“መስከረም አበራ የአማራ ክልልን ከፌደራል መንግስት ለመነጠል ገንዘብ ተከፍሏት እየሰራች ነው” ሲል ፖሊስ ገለፀ

መስከረም አበራ ሚድያዎችን በመጠቀም ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ በማድረግ፣ የአማራ ክልልን ከፌደራል መንግስት ለመነጠል ገንዘብ ተከፍሏት በመስራት እንዲሁም በፋኖ እና በፌዴራል መንግስት መካከል እምነት እንዳይኖር አድርጋለች ሲል መርማሪ ፖሊስ ለችሎት አስረዳ።

መስከረም አበራ ዛሬ ግንቦት 15 ቀን 2014 ዓ.ም. በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 2ተኛ የጊዜ ቀጠሮ በዋለው የወንጀል ችሎት ከጠበቃዎቿ ጋር ቀርባለች።

መርማሪ ፖሊስ የ14 ቀን ቀጠሮ የጠየቀ ሲሆን የመስከረም አበራ ጠበቃዎች ፖሊስ ተፈጸመ ያለው ወንጀል በመገናኛ ብዙሃን መደበኛው የጊዜ ቀጠሮ ሳይሰጥ ለዐቃቤ ሕግ ተመርቶ ክስ የሚመሰረትበት እንጂ የምርመራ ጊዜ የሚጠየቅበት ስርዓት የለም በማለት ተከራክረዋል።

በተጨማሪም ለተጨማሪ ጊዜ ያቀረባቸው ተባባሪ አባሪዎችን ለመያዝ ፣ የኤሌክትሮኒስ ማስረጃቸውን ምርመራ ለማከናወን እና ምስክሮችን ለማሰባሰብ የሚሉት ምክንያቶች ተፈፀመ ስለተባለው ወንጀል ማስረጃ እንደሌለ ያሳያል ብለዋል።
መስከረም ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብታቸውን ተጠቅመው ስርዓቱን በመሞገታቸው ለማሸማቀቅ የቀረበ እስር እንጂ ለእስር የሚዳርግ ተግባር አልፈፀሙም ያሉት ጠበቆቿ የ7 ወር አራስ በመሆናቸው የዋስትና መብታቸው ይከበር ብለዋል።
ፍርድ ቤቱ ብይን ለመስጠት ለነገ ግንቦት 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ጠዋት 3፡30 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። መስከረም አበራ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህርትነት እና በተለያዩ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በምትሰጣቸው ትንታኔዎች ትታወቃለች። መስከረም ከእነ ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ጋር ህብረት ፈጥራ እንደምትሰራ በተለያዩ ጊዜያት ሲነገር እንደነበር ይታወሳል።
@AddisZeybe (አዲስ ዘይቤ)

See also  የባልደራስ አመራሮች ላይና የተባበሩት ኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፓርቲ ላይ የተውሰነውን ውሳኔ ፍርድ ቤት አጸናው

Leave a Reply