አማራ ክልል ወደ እርሻ ! 4.8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ይታረሳል

የአማራ ክልል መንግስት ለአርሶ አደሮች 136 የእርሻ ትራክተሮችን አስረክቧል።

በክልሉ በቁጥር ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚባል መልኩ የተዘጋጀው የመካናይዜሽን ርክክብ ስነ-ስርአት የክልሉን ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በባህር ዳር ከተማ እየተከናወነ ነው። ርዕሰ መስተዳደሩ ዶክተርይልቃል ከፋለ በዚህ ወቅት እንደገለጹት የክልሉ መንግስት በበርካታ ችግሮች ውስጥ ቢሆንም ግብርናውን ለማዘመንና የአርሶ አደሮችን አቅም ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ ነው። ግብርናውን ለማዘመን የሚሰራው ስራ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሃይለማሪያም ከፍያለው በበኩላቸው በክልሉ በ2014 እና 2015 ዓ.ም የምርት ዘመን ከ4 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተከናወነ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ለእርሻ ተስማሚ ከሆነው የክልሉ መሬት ውስጥ 2 ሚሊዮን ሄክታሩ በትራክተር ለመታረስ አመች መሆኑን አስረድተው ነገር ግን እስካሁን ባለው ከ 20 በመቶው ያልበለጠው ነው በትራክተር እየታረሰ ያለው ብለዋል። እስካሁን ባለውም ከ800 ያልበለጡ የእርሻ ትራክተሮች በክልሉ እንደሚገኙ አመልክተው በዚህ አመት ለዘርፋ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶት 1000 ትራክተሮችን ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የዛሬውን ጨምሮ እስካሁን ከ300 በላይ ትራክተሮች ለአርሶ አደሮች እንዲደርሱ ተደርጓል ሲሉም ተናግረዋል። ትራክተሮቹ በባለሀብቶች፣በዩኒቨርሲቲዎችና በአርሶ አደሮች እንደተገዙ የተገለጸ ሲሆን በርክክብ ስነ-ስርአቱ አርሶ አደሮችና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል ሲል ኢዜአ አስታውቋል።

አሚኮ በበኩሉ የትራክተራቸውን ቁልፍ ከክልሉ መንግሥት የተረከቡት አርሶ አደር ሙሴ ሙሳ የእስከዛሬ እድሜያቸውን በባሕላዊ ግብርና እንደገፉት መናገራቸውን አስታውቋል። ስለኾነም ከእጅ ወደ አፍ እንጂ ኑሯቸውን ማሻሻል እንዳልቻሉ ነው አርሶ አደሩ የተናገሩት። ዛሬ የትራክተር ተጠቃሚ በመሆናቸው የተደሰቱት አርሶ አደር ሙሴ መንግሥት አስፈላጊውን የቴክኒክ ድጋፍ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ ጠይቀዋል።

አርሶ አደር ደርቤ አባተ በበኩላቸው ከራሳቸው እርሻ በዘለለ በተመጣጣኝ ዋጋ ሌሎች አርሶ አደሮችንም ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። የክልሉ መንግሥት ለግብርና ዘርፉ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።

አርሶ አደር ጌታሁን ከበደ በበሬ ማረስ ውጤታማ ካለመሆኑም በላይ እንሳትንም ማንገላታት እንደኾነ ተናግረዋል። ዛሬ ክልሉ ባስረከባቸው ትራክተር ግን አቅማቸው በፈቀደው ሁሉ በማልማት እራሳቸውንና ሀገራቸውን ለመጥቀም ቁርጠኛ እንደሆኑ አስረድተዋል።

በተምነሳሳይ ዜና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የክልሉን ግብርና ለማዘመን የሚያግዙ 136 ትራክተሮችን ለአርሶ አደሮች መሰጠቱን ጠቅሶ፣ አርሶ አደሮቹ የተረከቡት የግብርና ትራክተር የአንድ ዓመት ዋስትና እንዳላቸው ከፍተኛ የሽያጭ መሀንዲስና ወረታ ኢንተርናሽናል ቢዝነስ አስተባባሪ ዘላለም ልይህ በተለይ ለአሚኮ አስረድተዋል። ትራክተሮቹ በአንድ ዓመት ውስጥ ችግር ቢያጋጥማቸው ለአርሶ አደሮቹ የነፃ ጥገና ይደረግላቸዋል ነው ያሉት።

የጥገና አገልግሎቱን ለማሳለጥ ባሕር ዳር ውስጥ የመገጣጠሚያ ማእከል እንዳላቸው ገልጸዋል። የትራክተሮቹ ቁሳቁስ መሸጫም ባሕር ዳር እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ሙያውን ያካበቱ ባለሙያዎች በአርሶ አደሩ እርሻ ድረስ በመገኘት የጥገና አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ናቸው ተብሏል። ከ12 በላይ ከፍተኛ ባለሙያዎች እንዳሏቸው ያስረዱት አቶ ዘላለም በጥገና ወቅት በአርሶ አደሮች እርሻ ላይ ለመገኘት የሚረዳቸው 6 ተሽከርካሪዎች እንዳላቸው አብራርተዋል። ትራክተሮቹ አስተማማኝና ከፍተኛ ጉልበት ያላቸው እንደሆነም አቶ ዘላለም የገለጹት።

Leave a Reply