ስለ ፈለገ ዮርዳኖስ… የቀድሞ የፈሌ ተማሪ


ዳዊት ከበደ የተባሉ የቀድሞ የፈሌ ተማሪ ” ስለ ፈለገ-ዮርዳኖስ ት/ቤት ይህን ያውቁ ኖሯል?” በሚል ከ10 አመት በፊት የፃፉትን አንድ ፅሁፍ ወዳጆቼ አጋርተውኝ አነበብኩት። የወደድኩት እና ወደ ኋላ ዘመናትን የመለሰኝን ፅሁፍ በመሆኑ ላጋራችሁ ወዲህ አምጥቼዋለሁ።


1- የፈለገዮርዳኖስ ት/ቤት መስራች አቶ ሲሳይ ገብረጻዲቅ፤ ሰነፍ ተማሪዎችን ብቻ ሳይሆን ሰነፍ አስተማሪዎችንም ይገርፉ ነበር።

2- አስቤስቶስ በሳምባ ላይ በሚያመጣው ካንሰር ምክንያት፤ በአለማችን ላይ እንዳይመረትም ሆነ፤ በጥቅም ላይ እንዳይውል ታግዷል።

ከአርባ አመት በፊት በፈለገዮርዳኖስ ውስጥ ጥቁር ሰሌዳውን ጨምሮ በርካታ የመማሪያ ክፍሎች የተሰሩት ከአስቤስቶስ ሲሆን፤ ብዙ ሺህ ተማሪዎች በ’ነዚህ የአስቤስቶስ ክፍሎች ውስጥ ተምረዋል።

3-በፈለገ ዮርዳኖስውስጥ ከ6ኛ – 8ኛ ያሉት ተማሪዎች ቀይ ኮከብ እና ድል በትግል በሚል ለሁለት የሚከፈሉ ሲሆን፤ ከዚያ በፊት ግን ተማሪዎች የሰሜን፣ የደቡብ፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ዞን ተብለው ይከፈሉ ነበር። ሳምንታዊ ውድድርም በነዚህ ዞኖች መካከል ይደረግና ለአሸናፊዎች የደስ ደስ በሬ ይታረድላቸዋል።

4- በ19ስልሳዎቹ መጨረሻ ላይ የቀብር ስነ ስርአታቸው በከፍተኛ ድምቀት ከተፈጸመላቸው ሰዎች መካከል የፈለገ ዮርዳኖስ መስራች አቶ ሲሳይ አንዱ ነበሩ። በቀብራቸው ላይ ከአስር ሺህ በላይ ሰዎች ሲገኙ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ተማሪዎቻቸው ናቸው።

5- በኢትዮጵያ የአንደኛ እና መለስተኛ ትምህርት ቤቶች ታሪክ ውስጥ፤ በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ሁለት ዞን ያሉበት፤ ሁለቱንም የተለያዩ አስተማሪዎች የሚያስተምሩበት ቦታ ፈለገ ዮርዳኖስ ነበር።

6- በአንድ ጊዜ ከአንድ ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለስድስተኛና ስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ፈተና አስፈትኖ፤ ሁሉም የሚያልፉበት ትምህርት ቤት ፈለገ ዮርዳኖስ ተብሎ ይጠራል።

7- በ1973 ዓ.ም. በወቅቱ የትምህርት ሚንስትር ኮ/ል ጎሹ ወልዴ ተጎብኝቶ፤ ከሁሉም የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የላቀ በመሆኑ የመንግስት እርዳታ የተሰጠው፤ በህዝብ ድጋፍ የራሱን የፎቅ የገነባ የመጀመሪያው መለስተኛ የህዝብ ትምህርት ቤት ፈለገዮርዳኖስ ነበር።

8- የትምህርት ሰዓት ካለቀ በኋላ፤ የራሱ “የጥናት ፔሬድ” የነበረው ፈለገ ዮርዳኖስ ነበር።

9- ያጠፉና የሰነፉ፤ የረበሹና ያረፈዱ ተማሪዎች ያለ ርህራሄ የሚገረፉበት ቦታ ፈለገዮርዳኖስ ነው።

10- ግርፊያ እንደሙያ ተቆጥሮ “ገራፊ” ተቀጥሮ የሚሰራበት ትምህርት ቤት ፈለገዮርዳኖስ ይባላል።

11- ከአስተማሪዎች እጅ ጠመኔና መጽሃፍ እንደማይጠፋው ሁሉ፤ እያንዳንዱ አስተማሪ የቺንጋ መግረፊያ ይዞ የሚታይበት ትምህርት ቤት ፈለገዮርዳኖስ ነው።

12- ተማሪዎች እንደ እንግሊዝ ፕሪሚየም ሊግ ጨዋታ ውጤቱን በናፍቆት የሚጠባበቁት፤ በየሳምንቱ ቅዳሜ የተማሪዎች ውድድር የሚካሄድበት ስፍራ የሚገኘው ፈለገዮርዳኖስ ውስጥ ብቻ ነበር።

13- ተማሪዎች ከሌላው ትምህርት ቤት ተለይተው፤ የራሳቸው ልዩ ዘፈን የነበራቸው በፈለገዮርዳኖስ ውስጥ ነው። የዘፈኑም መጠሪያ… “ተናፋቂዋ ቅዳሜ፤ ትመጫለሽ በህልሜ…” የሚል ነበር።

14- ፈለገዮርዳኖስ ታዋቂ ሰዎችን ለአገሪቱ አበርክታለች። ሁለቱን ለመጥቀስ ያህል አርቲስት አስቴር አወቀ እና የሰን ሻይን ኮንስትራክሽን ባለቤት ተጠቃሾች ናቸው።

15- በቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚገኙት ትላልቅ ሃውልቶች መካከል፤ ከአትሌት አበበ ቢቂላ ቀጥሎ ጎልቶ የሚታየው የፈለገ ዮርዳኖስ መስራች የአቶ ሲሳይ ሃውልት ነበር።

16- በፌስ ቡክ ውስጥ ካሉት የኢትዮጵያ ትምህርት ቤት ግሩፖች ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፈለገ ዮርዳኖስ ተማሪዎች የፌስ ቡክ ግሩፕ መሆኑን ያውቃሉ?

(እባክዎን ሌላም እኛ የምናውቀው፤ ሌሎች ግን የማያውቁት ነገር ካለ ይጨምሩበት።)

የፅሁፉ ባለቤት:- Dawit Kebede /February 15, 2012

Leave a Reply