የመተማ ወረዳ ፖሊስ ሰው በማገት ወንጀል ሲፈለጉ የነበሩ ግለሠቦች በተካሄደ ኦፕሬሽን መመታታቸውን እንዲሁም ቆስለው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አሳወቀ።

በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ መቃ ቀበሌ ልዩ ስሙ ” ጎርድም ” በተባለው ተራራ በተደረገ ኦፕሬሽን ሰው በማገት ወንጀል ሲፈለጉ የነበሩ 4 ግለሰቦች መመታታቸው እና ቆስለው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።

ፖሊስ ይፋ ባደረገው መረጃ ባዜ ብርሀኑ እና ላቀው የኔሁን የተባሉ ግለሰቦች የተመቱ ሲሆን አያናው አማረ እና ወርቁ ድረስ የተባሉ ግለሰቦች ደግሞ ቆስለው በህግ ጥላ ስር መሆናቸው ተገልጿል።

ከቀናት በፊት በዚሁ በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ሰው በማገት ፣ ሰው በመግደል ሲፈለጉ የነበሩ 3 ግለሰቦች እርምጃ እንደተወሰደባቸው የወረዳው ሰላምና ደህንነት ጽ/ቤት ማስታወቁ ይታወሳል።

በሌላ በኩል ፤ በወረዳው አኩርፈው ሆነ ሸፍተው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በተደረገው የምህረት አዋጅ እድል ተጠቅመው በሰላም ገብተው ከህብረተሰቡ ጋር በሰላም እንዲኖሩ ፖሊስ ጥሪ ቀርቧል።

በሌላ ተመሳሳይ ዜና በትህነግ የግዞት ዘመን በጠገዴ ወረዳ የሚኒሻ ሃላፊ የነበረው ካሳሁን ጫካ ሸፍቶ ቢቆይም ትናንት ከጓደኛው ጋሻው መማረኩን አስፋው አብረሃ ምስል አስደግፎ በቴሌግራም ገጹ ዘግቧል። ከስር በምስሉ እንደሚታየው ወደ እስር ቤት ታጅቦ እየሄደ ሲሆን፣ ጋሻውም በተኩስ ልውውጥ ቆስሎ መያዙን አስታውሷል።

Leave a Reply