የጥላቻ ንግግርና የሐሰት መረጃን ማሰራጨት የሚያስከትለው የወንጀል ተጠያቂነት ምን ያህል ያውቃሉ?

የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1185/2012 አንቀጽ 4 መሰረት ማንኛውም ሰው የጥላቻ ንግግርን በብሮድካስት፣ በህትመት ወይም በማህበራዊ ሚዲያዎች ወይም በሌላ ተመሳሳይ ዘዴዎች አማካኝነት በጽሑፍ፣ በምስል፣ በድምጽ፣ ወይም በቪዲዮ ማሰራጨት የተከለከለ ነው፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 5 መሰረት ማንኛውም ሰው የሐሰት መረጃን በአደባባይ ስብሰባዎች በብሮድካስት፣ በህትመት ወይም በማህበራዊ ሚዲያዎች ወይም በሌላ ተመሳሳይ ዘዴዎች አማካኝነት በጽሑፍ፣ በምስል፣ በድምጽ፣ ወይም በቪዲዮ ማሰራጨት የተከለከለ ተግባር ነው፡፡

የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭት የሚያስከትለው የወንጀል ተጠያቂነትን በተመለከተ በአዋጁ አንቀጽ 7 መሰረት:-

  1. ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ አንቀጽ 4 መሰረት የተከለከለውን የጥላቻ ንግግር ያደረገ እንደሆነ፣ እስከ ሁለት ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከብር 100 ሺ ያልበለጠ መቀጮ ይቀጣል፡፡
  2. በጥላቻ ንግግሩ ምክንያት በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት የተፈጸመ እንደሆነ፣ ቅጣቱ ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራት ይሆናል፡፡
  3. ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ አንቀጽ 5 መሰረት ክልከላ የተደረገበትን ተግባር የፈጸመ እንደሆነ፣ እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከብር 50 ሺ ባልበለጠ መቀጮ ይቀጣል፡፡
  4. የጥላቻ ንግግር ወይም የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ወንጀሉ የተፈጸመው ከ5 ሺ በላይ ተከታይ ባለው የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ከሆነ ወይም በብሮድካስት አገልገሎት ወይም በየጊዜው በሚወጣ የህትመት ውጤት ከሆነ ቅጣቱ እስከ ሶስት ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራት እና ከብር 100 ሺ ያልበለጠ ቅጣት ይሆናል፡፡
  5. ሐሰተኛ መረጃ በመሰራጨቱ ምክንያት በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት የተፈጸመ ከሆነ፣ ሁከት ወይም ግጭት የተከሰተ እንደሆነ ከሁለት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት የሚያስቀጣ ይሆናል፡፡
  6. በጥላቻ ንግግር ወይም በሐሰተኛ መረጃ ወንጀል መፈጸም ምክንያት በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት ያልተፈጸመ ወይም ያልተሞከረ ከሆነ፣ ሁከት ወይም ግጭት ያልተከሰተ እንደሆነ፣ እና ጥፋተኛውን ለማረም የተሻለ ነው ብሎ ሲያምን ፍርድ ቤቱ በእስራት ምትክ የግዴታ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራን በአማራጭ ቅጣትነት ሊወስን ይችላል፡፡

Leave a Reply