ኢትዮጵያ እየገጠሟት ካሉ ችግሮች እንድትወጣና ሀገራዊ ምክክሩ የታለመለትን ግብ እንዲያሳካ በየአካባቢው ያሉ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የጋሞ አባቶች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያነጋገራቸው የጋሞ አባቶች፤ በየአካባቢው የሚከሰቱ ግጭቶች ለማስወገድና ሰላም ለማስፈን የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቅርቡ የሚጀመረው ሀገራዊ ምክክር ውጤታማ እንዲሆንም የሀገር ሽማግሌዎችን በአግባቡ ማሳተፍ ይገባል ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሆደ-ሰፊ መሆን አለበት ያሉት ካዎ በቀለ ብዙነህ ናቸው። ሁሉም ዜጋ ከግለሰባዊ ጥቅሞች ይልቅ ሀገርን በማስቀደም ለኢትዮጵያ የሚበጁ ሥራዎችን ሊሠራ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች አለመግባባቶች በሚፈጠሩበት ወቅት ሌላ ተጨማሪ ችግሮች እንዳይፈጠሩ የሀገር ሽማግሌዎች በትኩረት ሊሠሩ ይገባል ያሉት ካዎ በቀለ፤ ወጣቱ ትውልድ የታላላቆቹን ምክርና ተግሳጽ መስማት ይኖርበታል ብለዋል።

ትውልዱ ታሪኩን በአግባቡ ማወቅና ቀደምት እናትና አባቶቻችን ለሀገራቸው ምን ሠርተው አለፉ? የሚለውን በሚገባ አውቆ አሁን ሀገራችን ለገባችበት ችግር መንስዔው ምንድነው ብሎ መመርመር እንዳለበት ጠቁመው፤ ከዚህ አንጻር የሽማግሌዎችና የምሁራን ሚና ከፍተኛ እንደሆነም አስረድተዋል።

“የቀደምት እናትና አባቶቻችን በጎ ሥራዎችን ማስቀጠልና ሀገራችንን ማሳደግ ሲገባን እዚህ ችግር ውስጥ ለምን ገባን ብለን መመርመር ይኖርብናል” ሲሉ አሳስበዋል።

ሁሉም ሰው ለሰላም ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል ያሉት ካዎ በቀለ፤ የመቻቻል፣ የመፈቃቀር፣ የመዋደድ፣ የመረዳዳትና ሌሎችም የጋራ እሴቶቻችን አጠናክረን ማስቀጠል እንደሚገባም አብራርተዋል።

አቶ ዮሃንስ ሆሌ በበኩላቸው፤ በየአካባቢው የሚፈጠሩ ግጭቶች ለማስወገድና ሰላም ለማስፈን የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን አውቀው በኃላፊነት ሊሠሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

አቶ ዮሃንስ የጋሞ አባቶችን ተሞክሮ ሲያስረዱ፤ “ግጭቶች ከመፈጠራቸው በፊት ስለግጭት አስከፊነትና ከዚህ በፊት ስለነበሩ ተሞክሮዎች በማስረዳት ኅብረተሰቡ ግጭትን እንዲያወግዝ እናስተምራለን” ብለዋል።

ግጭት ፈጣሪ የሰጠንን ሀብቶቻችን በአግባቡ እንዳንጠቀምና ሌላ የባሰ ችግር ውስጥ እንድንገባ በማድረግ ሀገራዊ እድገታችንን ያቀጭጫል ያሉት አቶ ዮሃንስ፤ በየአካባቢው ተሰሚነት ያላቸው የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በመላው ሀገሪቱ ግጭቶች እንዲጠፉና ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር ሊሰሩ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

ወጣቱ ትውልድ የሰላም አስፈላጊነትና የግጭት አውዳሚነት በመገንዘብ ለሰላም ዘብ እንዲቆምና ለሀገሩ እድገት የበኩሉን አስተዋጽዖ እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

አዲስ ዘመን

Leave a Reply