የኢዜማ ነገር !

ኢዜማ በመጪው ሰኔ ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዶ አዳዲስ የአመራር አባላት ምርጫ ያካሂዳል። ከምርጫው በፊት አንዳንድ ኢዜማ ነክ ሀሳቦች እንካችሁ :

፩. ኢዜማ በመንታ መንገድ ላይ

ጥቂት የማይባሉ የኢዜማ ደጋፊዎች ፓርቲው ከብልጽግናና ከለውጡ ሂደት አኳያ በያዛቸው አቋሞች ደስተኛ አይደሉም። ከፊሎቹ አባላቱና ደጋፊዎቹ ደግሞ ኢዜማ የለውጡ ሂደት ይረጋጋ ዘንድ የያዘውን አቋም ይቀጥልበት ዘንድ አሁንም ይፈልጋሉ። ኢዜማ ከዳን ባዮቹ ሰዎች የሽግግር ፖለቲካን ባህሪያት የማይረዱ ድህረ አምባገነን ስርአት የሚፈጠሩ የሀይል አሰላለፎችን ያልገባቸው ናቸው ብዬ አስባለሁ። ኢዜማ እንደ ሲቪክ ፖለቲካ አራማጅነቱ ብልጽግናን ከመሰሉ ለዘብተኛ ህብረብሄራዊ ድርጅቶች ጋር የመሰለፍ ግዴታ አለበት ባይ ነኝ።

ኢዜማ የመንግስት ስልጣን ላይ መጋራቱን የሚኮንኑ ሀይሎች ደግሞ በሽግግር ፖለቲካ ሀላፊነት የሚሰማቸው ፓርቲዎች sectarian politics ለማለዘብ የሚወስዷቸውን የተቀራርቦ መስራት ታክቲኮችን በቅጡ ያላሰቡበት ናቸው። ኢዜማ የህዝብ ድጋፍ ያጣው ( ካጣም) ህብረተሰባችን እገሌ መጣብህ በሚል ውዥንብር የብሄር ፖለቲካን መዳኛው አድርጎ ስላሰበ እንጂ በኢዜማ ህሳቤዎች ግድፈት አይደለም። ኢዜማ የትብብር ፖለቲካን በመከተሉ እንደ ፓርቲ ያገኘው ጠቀሜታ አሳንሰን ብናየውም ኢትዮጵያ ከፓርቲው በሳል አካሄድ ብዙ አትርፋለች። ብዙ ተስፋ የተጣለባቸው የቱኒዝያና ሱዳን ለውጦች የጨነገፉት መሀከሉን አጥብቀው የሚይዙ የኢዜማ አይነት ፓርቲዎች ባለመኖራቸው ነው።

፪. የሽግግር እና የነጻ አውጪነት ፖለቲካ

የኢትዮጵያ ፖለቲካ የቱንም ጠጋ ብለህ ብታየው የነጻ አውጪነት ፖለቲካ ነው። ይሄን አድርጌ ፣ እነዚህን የፖሊሲ አማራጮች ተጠቅሚ ኖርህን አሻሽላለሁ የሚል ፖለቲከኛ በድንጋይ ለመወገር የፈቀደ ብቻ ነው። የህዝብ ልብ ውስጥ ለመግባት ወይ ከአማራ የበላይነት ነጻ አወጣሃለሁ አልያም ከኦሮሙማ ተረኝነት እታደግሀለሁ ብለህ ስሜት ካልቀሰቀስክ ተከታይህ እምብዛም ነው። ኢዜማውያን ልባቸው ለሁለት የተከፈለውም ለዚህ ነው። ከፊል አመራሩ እንደ እስክንድር ነጋ የከተሜው ነጻ አውጪ ሆኖ ሊጀግን ይፈልጋል ጥቂቱ ደግሞ የለም ፖለቲካውን በስሌት እናዘምነው ባይ ነው።

፫. በስሜት የመኃሏን መንገድ መተው

ኢዜማ ህዝባዊ ቅቡልነቱ የቱንም ያህል ውሱን ቢሆን እጅግ ተሰሚና ተጽዕኖ ፈጣሪ ፓርቲ ነው። ለዚህ ምሳሌው በአዲስአበባ ኮንዶሚኒየምና መሬት ወረራ ላይ ፓርቲው የያዘው አቋምና የፈጠረው ተጽዕኖ ጥሩ ማሳያ ነው። እነ እስክንድር ነጋ ለወራት የጮኹለትን ጉዳይ ኢዜማ በአንዲት ጥናት ጠገብ ወረቀት ህዝብ አይን ውስጥ ገብቷል የከተማ አስተዳደሩ አካሄዱን እንዲመረምር ማስገደድ ችሎ ነበር። ኢዜማ ርዕዮተ አለሙም ቢሆን ( ሶሻል ዲሞክራሲ ) የመሀል መስመር የሚከተል የቅይጥ ኢኮኖሚና welfare state capitalism አቀንቃኝ ነው። በብሄር ለተቧደነው ፖለቲካችንም ዜግነት ተኮር ፖለቲካን ይዞ በመምጣቱና ከሁሉም ፓርቲዎች ጋር በትብብር ለመስራት መሞከር የመሀል መስመር ሀይል centrist politics የሚከተል አድርጎታል። ኢዜማ ይህንን መስመር ለቅቆ ጭብጨባና ሆታው መንገድ ሲገባ ከእርሱ በላይ በሚጮሁ ሀይሎች ተውጦ ህልውናው ያከስማል።

See also  የመቃወም አዚም!

፬. ገዥውን ፓርቲ የመውገር ፖለቲካና ኢዜማ

የመድብለ ፓርቲን ዲሞክራሲ በሚከተሉ ሀገሮች ሁሉ ስልጣን ላይ ያሉ ፓርቲዎች ዘወትር በጫና ውስጥ ናቸው። እኛ ሀገር ግን ገዥ ፓርቲዎችን እንደ ባዕዳን የመቁጠር በመቃብሩ ላይ አዲስ ስርአት የመመስረት ትግል ነው የሚካሄደው። በዚህም ሳቢያ ፖለቲካችን ይመራል ልዩነታችንም ለመጋደል ቢላ የመሳል ዝግጅትን ያካትታል። ከገዥ ፓርቲ ጋር መስራት ከሀዲነት ነው ፣ የመንግስት ደጋፊነትም እንደ ፖለቲካ ምርጫ ሳይሆን የአድርባዮች እና ከሃዲዎች ስራ ተደርጎ ይወሰዳል።

ኢዜማ እዚህ ኃላቀር የፖለቲካ ባህል ውስጥ በመወለዱ ከገዥው ፓርቲ ጋር ወንበር መጋራቱ እንደ ከሀዲነት ተቆጥሮበታል ይህንን ስሜት የሚጋሩ አባላት ደጋፊዎቹ ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። ፓርቲው ድህረ አምባገነን መንግስት ሊፈጠሩ ስለሚገባቸው በጎ ልማዶች ለህዝብም ለደጋፊዎቹም ባለማስተማሩ የኖረው የጨለምተኛ ፖለቲካዊ ዕይታችን ሰለባ ሆኗል።

ለማጠቃለል የኢዜማ ጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊዎች መጪውን ስብሰባቸውን እንዲሁ የመሪዎች መረጣ አድርገው ከሚያስቡ ይልቅ ኢትዮጵያ እየሄደችበት ያለውን የሽግግር ፖለቲካና የፓርቲውን ሚና በጥልቀት ቢመረምሩ እና ለመጪው ጊዜ የሚሆናቸውን መንገድ ከብርቱ የሀሳብ ፍጭት በኃላ ንድፍ ቢያወጡለት ጥሩ ነው። ይኼ የሚሆን አይመስለኝም። ለፓርቲውና አባላቱ ስኬት ብመኝም ውስጤ my gut feeling ፓርቲው ከጠቅላላ ጉባኤው በኃላ ለሁለት የመከፈል ዕጣ ይገጥመዋል። ዛሬ ማለዳ ለመጠቆም እንደሞከርኩት የኢዜማን የመሀከል ፖለቲካ አቶ ጃዋር መሀመድና ልደቱ አያሌው የሚፈጥሩት ጥምረት ይወርሰዋል። እኛም ከጥቂት አመታት በኃላ ኢዜማን የመሰለ ፓርቲ አልነበረም ስንል የሞተን ማድነቅ እንጀምራለን።

Via Samson michailovich

Leave a Reply