Site icon ETHIOREVIEW

የ18 ዓመቱ ጎረምሳ በኒውዮርክ የገበያ አዳራሽ በጥይት እሩምታ አስር ሰው አጠፋ

በኒውዮርክ የመገበያያ አዳራሽ በተከፈተ ተኩስ የአስር ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን ጥቃቱ ዘርን መሰረት ያደረገ የጥላቻ ወንጀልም ነው በሚል ፖሊስ ምርመራ ከፍቷል።

ጥቃቱን ፈጽሟል የተባለ የ18 አመት ወጣት በቡፋሎ ከተማ በቁጥጥር ስር ውሏል። ፖሊስ የግለሰቡን ማንነት ይፋ አላደረገም። ተጠርጣሪው ቅዳሜ ከሰአት በኋላ በተጨናነቀ የመገበያያ አዳራሽ ከገባ በኋላ ነው ተኩስ የከፈተው።

ጥቃቱን በበይነ መረብ በቀጥታ ለማስተላለፍም ካሜራ ተጠቅሟል ሲል ፖሊስ ተናግሯል። ኤፍቢአይ ጥቃቱን “ሁከተኛ አክራሪነት” ሲል ገልጾታል።

“ይህንን ጥቃት የጥላቻ ወንጀል እና በዘር ላይ የተመሰረተ አክራሪነት በሚል ነው ነው እየመረመርነው ነው” በማለት የኤፍቢአይ ቡፋሎ ፅህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት እስጢፋኖስ ቤሎንግያ በአንድ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

ተጠርጣሪው በከተማዋ ጥቁሮች በብዛት ወደሚገኙበት አካባቢ ለመድረስ ለበርካታ ሰዓታት መኪና ማሽከርከሩ ተሰምቷል። የቡፋሎ ፖሊስ ኮሚሽነር ጆሴፍ ግራማሊያ እንዳሉት 13 ሰዎች በጥይት የተመቱ ሲሆን አብዛኞቹ ጥቁሮች ናቸው።

በመገበያያ አዳራሹ ውስጥ የሚሰሩና በተኩስ ጉዳት የደረሰባቸው ሶስቱ ግለሰቦች ለሕይወት የሚያሰጋ ጉዳት አልደረሰባቸውም።

በመገበያያ አዳራሹ በጥበቃ ስራ ላይ የነበረ አንድ ጡረታ የወጡ ፖሊስ ተጠርጣሪው ላይ በጥይት ለመተኮስ ቢሞክሩም በዚህ ጥቃት ከተገደሉት መካከል አንዱ ሆነዋል።

ተጠርጣሪው ከፍተኛ ሃይል ያለው ሽጉጥ፣ የሰውነት መከላከያ ትጥቅ እንዲሁም የጭንቅላት መከላከያ ሄልሜት አድርጎ እንደነበር ፖሊስ ተናግሯል።

ከመታሰሩ በፊት በተፈጠረ ውጥረት የተነሳ መሳሪያውን አስረክቧል።

ግለሰቡ በመጀመሪያ ደረጃ ግድያ ወንጀል መከሰሱንና ተጨማሪ ክሶችምሊቀርቡበት እንደሚችል የኤሪ ካውንቲ ወረዳ አቃቤ ህግ ጆን ፍሊን ተናግረዋል ሲል የዘገበው ቢቢሲ አማርኛው ነው።

Exit mobile version