በሳውዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 28 ሺህ ዜጎች ወደ ሃገራቸው መመለሳቸው ተገለፀ

ባላለፉት ሁለት ወራት በሳምንት ዘጠኝ ጊዜ በሚደረጉ የአውሮኘላን በረራዎች 28 ሺህ ያህል ዜጎችን መመለስ መቻሉ ተገለፀ። ለተመላሾቹ ዘጠኝ የማቆያ ማዕከላት በአዲስ አበባ ተዘጋጅተው አገለግሎት እየሰጡ እንዲገኙም ተገልጿል።

በሌሎች ሀገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ለመመለስ ዝግጅት እየተጠናቀቀ እንደሚገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገልጸዋል።

በሳውዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ በእስር ቤቶችና በማቆያ ማዕከላት ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሃገር ቤት ለመመለስ ብሄራዊ ኮሚቴ በማቋቋም መጋቢት 21 ቀን 2014ዓ.ም ነበር የመመለሱ ስራ የተጀመረው።

ዜጎችን ወደ ሃገር ቤት ለመመለስ እስካሁን የተከናወኑ ተግባራት፤ ያጋጠሙ ችግሮችና ቀጣይ ስራዎችን ብሄራዊ ፈፃሚ ኮሚቴው ውይይት አካሂዷል።

የብሄራዊ ፈፃሚ ኮሚቴው ሰብሳቢና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እንዳሉት ዜጎችን የመመለሱ ስራ ከጀመረበት እለት እስካሁን በታቀደው መሰረት ሳይቋረጥ መቀጠሉን ገልፀዋል።

ለዚህም በውጤት መገኘት በስራው እየተሳተፉ ያሉ ተቋማት ቅንጅታዊ ስራ አንዱ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል።

ከ7 እስከ 11 ወራት ውስጥ ከ100 ሺህ ዜጎችን የመመለስ እቅድ መያዙን አስታውሰው በቀሪ ጊዜም የተጠናከረ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የዜጋ ተኮር ዲኘሎማሲ የመንግስት ዋንኛ ትኩረት ሆኖ እንደሚቀጥል ገልፀው፤ በቀጣይም በታንዛኒያ፣ ሱዳን፣ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣የመንና ኦማን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ዜጎችን የመመለስ ስራ ለመጀመር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል ።

ሰዎችና ጓዞቻቸውን በተለያየ በረራዎች እንዲመጡ መደረጉ ደግሞ ተመላሾችን ወደ ቀያቸው በመሸኘቱ ሂደት ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩም በሪፖርቱ ተመላክቷል።

(ኢ ፕ ድ)

See also  በአፋር የተረጂዎች ቁጥር ጨምሯል፤ በአማራና ትግራይ በምግብ እጥረት ህይወት እያለፈ ነው

Leave a Reply