“የመርዓዊ ሕዝብ ወደ ጫካ እየገባ ነው”ባልደራስ፤ “ከተማችን የተለመደ እንቅስቃሴ ላይ ናት” አስተዳደሩ

“የመርዓዊ ከተማ ኗሪ በተቃውሞ ጫካ እየገባ ነው፣ በሞጣ ንፁሃን ተገድለዋል” ሲል ባልደራስ ለውነተኛ ዴሞክራሲ የሚሰኘው ድርጅት አስታወቀ። የመርዓዊ ከተማ በፍጹም ሰላም ውስጥ እንደምትገኝ አስተዳደሩ አመልክቷል። ቀደም ሲል የመረጃ ብዥታ እንደነበርና አሁን ላይ ከሕዝብ ጋር ስምምነት ላይ መደረሱ ተመልክቷል።

“የአማራ ሕዝባዊ ሃይል (ፋኖ) ሰብሳቢ በሆነው ፋኖ ዘመነ ካሤ ላይ ተኩስ ተከፍቶበታል። በምዕራብ ጎጃም ዞን፤ ሰሜን ሜጫ ወረዳ መርዓዊ አካባቢ ነው ዛሬ አርብ ግንቦት 12 ቀን ማለዳ ተኩሱ የተከፈተው” ሲልባልደራስ አመልክቷል። የግንቦት ሰባት ሃይል አባል ሆነው ኤርትራ የነበሩት አቶ ዘመነ ካሴ የየትኛው አካባቢ ፋኖ መሪ እንደሆኑ፣ መቼና እንዴት ይህን ስም እንዳገኙ ባልደራስ አላብራራም።

“የመርዓዊ ኗሪ በአሁኑ ጊዜ በቁጣ ወደ አደባባይ ወጥቷል። ከፊሉም ወደ ካጫ እየገባ ነው” በሚል ባለፈው ዓርብ መረጃ ያሰራጨው ባልደራስ ዛሬ ተጠርቶ የነበረው “ምድር አንቀጥቅጥ” የተባለ ሰልፍ ስለመካሄዱ ያለው ነገር የለም። ባልደራስ በምራቅ ጎጃም፤ ሞጣ ውጥረት እንደነበረ፣ ባዶ እጃቸውን ለተቃውሞ በወጡ ላይ ጥይት መተኮሱንና የሞቱ እንዳሉ አስታውቋል ግን ምን ያህል እንደሞቱ በቁጥርም ይሁን በስም አልለየም።

መርዓዊ ከተማ አስተዳደር ትናንት ይፋ እንዳደረገው ውጥረት ነግሶባታል፣ በታጣቂዎችና ከባድ መሳሪታ ታውካለች የተባለላት መርዓዊ ከተማ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ መሆኗን ፖሊስ አስታውቋል። የምዕራብ ጎጃም ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት እንዳለው ምዕራብ ጎጃም ዞን የመርዓዊ ከተማ አስተዳደር በተለመደው ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ እንደምትገኝ ያስታወቀው የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ጽ/ቤት ነው።

የጽ/ቤቱ ኃላፊ ዋና ኢ/ር ይንገስ ጌትነት እንደገለፁት አንዳንድ ወጣቶች በህግ ማስከበር እንቅስቃሴው ላይ የተዘባ አመለካከት በመያዛቸው ግንቦት 12/2014 ዓ.ም በከተማው ዋና አስፓልት ላይ ህገወጥ ሰልፍና አመፅ መሰል እንቅስቃሴ ተስተውሎ መንገድ ለመዝጋት ሙከራ ተደርጎ እንደነበር የተናገሩ ሲሆን የፀጥታ ሀይሉ ከባለድርሻ አካላት በቅንጅት ባደረገው ጥረት ጉዳዩ ሊከሽፍ ችሏል ብለዋል፡፡

እንደ መርዓዊ ከተማ አስተዳደር ከሕዝቡ ጋር በየደረጃው ውይይት ከተደረገ በኋላ ወደተቀናጀ የሕግ የበላይነትን የማስከበር እንቅስቃሴ ተገብቷል የሚሉት ዋና ኢ/ር ይንገስ “መንግሥት የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብር የሕዝቡ የዘወትር ጥያቄ ነበርም” ብለዋል።

See also  በአማራ ክልል "በተደራጀ የሽብር ተግባርና ባለስልጣናት ግድያ" ተሳትፈዋል በተባሉ ላይ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ተፈቀደ

በዚኽም በተለያየ ጊዜ ከመከላከያና ከልዩሃይል ፖሊስ ከእነ ትጥቃቸውና ከነደንብ ልብሳቸው ከድተው በመምጣት ማኅበረሰቡን በማወናበድ የሚዘርፉና እረፍት የሚነሱ 35 ግለሰቦች በሕግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የገለፁት ኃላፊው በተጨማሪም 11 ሽሻ ቤቶች ላይ እርምጃ መወሰዱንም ገልፀዋል፡፡

በከተማው ይስተዋል የነበረው ህገወጥ ጥይት ተኩስ የፀጥታ ሃይሉ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ቅንጅታዊ አሰራር በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን የሚገልፁት ዋና ኢ/ር ይንገስ ሰዎች በሰላም ወጥተው የሚገቡበት ሰላማዊ የመኖሪያ አካባቢ ለመፍጠር በሚደረገው የህግ ማስከበር ስራ ውጤታማ እንዲሆን ወጣቶች በሰከነ መንገድ ከፀጥታ ሃይሉ ጋር በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ውድ የገፃችን ተከታዮች ከላይ በሃላፊው የተጠቀሰው ሀሳብ የመርዓዊ ከተማ አስተዳደርን ብቻ የሚመለከት መሆኑን እየገለፅን ከከተማው ውጭ (ሰሜን ሜጫ ወረዳ) ስለሚደረጉ የህግ ማስከበር ተግባራት ከሚመለከተው አካል መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባለመሳካቱ ይቅርታ እንጠይቃለን ፡፡ #መርዓዊ ኮሙዩኒኬሽን።

የአካባቢው ነዋሪዎች አሁን ላይ እንዳስታወቁት ከተማዋ መደበኛ እንቅስቃሴ ውስጥ ናት። ሞጣና ብቸና ደውለን እንደሰማነው ምንም ነገር የለም።

Leave a Reply