Site icon ETHIOREVIEW

ፊንላንድ 3.6 ሚሊዮን ሕዝብ የሚይዙ ዋሻዎች አዘጋጀች – ለኢትዮጵያውያን ጠቃሚ የጥንቃቄ መረጃ

የሄልስንኪ ከተማ 900ሺ ሰዎችን የሚይዙ ከ5ሺ 500 የሚልቁ ዋሻዎችን አዘጋጅታለች

በፊንላንድ ነዋሪ ለሆናችሁ ኢትዮጵያውያን ጠቃሚ የጥንቃቄ መረጃ፤

በቀጣዮቹ ቀናት ፊንላንድ ከስዊድን ጋር ኔቶን ልትቀላቀል መሆኑን ተከትሎ ሩሲያ ጥቃት ልትፈጽም ትችላለች በሚል የፊንላንድ መንግሥት አስፈላጊውን ዝግጀት ማድረጉን፣ ሆኖም ዜጎች ሊወስዷቸው ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች ማሳሰቢያዎችን ደጋግሞ አውጥቷል፡፡ ሩሲያ ፊንላንድ ላይ በትክክል ጥቃት ልትፈጽም ትችላለች አትችልም የሚለውን ጉዳይ ትተን ነዋሪው ሊያደርጋቸው ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎችና የመንግሥትን ዝግጅት ማሳወቅ የዚህ ማስታወሻ ጭብጥ ነው፡፡ ሐሳቦቹ በሱዋሚ፣ በስዊድንኛና በእንግሊዝኛ ከቀረቡ የመንግሥት ማሳሰቢያዎች የተወሰዱ ናቸው፡፡

1) በፊንላንድ መንግሥት የተደረጉ ዝግጅቶች፤

በአገሪቱ ባሉ ትልልቅ ከተሞች ኑክሊየርን ጨምሮ ማናቸውንም ዓይነት ጥቃት መመከት የሚችሉ ለወራት ውኃ፣ ኤሌክትሪክ፣ የሕፃናት መጫወቻ፣ ስፖርት ማዘውተሪያ ወዘተ ያላቸው 3.6 ሚሊዮን ሰዎችን የሚይዙ መጠለያ ዋሻዎች (Civil Defence shelters) ዝግጁ ሆነዋል፡፡ የከተማ ማዘጋጃዎች የእነዚህን መጠለያ ዋሻዎች ያሉባቸውን ቦታዎች በየድረገፃቸው ለነዋሪዎች ግልጽ አድርገዋል፡፡

አብዛኛው ሐበሻ የሚኖርባት የሄልስንኪ ከተማ 900ሺ ሰዎችን የሚይዙ ከ5ሺ 500 የሚልቁ ዋሻዎችን አዘጋጅታለች፡፡ እንደ ከተማ አስተዳደሩ መረጃ በካሊዮ፣ ፓሲላ፣ ኮንቱላና ካምፒ እያንዳንዳቸው ከ10ሺ በላይ ሰዎችን መያዝ የሚችሉ ዋሻዎች አሉ፡፡ በአጠቃላይ በሔልስንኪ የከተማዋንና በአቅራቢያ ያሉ ዜጎችን መያዝ የሚችል አቅም ያላቸው ዋሻዎች ዝግጁ ናቸው፡፡

2) እንዴት የመጠለያ ጣቢያዎችን (ዋሻዎችን) ማግኘት ይቻላል?

የአደጋ ጊዜ መጠለያ ጣቢያዎች ዓለም አቀፋዊ ምልእክት የሆኑ ሰማዊያ ጎነሦስቶች በቢጫ መደብ በአቅራቢያቸው አለ፡፡ መንግሥት እንደአስፈላጊነቱ ወደዚያ ሊወስዱ የሚችሉ መንገድ ጠቃሚዎችን አዘጋጃለሁ ብሏል፡፡ በተጨማሪም በምትኖሩበት ከተማ ሁሉም ማዘጋጃ ቤቶች የስልክ ቁጥሮችን አስቀምጠዋል፡፡ በ112 የሞባይል አፕም መጠየቅ ይቻላል፡፡

3) ዋሻዎቹ ጋ መቼ ነው የሚያስፈልጉት?

መንግሥት ሁኔታዎችን አገናዝቦ ውሳኔ ያሳልፋል፤ ከዚያ በየ7 ሰከንድ የሚወጣና የሚወርድ ለአንድ ደቂቃ የሚቆይ የአደጋ ደወል /ሳይረን/ በድምጽ ማጉያዎች በሁሉም ቦታ ይሠማል፡፡

4) ወደ መጠለያ ዋሻዎቹ ስሄድ ምን መያዝ አለብኝ?

የማንነት መታወቂያ፣ ከ2-3 ቀናት ሊሆኑ የሚችሉ ምግብና መጠጥ፣ አስፈላጊ የሕክምና መድኃኒቶች፣ የጽዳት እቃዎች፣ የመኝታ ቦርሳዎች /ፍራሻ፣ ባትሪ፣ የመጫዎቻ እቃዎች፣ የሚነበቡ መጽሐፍት፣ የአዮዲን እንክብሎችን መያዝ ይመከራል፡፡ የአዮዲን እንክብሎች ለጤና ጠንቅ የሆነ የኑክሊየር ሐረር በአየሩ ቢረጭ እንክብሎቹ እጅግ አስፈላጊ በመሆናቸው ነው፡፡

በተረፈ ይህ የጥንቃቄ መልእክት የፃፍኩት ኢትዮ ፊኒሾችን መረጃው እንዲኖራቸው በሚል እንጅ አላስፈላጊ ድንጋጤን ለመፍጠር እንዳልሆነ ይሠመርበት፡፡

Exit mobile version