ስማርት ኮንታክት ሌንስ

ኮንታክት ሌንስ የዓይን ብሌን የውጨኛው ክፍል ላይ የሚለጠፍ በጣም ስስ የሆነ የፕላስቲክ ቁስ ነው፡፡ ለተለያዩ የዓይን ችግሮች ከመነፅር በተጨማሪ በመፍትሔነት እያገለገለ የሚገኘው ይህ ቁስ አሁን ደግሞ ወደ ስማርትነት እየተሸጋገረ ይገኛል፡፡

እርስዎ መድረክ ላይ ንግግር ማድረግ ቢፈልጉ እና በጽሁፍ ያዘጋጁትን ንግግርዎን እያጎነበሱ ከመመልከት ይልቅ እያንዳንዱ ቃል ዓይንዎ ፊት ተንሳፎ ቢደረደር ሂደቱን ምን ያህል ቀላል ሊያደርገው እንደሚችል ያስቡት፡፡

መቀመጫውን ካሊፎርኒያ ያደረገ ሞጆ ቪዥን የተባለ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ይህን እውን ለማድረግ የስማርት ኮንታክት ሌንስ ሥራውን ወደ ምስለ-ምርት (ፕሮቶታይፕ) ደረጃ አድርሼያለሁ ማለቱን ቢ.ቢ.ሲ ዘገቧል፡፡

ቁሱ ከመደበኛ አገልግሎቱ በተጨማሪ አነስተኛ ኤል.ኢ.ዲ ማሳያ፣ የምስል ሴንሰር፣ ማይክሮፕሮሰሰር፣ ኃይል ለማስተዳደር የሚረዳ ቺፕ እና ባትሪን ይይዛል፡፡

አንቴና እና መሠረታዊ የኮምፒዩተር አቅሞችንም በተጨማሪነት በመያዙ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለመስጠት ብቁ ያደርገዋል፡፡

በዚህም የእውነተኛውን ዓለም መቼት መሠረት አድርጎ በኮምፒዩተር አማካኝነት የሚመነጭ ምናብን (Augmented Reality (AR)) ለአገልግሎቱ ጥቅም ላይ ማዋል አስችሎታል፡፡

ሰዎች የተለያዩ ስራዎችን እያከናወኑ በተመሳሳይ ሰዓት መረጃዎችን ማግኝት እንዲችሉ፣ ሯጮች በውድድር ወቅት ምን ያህል ርቀት እንደሸፈኑ እንዲሁም የጉዞ መረጃዎችን ለማግኘት እና የመሳሰሉት ከብዙ በጥቂቱ በስማርት ኮንታክት ሌንሱ ይከወናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Technology and Innovation Institute, Ethiopia 

Leave a Reply