«የግል የትምህርት ተቋማት የሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የሚታደልባቸው እየሆኑ መጥተዋል»

የግል የትምህርት ተቋማት የሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የሚታደልባቸው እየሆኑ መጥተዋል-የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ

በርካታ የግል የትምህርት ተቋማት የሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የሚታደልባቸው እየሆኑ በመምጣታቸው ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት፣ሥራ ሥምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን በመገኘት የመስክ ምልከታ አድርጓል።

ተቋሙ ሥራውን በአግባቡ ለማከናወን የሚያስችለው ምቹ የሥራ ቦታ የሌለው መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው ተመልክቷል።

የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዱዓለም አድማሴ፤ ተቋሙ በተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎችም ውስጥ ሆኖ ኃላፊነቱን ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል።

ለሰራተኞች ቢሮ ምቹ ካለመሆኑ በተጨማሪ የቢሮ እጥረት በመኖሩ በአንድ ክፍል ውስጥ ከ30 በላይ ሰራተኞች በተጨናነቀ ሁኔታ ለመሥራት መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡

የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ከፍተኛ አገራዊ ኃላፊነት ተጥሎበት የሚሰራ ተቋም ቢሆንም ሰፊውን ሴክተር በበቂ ሁኔታ መፈጸም የሚችል የሰው ኃይል አደረጃጀት አለመኖሩንም ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

ሕገ-ወጥ የትምህርት ማስረጃ እና ሕገ-ወጥ ተቋማት በየቦታው እየተበራከቱ በመሆኑ ችግሩን ለማስተካከል ቀደም ሲል ከቋሚ ኮሚቴው ጋር መምከራቸውን አስታውሰዋል።

በምክር ቤቱ የሰው ሃብት ልማት፣ሥራ ሥምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ስብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ፤ በርካታ የግል የትምህርት ተቋማት የሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የሚታደልባቸው እየሆኑ መጥተዋል ብለዋል።

የትምህርት ዘርፍ ለአገር ግንባታ ዋነኛ መሰረት መሆኑን ገልጸው፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ቀልጣፋና ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋት ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።

ከሚመለከተው አካል ተገቢ ፈቃድ ሳይሰጣቸው የሚሰሩ ተቋማት እርምጃ ሊወሰድባቸውና በሕግም ሊጠየቁ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ለዚህ ተግባር በተለይም የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ከፍተኛ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን የገለጹት ዶክተር ነገሪ የቁጥጥርና ክትትል ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

በተቋሙ ለሥራ አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎች በተቻለ መጠን መስተካከል እንዲችሉ ቋሚ ኮሚቴው አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ስብሳቢ ዶክተር ኽይረዲን ተዘራ፤ የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ አንጻር እንደ አገር ተቋሙ ትልቅ ተልዕኮ የተሰጠው በመሆኑ የሁሉንም ድጋፍና እገዛ ይጠይቃል ማለታቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።

በውስን የሰው ኃይል እና ምቹ ባልሆነ የሥራ ቦታ ተቋሙ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን አድንቀው ችግሮች እንዲፈቱ ቋሚ ኮሚቴው ከጎኑ እንደሚቆም አረጋግጠዋል፡፡

በባለሥልጣኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኘው የሂሳብና ሳይንስ ትምህርቶች ማሻሻያ ማዕከል በርካታ ቢሮዎች ከአሥር ዓመታት በላይ ተዘግተው መቆየታቸው ተገቢ አለመሆኑን ቋሚ ኮሚቴው አስገንዝቧል።

የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ከዓለም ባንክ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ባለ ሰባት ወለል ህንጻ ለማስገንባት በሂደት ላይ መሆኑ ታውቋል። (ኢ ፕ ድ)

You may also like...

Leave a Reply