሲያና ቻይና ቀይ ባህርን “እንዳሻችሁ” ማለቷ አሳሳቢ የሆነባት አሜሪካ፣ ኤርትራ ከፍተኛ ሚስጢር የተባለ የጦር ስምምነት ከሩሲያ ጋር ማድረጓ ለቀጠናው የአሜሪካን የበላይነት ስለማያመች ኢትዮጵያን በመጫን የትግራይ ነጻ አውጪ ሃይሎች ኤርትራን እንዲወጉ ታስቦ ሊሆን እንደሚችል የሚገምቱ አሉ።

ከሁሉም ወገን መላምቶች ቢኖሩም አንድ ሃቅ ግን ሻቢያ፣ ትህነግና የኢትዮጵያ መልከላከያ በዝግጅት ላይ ናቸው። ሱዳንም ብርድ ብርድ እንዳላት እያስታወቀች ነው። ይህ የተረዱ በጎነደር ሰላም እንዲናጋ የኢትዮጵያን ማሊያ ለብሰው በሚጫወቱ ሃይሎች አማካይነት እየታተሩ ነው። ፓርላማን ተሸሽገውና መብቱን ተገን አድርገው በመጋመድ የሚሰሩ አሉ።

ማሳሰቢያ – ከተለያዩ ማህበራዊ አውዶች የተጠቀምናቸው በብዛት ስለተሰራጩና ባለቤቶቹ ስለተምታቱ በጥቅሉ ከማህበራዊ ገጽ የወሰድናቸው ናቸው ከማለት ያለፈ ለመዘርዘር አልቻልንም።

Leave a Reply