“የሕግ የበላይነትን የማስከበር ተግባር ዋና ዓላማው ክልሉ ከወንጀለኞች የፀዳ ኾኖ እና አንድነቱ የተጠበቀ ሕዝብ ኖሮት ሊመጣ የሚችልን ጠላት ኹሉ በብቃት ለመመከት ነው” በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ ሰማ ጥሩነህ (ዶ.ር)

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ ሰማ ጥሩነህ (ዶ.ር) በወቅታዊ የሕግ ማስከበር ተግባር ላይ ለአሚኮ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

“በአማራ ክልል እየተከናወነ ያለው የሕግ የበላይነትን የማስከበር ተግባር ዓላማው የክልሉን ሕዝብ በሰላም ወጥቶ የመግባትና የመሥራት መብት ለማረጋገጥ ነው” ብለዋል።

በክልሉ አፈና፣ ዝርፊያ፣ ግድያ፣ በሃይማኖት ሰበብ ግጭት ቀስቃሽነት እና ሌሎችም ወንጀሎች በርከት ብለው በመስተዋላቸው ይህንን ለመቅረፍ ወደተቀናጀ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራ ተገብቷል ነው ያሉት። ዋና ዓላማውም “ክልሉ ከወንጀለኞች የፀዳ ኾኖ እና አንድነቱ የተጠበቀ ሕዝብ ኖሮት ሊመጣ የሚችልን ጠላት ኹሉ በብቃት ለመመከት ነው” ብለዋል።

የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥና በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን በሚደረገው እንቅስቃሴ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ በተቀናጀ አሠራር እየተሳተፉ መኾኑንም አንስተዋል። በየአካባቢው የሚገኝ በርካታ ሕዝብም ከፀጥታ አካላት ጎን ቆሞ ድጋፉን እየሰጠ ነው ብለዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ ሕዝብን ወደ ቁጣ ለማስገባትና ለጠላት በር ለመክፈት የሚጥሩ ተላላኪዎች አፍራሽ ተግባር ላይ ተጠምደው እንደሚገኙ አረጋግጠናል ያሉት ዶክተር ሰማ ሕዝቡ ከነዚህ አካላት ማደናገሪያ ራሱን ማራቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

“ወደተቀናጀ የሕግ የበላይነትን የማስከበር እንቅስቃሴ የተገባው ከሕዝቡ ጋር በየደረጃው ውይይት ከተደረገ በኋላ ነው” ያሉት ዶክተር ሰማ “መንግሥት የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብር የሕዝቡ የዘወትር ጥያቄ ነበር” ብለዋል። በዚኽም መሠረት ማኅበረሰቡን የሚዘርፉ፣ እረፍት የሚነሱ እና ትልልቅ ከተሞችን ጭምር የጦርነት ቀጣና ለማድረግ የሚሹ አካላትን የመለየትና በሕግ አግባብ ብቻ ወደ ተጠያቂነት እንዲሰፍን የማድረግ ሥራ ተገብቷል ብለዋል። እነዚህ አካላት የአማራን ሕዝብ ከፋፍሎ የማዳከምና ለጠላት የማጋለጥ ተልዕኮም ይዘው እንደሚንቀሳቀሱ በጥናት እንደተደረሰበት አመላክተዋል።

ቀድሞውንም ቢኾን ጠላት አማራ ክልልን ሊወር የቻለው በውስጥ ተላላኪዎቹ አማካኝነት እንደኾነም ገልጸዋል። አሁን ግን ያለፈው እንዲደገም የክልሉ መንግሥትና ሕዝብ ስለማይፈልግ ግንባር ላይ ካለው የለየለት ጠላት ጎን ለጎን ውስጣዊ አንድነትን ለመሸርሸር የሚሠሩ ተላላኪዎችን በሕግ የመጠየቅ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

“በዚኽ ሂደት ውስጥ መጠነኛ ስሕተቶች ተፈጥረው ያለወንጀሉ የሚያዝ ሰው ሊኖር ቢችል እንኳን በፍጥነት ተጣርቶ ይለቀቃል እንጅ ተጠያቂ አይኾንም” ሲሉም ገልጸዋል። ወንጀለኞች ግን በሕጉ መሠረት ይጠየቃሉ ነው ያሉት።

ሕዝቡም ሰላምን ሲያደፈርሱ፣ ሲዘርፉ እና የተለያየ አፍራሽ ተግባር ላይ ሲሳተፉ የተመለከታቸውን አካላት በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ ብቻ በመታገል ወደ ሕግ እንዲቀርቡ መሥራት እንደሚገባው ገልጸዋል።

በሕግ ጥላ ሥር ስለሚያዙ ሰዎች አያያዝና ሰብዓዊ ደኅንነት በተመለከተ ሲያብራሩ “ሕግን መሠረት ባደረገ መልኩ እና በተገቢው መልኩ ተይዘው ለቤተሰቦቻቸው አስፈላጊውን መረጃ ኹሉ ይሰጣል” ብለዋል። በክልሉ ስለሚደረገው የሕግ የበላይነትን የማስከበር እንቅስቃሴ ለሕዝብ ግልጽ መረጃዎች የሚሰጥ ግብረ ኀይልም ተቋቁሟል ነው ያሉት።

ይሕ ኾኖ እያለ ጠላት በተለመደው የበሬ ወለደ ትርክት ፈጥሮ በሚያሰራጨው ከፋፋይ አሉባልታ ሕዝቡ መታለልና አንድነቱን ማላላት እንደሌለበትም አስገንዝበዋል።

“በወንጀል ተጠርጥረው የሚያዙ ሰዎች ወገኖቻችን ስለኾኑ በአስፈላጊው እንክብካቤ ተይዘው ፍርድ ያገኛሉ፣ ታርመው ለሕዝባቸው ይቅርታ ከጠየቁም በሰላም ይኖራሉ” ነው ያሉት።

የወቅታዊው የጦር መሳሪያ ምዝገባን በተመለከተም “የምዝገባው ዓላማ የክልሉ መንግሥት በገባው ቃል መሠረት ሕዝቡ በጀግንነት ታግሎ ከጠላት የማረከውን መሳሪያ በሕጋዊ መልኩ አስመዝግቦ እንዲይዝ ነው” ብለዋል። አሁንም ቢኾን በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በጠላት የተወረሩ በመኾናቸውና የጠላት የጦርነት ጉሰማ ያልበረደ በመኾኑ ሕዝቡ በእጁ የያዘውን ትጥቅ አስመዝግቦ ራሱንና ወገኑን ለመጠበቅ እንዲያውለውም አሳስበዋል። የጦር መሳሪያ ምዝገባው ከሕዝብ የተሰወረ ምንም አይነት ሌላ ዓላማ እንደሌለውም አስረድተዋል።

በርካታ ሰዎች የጦር መሳሪያ እያስመዘገቡ ሲኾን በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ምዝገባው መጠናቀቅ ባለመቻሉ ተጨማሪ ቀን ተሰጥቶታል ብለዋል። ምዝገባው እስከ ረቡዕ ግንቦት 17/ 2014 ዓ.ም በኹሉም አካባቢዎች እንዲቀጥል ተወስኗል ነው ያሉት። በዚኽም መሠረት ማንኛውም ሰው በጀግንነት ከጠላት የማረከውን እና ያለውን ትጥቅ አስመዝግቦና ሕጋዊ አድርጎ የመያዝ መብቱን እንዲያረጋግጥም ጥሪ አቅርበዋል።

#አሚኮ

Leave a Reply