ሀሰተኛ ሰነዶችን በመገልገል ከ13 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ ያደረገው ተከሳሽ በፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነበት

ሀሰተኛ መንግስታዊ ሰነዶችን በመገልገል ከኢትዮጵያ መድሐኒት ፈንድ እና አቅርቦት ኤጀንሲ የባንክ ሂሳብ ላይ ለግል ጥቅሙ ከ13 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ ያደረገው ተከሳሽ በፅኑ እስራትና በገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ ተወሰነበት

ተከሳሹ ከተወሰነበት የፅኑ እስራትና የገንዘብ ቅጣት በተጨማሪ ያለአግባብ ለግል ጥቅሙ ወጭ ያደረገውን ገንዘብ ለመንግስት ተመላሽ ለማድረግ የውርስ ማመልከቻ ለፍርድ ቤት ለማቅረብ የሚመለከተው አካል መዝገብ መረከቡን ማወቅ ተችሏል።

የቅጣት ውሳኔውን ያሳለፈው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ፀረ ሙስና ወንጀል ችሎት ነው ።

አንተነህ እንዳለ የተባለው ተከሳሽ የተለያዩ ሀሰተኛ መንግስታዊ ሰነዶችን በመገልገል ከኢትዮጵያ መድሐኒት ፈንድ እና አቅርቦት ኤጀንሲ የባንክ ሂሳብ ላይ ለግል ጥቅሙ ከ13 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ በማድረጉ ነው በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ህግ ዳይሬክቶሬት ጄነራል ክስ የተመሰረተበት ።

ተከሳሽ የማይገባውን ብልፅግና ለማግኘት በማሰብ ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ገነት ቅርንጫፍ በአካል በመገኘት ስልጣን ባለው አካል ባልተመዘገበ የብርሃን ድንበር ተሻጋሪ የደረቅ ጭነት ማመላለሻ ማህበር በተባለ ሀሰተኛ የድርጅት ሥም የባንክ ሂሳብ ለመክፈት ሃሰተኛ በሆኑ የድርጅቱ ሥም የተዘጋጀ የንግድ ስራ ፍቃድ ߹የንግድ ምዝገባ ምስክር ወረቀት߹ የግብር ከፋይ ምዝገባ ሰርተፍኬት߹የመመስረቻ ፅሁፍና መተዳደርያ ደንብ እንዲሁም በሀሰተኛ ሥም በተዘጋጀ መታወቂያ ይዞ በማቅረብ ባንኩ በከፈተለት ሃሰተኛ የማህበሩ ተንቀሳቃሽ ሂሳብ ቼክ በመውሰድ ጥር /18/2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ መድሐኒት ፈንድ እና አቅርቦት ኤጀንሲ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካለው ሂሳብ በቼክ ተቀንሶ ለሃሰተኛው የድርጅቱ ማህበር በኤጀንሲውና በማህበሩ መካከል ምንም አይነት ግብይት ባልተደረገበት ሁኔታ ከኤጀንሲው ሂሳብ ላይ ተቀንሶ ቡና ባንክ ወዳለው ሃሰተኛ የድርጅቱ ሂሳብ አንዲገባለት ያዘጋጀውን የኢትዮጵያ የንግድ ባንክ ቼክ ለቡና ኢንተርናሽናል ባንክ በማቅረብ 13‚091‚000‚00 ( አስራ ሶስት ሚሊየን ዘጠና አንድ ሺህ ብር ) ያስተላለፈ ሲሆን ገንዘቡ ከገባለት በኋላ በራሱና በሌሎች ማንነታቸው አንዳይታወቅ በሃሰተኛ መታወቂያ የባንክ ሂሳብ በከፈቱ ግለሰቦች ሥም ወጭ በማድረግ በህዝብና በመንግስት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ በመሆኑ በፈፀመው ሀሰተኛ መንግስታዊ ሰነድ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀልና በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ በማቅረቡ ነው በሁለት ወንጀሎች ክስ የተመሰረተበት ።

ተከሳሽ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ፀረ ሙስና ወንጀል ችሎት ቀርቦ ክሱ ደርሶትና ተነቦለት የእምነት ክህደት ቃሉን ሲጠየቅ ” እኔ ድርጊቱን አልፈፀምኩም ጥፋተኛም አይደለሁም ”ሲል ቃሉን ሰጥቷል ።

ዐቃቤ ህግ በበኩሉ የተከሳሽን ጥፋተኝነት ለፍርድ ቤቱ ያስረዱልኛል ያላቸውን ዝርዝር የምስክሮች ቃል እና የሰነድ ማስረጃዎች በበቂ ሁኔታ ለችሎቱ በማስረዳቱ ተከሳሽ ዐቃቤ ህግ ያቀረበበትን ክስ አንደ ክስ አመሰራረቱ መከላከልና ማስተባበል ባለመቻሉ ግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤት በተከሳሽ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላልፏል ።

በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ ያቀረባቸውን ስድስት የቅጣት ማቅለያዎች ከግምት በማስገባት በ11 ዓመት ፅኑ እስራትና በ5‚500 ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ ወስኖበታል ።

ተከሳሹ ከተወሰነበት የፅኑ እስራትና የገንዘብ ቅጣት በተጨማሪ ያለአግባብ ለግል ጥቅሙ ወጭ ያደረገውን ገንዘብ ለመንግስት ተመላሽ ለማድረግ በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ጄነራል በንብረቱ ላይ የውርስ ማመልከቻ ለፍርድ ቤት ለማቅረብ ይህን መዝገብ መረከቡን ማወቅ ተችሏል ።

Via attorney general

Leave a Reply