የፕሬስ ነፃነትን እንደ ሽፋን በመጠቀም የሀሰት መረጃ የሚያሰራጩ ጋዜጠኞች አሉ

– ሙያዊ ሥነ ምግባር አክብረው የሚሠሩ ጋዜጠኞችን ከጥቃት መጠበቅ እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፡- ሙያዊ ሥነ ምግባር አክብረው የሚሠሩ ጋዜጠኞችን ከሚደርስባቸው ጥቃት መጠበቅ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃንና የዩኔስኮ ኃላፊዎች አስገነዘቡ።

የፕሬስ ነፃነትን እንደ ሽፋን በመጠቀም በሃይማኖት፣ በብሔርና በተለያየ መንገድ አሳሳች መረጃዎች የሚያሰራጩና ችግር እየፈጠሩ ያሉትን ጋዜጠኞች ከድርጊታቸው መታቀብ እንደሚኖርባቸውም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት የዓለም ፕሬስ ነፃነት ቀን ምክንያት በማድረግ «ጋዜጠኝነት በዲጂታሉ ዓለም ውስጥ» በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት ውይይት አድርጓል።

በወቅቱ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ሰብሳቢና የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤት አቶ አማረ አረጋዊ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሙያዊ ሥነ ምግባር አክብረው የሚሠሩ ጋዜጠኞችን አስፈላጊውን ከለላ በማድረግ ከጥቃት መከላከል ይገባል። በተለይም መንግሥት ጋዜጠኞችን ከጥቃት በመከላከል ረገድ አስፈላጊውን ኃላፊነት መወጣት ይኖርበታል።

ሙያዊ ሥነምግባርን በተከተለ መንገድ መረጃን ለኅብረተሰቡ ለማድረስ የሚጥሩ ባለሙያዎች እንዳሉ ሁሉ ሰዎችን ለግጭትና ለአላስፈላጊ መከፋፈል የሚዳርጉ ሃሰተኛ መረጃዎችንም የሚያሰራጩ ጋዜጠኞች መኖራቸውን ጠቁመው፤ በተለይ የፕሬስ ነፃነትን እንደ ሽፋን በመጠቀም በሃይማኖት፣ በብሔርና በተለያየ መንገድ አሳሳች መረጃ የሚያሰራጩና ችግር እየፈጠሩ ነው ብለዋል።

ይህ የተሳሳተ አካሄድ እንዲቆም ለማድረግ ከሁሉም ወገን የተደራጀ ጥረት ይጠበቃል። በዚያው ልክ ደግሞ ሙያዊ ግዴታቸውን እየተወጡ የሚገኙና ትክክለኛ መረጃ ላይ ተመርኩዘው የሚሠሩትን ጋዜጠኞች ደግሞ  ከሚደርስባቸው አሉታዊ ተጽዕኖ መጠበቅ ያስፈልጋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር ዩሚኮ ዮኮዘኪ እንደገለጹት ደግሞ፤ የዓለም ፕሬስ ነፃነት ቀን ሲከበር በችግር ውስጥ ያሉ ጋዜጠኞችንም ከጥቃት ስለመጠበቅ ማሰብ ያስፈልጋል።

ጋዜጠኞች በተረጋጋ መንገድ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ በማድረግ ከጉዳት መጠበቅ ያስፈልጋል። የፕሬስ ነፃነት ሲታሰብም በተለያየ ምክንያት ከሥራ ገበታቸው በኃይል እንዲርቁ የተደረጉ፣ ጉዳት የደረሰባቸውንና በተጽዕኖ ውስጥ ያሉትንም በማሰብ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

መረጃ በተሳካ ሁኔታ ለሕዝብ ለማድረስ የጋዜጠኛው ደህንነት መጠበቅ አለበት ያሉት ዳይሬክተሯ፤ በተለይ በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ጋዜጠኞች በተለያየ ምክንያት ለጥቃት እንደሚጋለጡ ጠቁመው፤ ይህንና ተያያዥ ችግሮችን በጋራ በማስወገድ ተጽዕኖዎቻቸውን ማስቀረት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአሃዱ ሬድዮ ኃላፊ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በበኩሉ እንደገለጸው፤ የጋዜጠኛውን ደህንነት በሚያናጋ መልኩ የሚከናወኑ እንቅስቃሴዎች በሙያው ላይም ተጽዕኖ ይፈጥራሉ። በመሆኑም ባለሙያው ያለስጋት የሚሰራበትን መንገድ በማመቻቸት ትክክለኛው መረጃ ኅብረተሰቡ ዘንድ እንዲደርስ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል።

ኃላፊነት የጎደለው የማህበራዊ ሚዲያዎች አጠቃቀም በአገር ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው። ይህን ለመከላከል ሙያውን አክብሮ የሚሰራውን ጋዜጠኛ በመጠበቅ ትክክለኛ መረጃዎች እንዲስፋፉ ማድረግ ይገባል። በዚህ ረገድ የተደራጀና ከንግግር ያለፈ ዕርምጃ ይጠበቃል ብሏል።

በተለይ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤትና የሚመለከታቸው ተቋማት የጋዜጠኛውን መብት በማስጠበቅ ረገድ የተጠናከረ ሥራ ሊያከናውኑ እንደሚገባ ገልጿል።

ጌትነት ተስፋማርያም

አዲስ ዘመን  ንቦት 2/2014

Related posts:

በሳዑዲና ኢራን በሞት የሚቀጡ ሰዎች ቁጥር ጨምሯልMay 26, 2022
የመሰረተ ልማት ቀበኞች ላይ " የሞት ቅጣት"May 26, 2022
ኢሳያስ - ዘመቻው እስከ መጨረሻ ቀብር ይሆናል ሲሉ ትህነግን አስጠነቀቁMay 25, 2022
በአማራ ክልል እፎይታ እየነገሰና የትህነግ የወረራ ዕቅድ መምከኑ ተሰማMay 25, 2022
ንግድ ባንክ ለአፈር ማዳበሪያ ግዥ ከ50 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን አስታወቀMay 25, 2022
ቢለኔ ታይም መጽሔትን ማብራሪያ ጠየቁ፤ የተሰላ ጥቃትና የአንድ ወገን ትርክት ማቅረቡን ኮንነዋልMay 25, 2022
"ከውስጥ በር ለማስከፈት ... ከጣራ በላይ ጩኸት" አብን አማራን ለሶስተኛ ዙር ወረራ እያመቻቹ ያሉትን በይፋ አወገዘMay 24, 2022
በኢትዮጵያ በተከሰቱ ግጭቶች ሁሉ የትህነግ እጅ እንዳለባቸው በመረጃ ተረጋገጠMay 24, 2022
ፋኖ እየጨፈረ ከመከላከያና አማራ ልዩ ሃይል ጋር የግዳጅ ቀጠናውን ተረከበMay 23, 2022
ተልዕኮ አስፈጻሚዎችና ከ1780 በላይ ሕዝባዊ ኀላፊነታቸውን ያልተወጡ ተጠርጣሪዎች ተያዙMay 23, 2022
በሕግ ማስከበር ዘመቻ ከ4 ሺህ በላይ ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ስር ዋሉMay 23, 2022
በአማራ ክልል መፈንቅለ መንግስት ታቅዶ ነበርMay 23, 2022

Leave a Reply