8.5 ሚሊየን ብር ጉቦ የጠየቁ የመከላከያ ሚኒስቴር አባላትና ግብረ አበሮቻቸው ተከሰሱ

ባለሀብቶችን በመሰለል፣ በማገትና በማስፈራራት ገንዘብ በጠየቁ እንዲሁም በተቀበሉ አራት የመከላከያ ሚኒስቴር አባላትና ግብረአበሮቻቸው ላይ ስልጣንን አላግባብ በመገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ስር ክስ ተመሰረተ

የመከላከያ መኪና በመያዝ ከጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ሃብት ማስመለስ የመጣን ዐቃቤ ህጎች ነን ህገ ወጥ ዘይት߹ ስኳር እና የጦር መሳርያ ስለምትሸጡ በወንጀል ትፈለጋላችሁ በማለት 8 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በጠየቁ የመከላከያ ሚኒስቴር አባላትና ግብረ አበሮቻቸው ላይ ክስ ተመስርቷል ።

የተለያዩ የምርምራ ሂዶትችን ከፖሊስ ጋር ሲያከናውን ቆይቶ በግለሰቦች ላይ ክሱን የመሰረተው ደግሞ በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ህግ ዳይሬክቶሬት ጄነራል ነው ።

ወንጀሉን ፈጽመዋል በሚል ክስ የተመሰረተባቸው በመከላከያ ሚኒስቴር በ93ኛ እና 94ኛ እግረኛ ክፍለ ጦር አባል የሆኑት 1ኛመቶ አለቃ ሀጂ ቱሉ ߹ 2ኛኦፊሰር መንግስቱ በቀለ ߹ 3ኛ ሻምበል ካህሊ መላክ ߹ 4ኛ ሻለቃ ዱጉማ ዲምሳ እና በተለያዩ የንግድ ስራዎች ውስጥ ተሰማርተው የሚገኙት ግብረ-አበሮቻቸው ከ5ኛ-8ኛ ስማቸው በክሱ የተጠቀሰው ተከሳሾች ሹምበዛ ፍቃዱ፣ አዲስ አለሙ፣ ተስፋዬ ለሚ እና አሸናፊ ወልደ ሰማያት ናቸው፡፡

ተከሳሾች ከጳጉሜ 03/2013 ዓ.ም እስከ የካቲት 13/2014 ዓ.ም ባሉት ጊዚያት ውስጥ በቡድን በመደራጀት ባለሀብቶችን ኢላማ አድርገው ጥናት በማድረግ የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘት በማሰብ በዐቃቤ ህግ ክስ ላይ እንደተመለከተው 2ኛ ፣ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች ታርጋ የለጠፈ የመከላከያ መኪና ይዘው ወደ ግል ተበዳይ መኖርያ ቤት በመሄድ ተበዳይ በወንጀል እንደተጠረጠረ በማስመሰል በመኪና አግተው ከወሰዱት በኋላ ህገ ወጥ ዘይት߹ ስኳርና የጦር መሳርያ ትሸጣለህ እንድንለቅህ የምትፈልግ ከሆነ 5 ሚሊየን ብር ክፈል ካልከፈልክ ግን ልጆችህን ጭምር እንገላቸዋለን ብለው ካስፈራሩ በኋላ 710,000 ( ሰባት መቶ አስር ሺ ) ብር የተቀበሉ ሲሆን፤

በሌላ 2ኛ ክስ ደግሞ ሌላ ተበዳይ መኪና እያሽከረከረ እያለ 5ኛ እና 7ኛ ተከሳሽ በመከላከያ መኪና ሲከተሉት ስጋት ስለገባው ለላፍቶ ፖሊስ ጣቢያ ኣዛዥ ጉዳዩን ያስረዳ ቢሆንም ሁለቱ ተከሳሾች የፖሊስ ጣቢያ አዛዡን ”ከደህንነት ነው የመጣነው” ግለሰቡ በብዙ ወንጀሎች ይፈለጋል አለቃችንም እየመጣ ነው ካሉ በኋላ 8ኛ ተከሽ አንደ አለቃቸው ሆኖ በመምጣት ፖሊስ ጣቢያ እንደሚታሰር ገልፀው ተበዳይ እህቱን አንዲጠራት ካደረጉ በኋላ እህቱንም ጭምር በመያዝ ይሄ የሕይወት ጉዳይ ነው እህትህን እንድንለቃት የምትፈልግ ከሆነ 3 ሚሊየን ብር ክፈል ያሉት ሲሆን
በ3ኛ ክስ ቀኑ በውል ባልታወቀ በመስከረም ወር 2014 ዓ.ም ደግሞ ወ/ሮ አዜብ በርሔ የተባለች ግለሰብን 5ኛ እና 7ኛ ተከሳሽ ”ከጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ሃብት ማስመለስ ዐቃቤ ህጎች ነን” በማለት ተበዳይን ባለቤትሽ ጄነራል ነው ትግራይ በመሄድ እያዋጋ ነው ቤትሽን በተመለከተም እያጣራን ስለሆነ አጠቃላይ የቤት ካርታና ሌሎች ሰነዶችን ኮፒ አድርገሽ አምጭ ብለው ከተቀበሏት በኋላ እንድንረዳሽ ከፈለግሽ አምስት መቶ ሺ ብር ክፈይ ሲሏት የመክፈል አቅም እንደሌላት ገልፃ ህጋዊነታቸውን ስትጠይቃቸው 8ኛ ተከሳሽን አናግሪው በማለታቸው 8ኛ ተከሳሽ የመከላከያ ታርጋ የለጠፈ መኪና ይዞ በመምጣት ተበዳይን አግኝቶ “ሰዎቹ ህጋዊ ናቸው የሚሉሽን አድርጊ እኔ የመከላከያ ሚኒስቴር አባል ነኝ አሁን ሃብት ማስመለስ ስራ ላይ ነው የምሰራ ” በማለት ከሁለቱ ተበዳዮች በአጠቃላይ 405 (አራት መቶ አምስት ሺ ብር ) የተቀበሉ ሲሆን ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነትና ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ነው እንደ ወንጀል ተሳትፏቸው በዐቃቤ ህግ ክስ የተመሰረተባቸው

ከ1ኛ እስከ 6ኛ ያሉት ተከሳሾች ዛሬ ግንቦት 22/2014 ዓ.ም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው የክስ ማመልከቻው አንዲደርሳቸው ተደርጎ ክሱ በንባብ እንዲሰማ ተደርጓል ።

ችሎቱ በቁጥጥር ስር ያልዋሉትን 7ኛ እና 8ኛ ተከሳሽን ፖሊስ አፈላልጎ አንዲያቀርብ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን ተከሳሾች በተመሰረተባቸው ክስ ላይ የመጀመርያ የክስ መቃወሚያ እና ባልተያዙ ተከሳሾች ላይ የፖሊስን ምላሽ ለመጠባበቅ ለግንቦት 29/2014 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰቷል ።

ዜናው የተቅላይ አቃቤ ህግ ነው

Leave a Reply