“የፌደራል ፖሊስ አባላት ነን”በማለት ወንጀል የፈፀሙ በቁጥጥር ስር ዋሉ

“የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አባላት ነን” በማለት ጦር መሣሪያና ሐሰተኛ መታወቂያ በመጠቀም ወንጀል የፈፀሙ ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ልዩ የክትትል አባላት ነን በማለት ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያና ሐሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም ተደራጅተው የዝርፊያ ወንጀል ሲፈፅሙ የተገኙ ግለሰቦች ከህዝብ በደረሰው ጥቆማ መሠረት ፖሊስ ባደረገው ጥብቅ ክትትል በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያ በመታጠቅ እና ሐሰተኛ የፖሊስ መታወቂያ በመያዝ ፖሊስ መስለው ወንጀል የሚፈፅሙ ነበሩ።

ለአብነት የሚጠቀሙባቸው ስሞች ባይሳ ገመቹ እና መርጋ ጋሩማ በሚሉና ትክክለኛ ባልሆኑ መታወቂያዎች አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው መርካቶ ይርጋ ኃይሌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የወንጀል ድርጊት ሲፈፅሙ ፖሊስ ደርሶባቸው በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እየተጣራባቸው ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል የግለሰቦቹ የወንጀል አፈፃፀም ዘዴ ህብረተሰቡ ለማደናገር በቀድሞ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሠራዊት ሬንጀር የደንብ ልብስ ለብሰው በተነሱት ፎቶግራፎች የተዘጋጀ ሐሰተኛ መታወቂያ በመጠቀምና እንዲያሳዩ ሲጠየቁ እንዳይታወቅባቸው በርቀት በማሳየትና በያዙት የጦር መሳሪያ በማስፈራራት ተጨማሪ የወንጀል ተግባር ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ፖሊስ ደርሶባቸዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ተጠርጣሪዎቹ የወንጀል ድርጊቱን የሚፈጽሙት የፌደራል ፖሊስ ልዩ ክትትል አባላት ነን በማለት በተለያዩ የንግድ ቦታዎች ተሰማርተው በነጋዴው ማህበረሰብ ላይ ጫና በመፍጠር ለዚህ እኩይ ዓላማ ማስፈፀሚያ በሚገለገሉበት ህገወጥ መታወቂያና የጦር መሣሪያ በማስፈራራት የተለያዩ ገንዘቦችንና ሞባይሎችን ሰርቀው ሲሰወሩ እንደነበር ፖሊስ ከህዝብ ባሰባሰበው መረጃ አረጋግጧል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የሚጠቀሙበት መታወቂያ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሚገለገልበት መታወቂያ ጋር በእጅጉ የሚለይ ሲሆን ይዘውት የተገኘው የጦር መሣሪያና ህገ-ወጥ ገንዘብ በተመለከተ ሙሉ መረጃ ለማግኘት ፖሊስ ምርመራውን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ይህንን ድርጊት የሚፈፅሙት በተደራጀ መልኩ መሆኑንና ግብረአበሮች እንዳላቸው አመላካች መረጃ በመገኘቱ ምርመራው ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላካልና የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፤ ከአዲስ አበባ ፖሊስ እና ከሌሎች የፀጥታና ደህንነት አካላት ጋር በመሆን ጥብቅ ህጋዊ እርምጃ እየወሰደ እንደሚቀጥል ያረጋግጣል፡፡

በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አደረጃጀት ውስጥ ልዩ የክትትል ፖሊስ የሚል ስያሜ አለመኖሩን ህብረተሰቡ እንዲያውቅና ከፀጥታ አከላት ጋር ሆኖ ከነዚህ ዓይነቱ አጭበርባሪዎች ራሱን እንዲከላከል ፖሊስ ያሳስበባል።

በመሆኑም ህዝቡ ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት ሲያጋጥመው ትክክለኛውን የፖሊስ የደንብ ልብስና መታወቂያ መሆኑን ማረጋገጥ፤ የሚያጠራጥር ሁኔታ ሲኖር በአፋጣኝ በስልክ ቁጥሮች
+251115-52-63-03፣
+251115-52-40-77፣
+251115-54-36-78 እና
+251115-54-36-81

እንዲሁም
በ987፣
991
816

ነፃ የስልክ መስመሮች በመጠቀም ጥቆማ በመስጠት ወይም በአካባቢው ለሚገኝ የፀጥታ ኃይል መረጃውን በአካል በማድረስ የተለመደ ድጋፍና ትብብሩን እንዲያደርግ ፖሊስ ጥሪውን አስተላልፏል።

(ኢ.ፕ.ድ)

Leave a Reply