ሬድዋን ከምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ተነስተው ገዱን ተኩ

ከለውጡ በሁዋላ ኤርትራ አምባሳደር ሆነው የከረሙት ሬድዋን ሁሴን አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ተክተው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። በምትካቸው ማን እንደሚሰየም እስካሁን ይፋ አልሆነም።

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ የተለያዩ ሹመት መስጠታቸውን ተከትሎ ነው አቶ ሬዲዋን አቶ ገዱን መተካታቸው የታወቀው። ይፋ በሆነው የሹመት ዜና ይፋ ባይነገርም ሹመቱ የማያሻማ ትርጉም እንዳለው ታውቋል። አቶ ገዱ የደህንነት አማካሪ ሆነው በፋኖ ስም በሚደራጀው አደረጃጀት ውስጥ እጃቸው እንዳለበት ሲታሙ እንደነበር ይታወሳል።

በኢህአዴግ የምርጫ ዘመቻ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን አንጀት እንዳራሱ የሚነገርላቸው አቶ ሬድዋን እስካሁን በስልጣን መቆየታቸው በበርካቶች ዘንዳ ብልጽግና ከሚወቀስበት ጉዳይ አንዱ ነበር። አቶ ሬድዋን ህዝብ የሚወዳቸውን የተቃዋሚ አመራሮችንና አመለካከትን በማበሻቀጥ የሚታወቁ የቀድሞው ስረዓት ታማኝ እንድነበሩ በርካቶች ሲናገሩ ቆይተዋል። አሁን የተሰጣቸው ስልጣን ረጋ ብለው ስለ ጡርታቸው እንዲያስቡ የሚረዳቸው እንደሆነ ተገምቷል። እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ እንደ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ ዳባ ደበሌ፣ የቀድሞ ኦሮሚያ ሊቀመንበር ሙክታር አይነት ሰዎችን መሸከሙ አሁንም ድረስ ብልጽግናን የሚያስወቅስ ነው።

ዛሬ ይፋ በሆነው ሹመት መሰረት አቶ ሄኖስ ወርቁ የነዳጅና ኢነርጂ ምክትል ዋና ዳይሬክተር፣ አቶ ካሊድ አብዱራሂማን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሚኒስትር ድኤታ ማዕረግ የፕሮጀክቶች ክትትል፣ አቶ ወንደሙ ሴታ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ፣ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር ሆነው መሰየማቸው ታውቋል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለፌዴራል ዋና ኦዲተርነት መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተርነት ወይዘሮ መሰረት ዳምጤን እንዲሁም አቶ አበራ ደምሴን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ምክትል ዋና ኦዲተርነት በማድረግ ሹመቱን እንዲያጸድቅላቸው መተየቃቸው ታውቋል።

Leave a Reply