በጭልጋና አካባቢዋ ተፈናቅለው የነበሩ የኅበረተሰብ ክፍሎችን ወደ ቀያቸው ሲመለሱ፣ በሌላ ቋንቋ ማተባቸው እተቀበረበት ምድራቸው ዳግም ሲገቡ የሚያሳየው ምስል ልብ ይነካል። በስልጣን ጥመጮችና በተገዙ ሆዳሞች ሳቢያ ተፈናቅለው ለማኝ የሆኑ ወገኖች ዳግም ለቤታቸው በቅተዋል። ይህ ግን በኢትዮጵያ ዜና አይደለም።

የስንዴ ነዶ፣ የአቡካዶ ጥላ፣ የከተማ እርሻ … የሰላምና የዳግም ወደመንደር መመለስ ዜና ዜና እንዲሆን የሚፈለገው ቀና ማሰብ ብቻ ነው። መፈናቀልን የሚያውቋት የተፈናቀሉና ከሞቀ ጎጇቸው ርቀው፣ ሌማት ከፍተው እንጀራ እያጠፉ ከሚመገቡበት አውድ ርቀው ልመና ላይ የወዱቁት ብቻ ናቸው። የስንዴ ምርት የሚያስደስታቸው ረሃብን የሚያውቁን የመጪውን ዘመን ጠኔ የተረዱ ብቻ ናቸው።

ተሰበረ፣ ወደም፣ ተቃጠለ፣ ተገደለ፣ ተበተነ፣ ተተራመሰ፣ ተፈናቀለ፣ ተሰደደ፣ ጦርነት ተከፈተ፣ ሰበር ዜና የሚሉት ጉዳዮች ብቻ ዜና የሚሆኑት የገቢ ምንጭ ስለሆኑ ነው። በተመለካችና ብዛትና በቅጥረኛነት የሚከፈላቸውን ለሚያሰሉ የልማትና የተስፋ ዜና ዜና አይደለም።

በምስሉ አንገት ለአንገት ተያይዘው ናፎቅታቸውን ሲገልጹ የሚታዩት ከአይከል ከተማ አስተዳደር ተፈናቅለው የነበሩ 11 ሺ 938 የኅብረተሰብ ክፍሎች ወደ ቀያቸው በተመለሱበት ወቅት ነው። የአይከል ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እንደሻው በምስል የተደገፈውን ዜና ይፋ ሲያደርጉ ተፈናቃዮቹ ከዚህ በፊት በአይከል ከተማ ይኖሩ እንደነበረ አስታውቀዋል።

በተፈጠረ የፀጥታ ችግር ምክንያት ከቦታቸው ተፈናቅለው በጎንደር ከተማ እንደቆዩና በተፈጠረው አንፃራዊ ሰላም ወደ መኖሪያ ቤታቸውና ቀያቸው የመመለስ ስራ እየተሰራ መሆኑን ከንቲባው አስታውቀዋል።

የማእከላዊ ጎንደር ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ይፋ ያደረገው ዜና ምስል እንደሚያስረዳው ተፈናቃዮቹ ቀያቸው ሲገቡ የሚታይባቸው ስሜት በጽሁፍ የሚገልጽ አይደለም። ስሜቱ ጥልቅ፣ ትርጉሙ ብዙ፣ አላማው አኩሪ ሲሆን በማተራመስና በትርምስ ዜና ኪሳቸውን ለሚሞሉ ሃዘን ነው። ዜናም አይደለም። የአስራ አንድ ሺህ ሰዎች ወደ መደበኛ ሕይወት መመለስ ከአንድ ሰው ጉዳይ በላይ መሆኑን ለመረዳት አለመቻል ህመም ነው።

Leave a Reply