ኢትዮጵያዊቷ ሳይንቲስት

. . . በጣም አስቀያሚ፣ ጾተኛ፣ ዘረኛና ክብረ ነክ አገላለጾችን የያዘ ነው። ስለ ጥቁሮች አስጸያፊ አገላለጾች ይዟል። ከእኔ ግኝት በኋላ ኤምአይቲ ዳታሴቱን ከላይብረሪው አጥፍቷል። ጥቅም ላይ እንዳይውልም አድርጓል። ኤምአይቲ እነዚህን ማጥፋቱ ትልቅ ስኬት ይመስላል. . .

Bbc Amharic

የክፍሏ ጎበዝ ተማሪ ነበረች።

ሰኔ ላይ ሰርተፍኬት ለመቀበል ቀድመው ከሚሰለፉ መካከል ናት።

ዛሬ በዓለም ገናና ስም ካላቸው ኮምፒውተር ሳይንቲስቶች አንዷ የሆነችው አበባ ብርሃኔ (ዶ/ር)፣ ያኔ ሰርተፍኬት የምትወስደው አባቷ እሽኮኮ ብለዋት ነበር።

ውጤቷ ሁሌም ያኮራቸዋል። በየትምህርት ዘመኑ መጨረሻ እሽኮኮ ብለዋት አብረዋት ሰርተፍኬት ይቀበላሉ። ከዚያ ደስታ ከረሜላ ይገዛላታል።

“. . . ደስታ ከረሜላ ገዝቶልኝ ጠጅ ቤት ይወስደኝ ነበር። ከዚያ ለጓደኞቹ በኩራት ያሳየኛል። ይህ ደስ የሚለኝ ትውስታዬ ነው። ዛሬ የደረስኩበት ለመድረሴ አባቴ ትልቅ ሚና አለው። ፀጉሬን ሁሉ የሚሠራኝ እሱ ነበር. . .”

አባቷ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ዘጠኝ ዓመቷ ላይ ነው። በሕይወት ሳሉ ለትምህርት ፍቅር እንድታሳድር አበረታተዋታል።

“. . . ምሳሌ ልስጥሽ፣ የማትሪክ ውጤት ሲወጣ ሰው ውጤቱን፣ መታወቂያ ቁጥሩንና ሌላም የግል መረጃውን በዘፈቀደ በበይነ መረብ እየለጠፈ ነበር። ይህ የግል መረጃ ሲለቀቅ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋሞች ሀርቨስት (ይሰበስቡታል) ያደርጉታል። ከዚያም ሰዎችን ለማግለልና ለመጉዳት ይውላል። በበይነ መረብ የምንለቀው መረጃ አንዴ ከተለቀቀ በኋላ እንደማይጠፋና እየተንሳፈፈ እንደሚቆይ ማወቅ አለብን. . .”

ነዋሪነቷን በአየርላንድ፣ ደብሊን ያደረገችው አበባ፣ በቅርቡ መነጋገሪያ ያደረጋት የማሳቹሴትስ ኢንስቲቲዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ (ኤምአይቲ) 80 ሚሊዮን ምሥሎችን እንዲያጠፋ ያደረገውና የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን ዘገባ የተቆጣጠረው ጥናቷ ነው።

ለቤተሰቧ ብቸኛ ሴት ልጅ ናት።

እናቷ “ሴት ልጅ ወደ ማጀት” ይሏት ነበር። የሴትን መማር እምብዛም በማይደግፍ ቤተሰብ ውስጥ ማደግ ለትምህርት ትኩረት መስጠትን ከባድ ቢያደርገውም ትምህርት ትወድ እንደነበር ትናገራለች።

እዚህ ጋር መምህሮቿን ሳታመሰግን አታልፍም።

በተለይ የዘጠነኛ ክፍል ፊዚክስ አስተማሪዋን።

ለሳምንታት ትምህርት ለማቋረጥ ስትገደድ ወደ ትምህርት ቤት የመለሷት እሳቸው ናቸው። ከዚያ በኋላም በተደጋጋሚ ትምህርት አቋርጣ ተመልሳለች።

መንገዱ ቀላል ባይሆንም ለትምህርት ያላት ፍቅር እንዳበረታት ትናገራለች።

ባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ስትገባ ፊዚክስ አጠናች። ስትመረቅ አየርላንድ ነጻ የትምህርት ዕድል አገኘች።

ዓለም አሉኝ ከምትላቸው የኢትዮጵያ የዘር ሐረግ ያላቸው ኮምፒውተር ሳይንቲስቶች መካከል አንዷ ናት። ትምኒት ገብሩ፣ ረድኤት አበበ እና አበባ ብርሃኔ።

አበባ የኮግኒቲቭ ሳይንስ ምሁር ናት። የቋንቋ፣ የሥነ ልቦና፣ የፍልስፍና፣ የኮምፒውተር ሳይንስ፣ የአንትሮፖሎጂ (ሥነ ሰብ) እና የአርቴፍሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሠራሽ ልኅቀት) ጥምር ጥናት ነው።

See also  ለሜቻ "እችላለሁ" ሲል ለፌዴሬሽኑ ማላሹን በገሃድ ሰጠ፤ ብር አገኘ፣ 5000 በሴቶች ነሃስ

የክፍሏ ጎበዝ ተማሪ ሳለች ጠጅ ቤት እሽኮኮ ተብላ የምትወሰደው ዶ/ር አበባ ዛሬም የትምህርት ሰው ናት።

“. . . ኒዮኮሎኒያሊዝም [የቅኝ ግዛት እጅ አዙር ቅጥያ] ነው። በተዘዋዋሪም ይሁን በቀጥታ እነሱ ነገሮችን የሚያደርጉበትን ወይም የሚያስኬዱበትን መንገድ እያስተዋወቁ እና እያሰረጹ ነው ያሉት። የራሳችንን የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ለመዘርጋት ገንዘቡ የለንም። እነሱ ወደ እኛ እየመጡ ስለሆነ ማድረግ የምንችለው መቆጣጠር እና ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠሩበትን ፖሊሲ ማውጣት ነው።”

“. . . ብዙ ሕይወቴን በትምህርት ውስጥ ነኝ። አሁን የምሠራው በጣም የምወደውን ነገር ነው። ፍትሕ ማስፈን፣ ጥሩ መስሎ ከውስጡ ግን ችግር ያለውን ነገር ማጋለጥ ነው በፍቅር እንድሠራ የሚገፋኝ. . .”

በኮግኒቲቭ ሳይንስ እና አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ [ኤአይ] አማካይ ላይ ታተኩራለች። ሥራዋ አእምሮን፣ አካባቢን፣ ማኅበረሰብን፣ ባህልን፣ ታሪክን መረዳት፣ ከዚያም ፈትሾ መተቸትን ያካትታል።

ከኤአይ ቅጥያዎች አንዱ ማሽን ለርኒንግ ሲሆን፣ ሰው ሠራሽ ማሽን መረጃ (ዳታ) ተመግቦ በተሻለ ቅልጥፍናና ትክክለኛነት ክንውን እንዲፈጽም የሚያስችል ዘመነኛ ቴክኖሎጂ ነው።

አበባ ለማሽን የሚቀርበውን መረጃ ትመረምራለች። ከሥነ ምግባር አንጻርም ትተቻለች። የዶክትሬት መመረቂያ ጽሑፏን እንደ ማሳያ እንውሰድ።

80 ሚሊዮን ምሥሎችን እንዴት አሰረዘች?

የዩኒቨርስቲ ኮሊጅ ደብሊን መመረቂያ ጽሑፏን ምክረ ሐሳብ ከ80 በላይ ጋዜጠኞች ዘግበውታል።

የጥናቱ ትኩረት ለማሽን ለርኒንግ የሚመገቡ ምሥሎች (ታይኒ ኢሜጅስ) ያላቸውን ክፍተት ማሳየት ነው።

እነዚህ ምሥሎች ወደ 80 ሚሊዮን የሚጠጉ ሲሆን፣ ከምሥሎቹ ጋር ተያይዘው የሚመጡትን አገላለጾች አበባ በጥናቷ ፈትሻለች።

“. . . መረጃው ከየት ነው የሚመጣው? በእነዚህ ምሥሎች ሰዎች፣ ባህሎች፣ ቡድኖች እንዴት ነው የሚወከሉት? የሚለውን መፈተሽ፣ መተቸትና ችግሩን አንጥሮ ማውጣት ነበር የኔ ሥራ. . .”

የጥናቱን ውጤትም እንዲህ ትገልጻለች።

“. . . በጣም አስቀያሚ፣ ጾተኛ፣ ዘረኛና ክብረ ነክ አገላለጾችን የያዘ ነው። ስለ ጥቁሮች አስጸያፊ አገላለጾች ይዟል። ከእኔ ግኝት በኋላ ኤምአይቲ ዳታሴቱን ከላይብረሪው አጥፍቷል። ጥቅም ላይ እንዳይውልም አድርጓል። ኤምአይቲ እነዚህን ማጥፋቱ ትልቅ ስኬት ይመስላል. . .”

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ ጾተኛ፣ ዘረኛ ወይም ማንኛውም ዓይነት መድልዎ ካላቸው አስተሳሰቦች በመነሳት የሚፈጠር ቴክኖሎጂ ሲተገበር ኢ-ፍትሐዊ ይሆናል። 

አበባ እንደምትለው፣ ፌስቡክ፣ ጉግል፣ አማዞን፣ ኔትፍሊክስ እና ሌሎችም መተግበሪያዎች መረጃ የሚመገቡት በማሽን ለርኒንግ ነው።

መረጃው በመድልዎ የተሞላ ከሆነ ደግሞ እነዚህ መተግበሪያዎችም ፍትሐዊ አገልግሎት አይሰጡም ማለት ነው።

“ወደድንም ጠላንም እነዚህን ማምለጥ አይቻልም። ሕይወታችን ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ” ትላለች።

See also  ስለ ጨጓራ ካንሰር ይህን ያውቁ ኖሯል?

አበባ ምሳሌ የምታደርገው ጉግልን ነው። 

ጉግል ጄኤፍቲ300 የሚባል የምሥሎችን ማብራሪያ የሚያሠለጥን ዳታሴት አለው። ይህ ዳታሴት ምን እንደሆነ ግን ጉግል ይፋ አላደረገም።

“ትልልቅ የቴክኖሎጂ ተቋሞች ዳታ ሴታቸውን በቤተ ሙከራ ሸሽገዋል። ይህም አስጊ ነው። የመረጃ ግልጽነት መኖር አለበት። ዳታ ሴት ለምልከታና ለትችት ክፍት ባለመሆኑ ሙያው አደጋ ውስጥ ነው።”

ማሽን ለርኒንግ ያሰጋናል?

ባለፉት 15 ዓመታት ማሽን ለርኒንግ በጣም ትልቅ ዘርፍ ሆኗል። ለምን?

አበባ እንደምትለው፣ ለዚህ ምክንያቱ ብዙ ዳታ በቀላሉ በበይነ መረብ መገኘቱ ነው። ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋሞች ይህን መረጃ በመሰብሰብ (ዳታ ሀርቨስቲንግ) ሞዴሎች ያሠለጥናሉ።

የመረጃ ክምችት መብዛት ማሽን ለርኒንግን ኃያል እያደረገው መጥቷል።

ነገር ግን መረጃ እንዴት ይመጣል? እንዴት ይዋቀራል? ሰዎች በመረጃው እንዴት ይወከላሉ የሚለው አጠያያቂ ሆኗል።

ነባራዊ መረጃ ላይ ተመሥርቶ ለወደፊት የሚጠበቁ ክስተቶችን አስቀድሞ የሚተነብየው አሠራር ‘ፕሪዲክቲቭ ሞዴል’ ይባላል።

የሰውን ባህሪ ጨምሮ ለወደፊት በዓለም የሚከሰቱትን የሚጠቁም ቴክኖሎጂ ነው። ነገር ግን እዚህ ቴክኖሎጂ ላይ ሙሉ እምነት መጣል እንደማይቻል አበባ ታስረዳለች።

“በማሽን ለርኒንግ ምንም ያህል አስደናቂ፣ አስደማሚ ሞዴል ብንሠራም የሰውን ባህሪ መቼም ቢሆን ሙሉ በሙሉ መተንበይ እንደማይችል መገንዘብ አለብን።”

ሰዎች ማሽን ለርኒንግ፣ አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ ወይም ሌሎችም የእነዚህ ቅጥያዎች ላይ ከመጠን ያለፈ እምነት ማሳደራቸውን አበባ ትተቻለች።

“ተቺ እና ተጠራጣሪ መሆን አለብን። ሁሉም አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ ትክክለኛ ነው ብለን መገመት የለብንም።”

ነገሩን ወደ ኢትዮጵያ አውድ እንውሰደው።

ሰልፊ መለጠፍ እናቁም?

አበባ በኢትዮጵያ በዋነኛነት የሚያሰጋት የግል መረጃ አጠባበቅ ግንዛቤ አለመኖሩ ነው።

“. . . ምሳሌ ልስጥሽ፣ የማትሪክ ውጤት ሲወጣ ሰው ውጤቱን፣ መታወቂያ ቁጥሩንና ሌላም የግል መረጃውን በዘፈቀደ በበይነ መረብ እየለጠፈ ነበር። ይህ የግል መረጃ ሲለቀቅ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋሞች ሀርቨስት (ይሰበስቡታል) ያደርጉታል። ከዚያም ሰዎችን ለማግለልና ለመጉዳት ይውላል። በበይነ መረብ የምንለቀው መረጃ አንዴ ከተለቀቀ በኋላ እንደማይጠፋና እየተንሳፈፈ እንደሚቆይ ማወቅ አለብን. . .”

ሌላው ጥንቃቄ ልንወስድበት የሚገባው ነገር የራስን ምሥል (ሰልፊ) በዘፈቀደ መለጠፍ ነው።

ብዙ ኢትዮጵያዊ ምን ችግር አለው? ብሎ ሰልፊ እንዳሻው ይለጥፋል። ሆኖም ምሥሉ ወደ መረጃ ቋት (ዳታቤዝ) እንደሚገባ፣ ከዚያም ማሽን ለማሠልጠን እንደሚውል መታወቅ አለበት።

አሁን ላይ ለታክሲ፣ ለባንክ ወይም ምግብ ለማዘዝም መተግበሪያ እየተጠቀምን እንገኛለን።

የግል መረጃችንን በስፋት በበይነ መረብ ስንለቅ ይህ መረጃ ይከማችና ኋላ ላይ አገልግሎት ስናገኝ የመድልዎ ሰለባ እንድንሆን ይጋብዛል።

See also  ዝንጀሮዎች ለኒው ደልሂ የቡድን 20 ጉባዔ ስጋት ሆነዋል

“ወደድንም ጠላንም የሰዎችን ታሪክ፣ የገንዘብ ልውውጥ፣ ብሔር እና ሌላም የግል መረጃ በመጠቀም ብድር እንስጣቸው ወይስ አንስጣቸው? የሚለው እየተወሰነ ያለበት ዓለም ነው። ኢትዮጵያውያንም ወደዚያው መንገድ እየሄድን ነው።”

የሙያ አጋሮቿ ትምኒት እና ረድኤት ያሉነት ብላክ ኢን ኤአይ ተቋም፣ ጥቁር ሴቶች በዘርፉ እንዲተሳሰሩ፣ እንዲተባበሩ መንገድ ከፍቷል።
የምስሉ መግለጫ, የሙያ አጋሮቿ ትምኒት እና ረድኤት ያሉነት ብላክ ኢን ኤአይ ተቋም፣ ጥቁር ሴቶች በዘርፉ እንዲተሳሰሩ፣ እንዲተባበሩ መንገድ ከፍቷል።

እኛ እና ፌስቡክ

ፌስቡክን “በጣም ሥርዓት አልባው የቴክኖሎጂ ተቋም” ትለዋለች።

ምን ያህል የሐሰት ዜና ተሰራጨ? ኢትዮጵያስ ምን ያህል ተቃወሰች? የሚለው እምብዛም ግድ እንደማይሰጣቸው ትተቻለች።

“ፌስቡክ በገጹ በሚሰራጨው ዜና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቢቃወስ፣ ነውጥ ቢነሳም ጉዳዩ አይደለም” ስትል ታክላለች።

የኮቪድ-19 ክትባትን የተመለከተ ሐሰተኛ መረጃ ከተራገበባቸው አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ናት።

“ለምሳሌ እናቴ ከዕድሜዋ አንጻር ክትባት ካልወሰደች እንደምትጎዳ አውቃለሁ። ‘ክትባት አልወስድም’ የምትለኝ ከፌስቡክ በተገኘ የሐሰት መረጃ ምክንያት ነው። በማኅበረሰባችን ስለ ኮቪድ-19 እና ስለ ክትባቱ ለተፈጠረው የተዛባ አመለካከት ተጠያቂው ፌስቡክ ነው።”

ፌስቡክ በፖለቲካው፣ በጤናውም ዘርፍ ሐሰተኛ መረጃን ወይም ግጭት አነሳሽ ይዘትን ለመገደብ ብሎም ለማስወገድ በቂ ገንዘብና የሰው ኃይል እንዳላሰማራ ትተቻለች።

ምን ጥንቃቄ እናድርግ?

አበባ ሦስት ምክሮች ትለግሳለች።

ዲጂታል እንቅስቃሴያችን ዲጂታል አሻራ ትቶ እንደሚያልፍ እንገንዘብ። የግል መረጃችንን በበይነ መረብ አደባባይ በዘፈቀደ አንዝራ። ቴክኖሎጂ ሁሉን-ዐወቅ ነው ብለን በጭፍን አንመን።

ምናልባት ቴክኖሎጂ የምዕራባውያኑ ያህል አላጠላብን ይሆናል። ጉዟችን ግን ቢያዘግምም ወደዚያው ነው።

እንደ ማኅበረሰብ ቴክኖሎጂን በተቺ ዐይን የምንመለከት ከሆነ መዘግየቱ ጸጋ ይሆናል።

ኢትዮጵያ እንደ የትኛውም አገር ኤአይ ስለሚያሰጋት፣ ጉዳቱን መቀነስ የሚቻልበትን መርኅ ከወዲሁ ማውጣትን ባለሙያዋ ትመክራለች።

ፌስቡክ፣ ጉግል፣ ትዊተር እና ሌሎችም ተቋማት መሠረተ ልማታቸውን እስከ ገጠር ድረስ የመዘርጋት ዕቅድ አላቸው።

ተቋማቱ ማኅበረሰብ ይህን ነው መምሰል ያለበት፣ ሰዎች መገናኘት ያለባቸው በዚህ መንገድ ነው፣ ዜና መምሰል ያለበት ይህን ነው የሚሉና ሌሎችም ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ጫናዎች ማሳደር እንደሚሹ በተደጋጋሚ ይተቻሉ።

አበባም እንዲህ ትገልጸዋለች።

“. . . ኒዮኮሎኒያሊዝም [የቅኝ ግዛት እጅ አዙር ቅጥያ] ነው። በተዘዋዋሪም ይሁን በቀጥታ እነሱ ነገሮችን የሚያደርጉበትን ወይም የሚያስኬዱበትን መንገድ እያስተዋወቁ እና እያሰረጹ ነው ያሉት። የራሳችንን የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ለመዘርጋት ገንዘቡ የለንም። እነሱ ወደ እኛ እየመጡ ስለሆነ ማድረግ የምንችለው መቆጣጠር እና ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠሩበትን ፖሊሲ ማውጣት ነው።”

ከሽልማቶቿ ዋና ዋናውን ጠቀስን እንጂ ያገኘቻቸው ዕውቅናዎች እነዚህ ብቻ አይደሉም። 

ለእሷ ግን ትልቅ ዋጋ ያለው ቅጽበት የፒኤችዲ መመረቂያ ጽሑፏን አቅርባ ያጠናቀቀችበት ነው።

“. . . ገና ትልልቅ ሕልሞች አሉኝ። ግን ፒኤችዲዬን ዲፌንድ አድርጌ ከቫይቫ ስወጣ የነበረውን ቅጽበት አልረሳውም። ከ5 ዓመታት ሥራ በኋላ የደረስኩበት ስለሆነ ትልቁ ከፍታዬ ነው።”

ጽሑፏን አቅርባ ስትወጣ የተነሳው ፎቶ ትዊተር ላይ ከተለቀቀ በኋላ የእንኳን ደስ አለሽ መልዕክት ጎርፎላታል።

የሙያ አጋሮቿ ትምኒት እና ረድኤት ያሉበት ብላክ ኢን ኤአይ ተቋም፣ ጥቁር ሴቶች በዘርፉ እንዲተሳሰሩ፣ እንዲተባበሩ መንገድ ከፍቷል።

ከጥናቶቻቸው አንዱ በአፍሪካውያን የኤአይ ባለሙያዎች የሚሠሩ ምርምሮች እንዴት ተደራሽ ይሁኑ? የሚለው ነው።

ስለ ሕብረተሰብ ጤና እና ስለ መድኃኒት የሚሠሩ የአፍሪካውያን ጥናቶች ሳይታተሙ ይቀራሉ። ሲታተሙም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዕውቅና አይሰጣቸውም።

አበባ ቀጣይ ዕቅዷ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እየተቋቋመ ያለውን የኮግኒቲቭ ሳይንስ ክፍል መደገፍ እንደሆነ ትናገራለች። አንድ ሁለቴም በዩኒቨርስቲው ግብዣ ሌክቸር ሰጥታለች።

“. . . አሁን ጥናቴ በሌሎች አገሮች ተሞክሮ ላይ የተመረኮዘ ቢሆንም፣ ዞሬ ዞሬ ግቤ ወደ ማኅበረሰቤ ተመልሼ ለእኛ መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን መፈተሽና አስተዋጽኦ ማበርከት ነው. . .”

Leave a Reply