በድርድር የሰጥቶ መቀበል መርህ ኢትዮጵያ ከትህነግ ምን ታገኛለች?

በድርድር የሰጥቶ መቀበል መርህ ኢትዮጵያ ከትህነግ ምን ታገኛለች? የሚለው ጥያቄ በስፋት እየተሽከርከረ ነው። ከዚያም በላይ መንግስት ስለ ድርድሩ በግልጽ ለሕዝብ የማሳውቀ ግዴታም እንዳለበት እየተጠቀሰ ነው። ለሳንቲም ለቀማና ለተራ የሌሊት ጩኸት ሳይሆን ምራቃቸውን የዋጡ ወገኖች “ንገሩን” ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።

ድርድር አለ?

አዎ ድርድር እየተደረገ ነው። ማንም መሸሸግ አይችልም። አደራዳሪው ኦባ ሳንጆ በግልጽ ተናግረዋል። መንግስትም በቃለ አቀባዩ አማካይነት ለሰላም ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል። ኦባሳንጆ “ለውጥ አለ ግን ዘገምተኛ ነው። ዛሬ ያለው ሁኔታ ከስድስት ወራት በፊት ከነበረው የተሻለ ነው” ሲሉ የመተማመን ስራ ለመስራት እየባተሉ መሆናቸውን አስታውቀዋል። በጥቅሉ ድርድር የሚባለው ነገር መኖሩ ግልጽ ነው።

ትህነግ ምን ይፈልጋል?

ሲጨመቅ ትህነግ በቀደመችው የትግራይ አካል ከአማራ ክልል የወሰዳቸውን ስፋራዎች አካቶ መያዝ፣ የሰበሰበውን ተዋጊ ባለበት ታንክና መድፍ እንዳስታጠቀ መቀጠል፣ የተቋረጡ አገልግሎቶችን ማስጀመር ማለትም ባንክ፣ መብራት፣ ስልክና ኢንተርኔት፣ ያላማቋረጥ በረራ …. አሁንም በጥቅሉ ሁሉም ነገር እንደቀድሞ እንዲሆን። ይህ ሁሉ እንግዲህ በሰጥቶ መቀበል መርህ ትህነግ “ይሰጠኝ” የሚለውና ኢትዮጵያ እንድተሰጥ እጇን የምትጠመዘዝበት ጉዳይ ነው።

ትህነግ ለኢትዮጵያ ምን ይሰጣል?

በድርድር ህግ ትህነግ ለመቀበል የሚፈልገውን ነግሮናል። በወረራ ሰፊ መሬት በያዘበት ወቅት በድንፋታ የቅድመ ሁኔታ ማስጠንቀቂያ ፣ አሁን ደግሞ በርሃብ ማስፈራሪያ ደጋግሞ ግልጽ ባደርገው የመቀበል መርህ ላይ ቆሞ በሌላኛው የመስጠት መርህ ” ምን ከእጅህ” ቢባል መልሱ ” ምንም” ነው። ምንም …. ምንም …. ምንም …..

ኦባሳንጆ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲኖር እና በድርድር ተኩስ ማቆም የሚቻልበት ደረጃ ላይ መድረስና ይፋዊ የግጭት ማቆም ውሳኔ እንዲኖር እንደሚፈልጉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ተኩስ ከቆመ በሁዋላ ትህነግ መላ ትግራይን ወታደር አድርጎና አስታጥቆ፣ “ሰብሬ ወልቃይትን እይዛለሁ እያለ፣ ወደ ሱዳን መውጪያ ፍለጋ ከግብጽና ከሱዳን ጋር አብሮ እያደባ መሆኑ እየታወቀ፣ ይህንን ተግባሩን ወልቃይትን እስካልወሰደ ድረስ እንደሚቀጥልበት እየገለጸ ነው። እውነታው ይህ ከሆነ ታዲያ ትህነግ “በድርድር ሲቀበል ምን ይሰጣል?” ለሚለው ጥያቄ መልስ አይገኝም። እናም ኢትዮጵያ የማታተርፍበትን ሩጫ እየሮጠች ነው? እንደ አገር የትግራይ ሰላም መሆን ኢትዮጵያ አንድ አካሏ ሰላም አገኘ ማለት ነው።

ከላይ እንደተባለው ትህነግ ሃሳቡ ካላሳካ በስተቀር የአማራ ክልል ሁሌም በስጋት የሚኖር ነው። መንግስት ደግሞ ሁሉንም ሕዝብ የመጠበቅ ግዴታ አለበት። በዚሁ መሰረት ከትህነግ ምኞት አንጻር ሰላም ይሰፍናል ብሎ ማሰብ የዋህነት አይሆንም?

አማራ ክልል ምን ይላል?

አማራ ክልል በተለይ የወልቃይት ሕዝብ ዳግሞ ትህነግን ወደ ቀዬው አያስገባም። ክልሉም ሆነ ህዝቡ “ወልቃይትን ማሰብ የዋህነት ነው” በሚል ግልጽ ቋንቋ ምላሽ ሰጥተዋል። እንደቀድሞ ሳይሆን ሰፊ ሃይልም ገንብተዋል። የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ሙሉ በሙሉ ታጥቆ፣ በፈረቃ በሙሉ ፈቃደኛነት መግቢያ መውጫውን እየጠበቀ ነው። መንግስትም ደርግ የሰራውን ስህተት እንደማይደግም አስታውቆ በሙሉ ሜካናይዝድ ሃይል አካባቢውን እየተበቀ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ” ወልቃይት ቤገምድር ነው” ሲሉም አትመውበታል።

መንግስት ከትህነግ ጋር ለመታረቅ ሲል ከአማራ ህዝብና በተለይም ከወልቃይት ጠገዴ ነዋሪ ጋር የመጋጨት አንዳችም ፍንጭ አላሳየም። አቶ ግደይ ዘርዓጽዮን የሚባሉት የትህነግ የቀድሞ ስራ አስፈሳሚ ሰሞኑንን ” በስልጣን ላይ እያሉ የህዝብን ጥያቄ አስተናግደው በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሳይፈቱ ማቆየታቸው የራሳቸው ችግር ነው” ሲሉ እንዳስረዱት በሃይል የተነጠቀን መሬት በሃይል ካስመለሰ ህዝብ ጋር በድርድር መልሶ መሬት የመውሰድ እብደትን አማራ ክልል አያብድም። መንግስትም አይብድም። ሕዝብም አይስማማም።

በወልቃይት ጠገዴ አማርኛ መዝፈን፣ እስክስታ መውረድ፣ የኢትዮጵያ ባንዲራ ያለበት ጥበብ መልበስ፣ አማርኛ መማር፣ በጥቅሉ አማራ መሆን ክልክል ነበር። የጎንደር ዩኒቨርስቲ ይፋ እንዳደረገው ትህነግ በወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት ሕዝብ ላይ ላለፉት አርባ ዓመታት በፈፀመው ስልታዊና የተቀናጀ የዘር ማፅዳት ወንጀል ከእያንዳንዱ ቤተሰብ 29 ከመቶ ለህልፈት፣ 26 ነጥብ 5 ከመቶ ለስደት መብቃቱንና 19ነጥብ 5 ከመቶ ደግሞ የት እንደገባ እስካሁን እንደማይታወቅ ። 12 የጅምላ መቃብር ቀጠናዎች መገኘታቸውንም አስታውቋል ይፋ አድርጓል። “ሃያ ከመቶ የወልቃይት ሕዝብ የት እንደገባ አይታውቀም” ይህ ሁሉ የህግ ፍርድ የሚጠብቅ ጉዳይ ነው ተብሏል። ሲጨመቅ የወልቃይት ጉዳይ በሃይልም ሆነ በድርድር አይታሰብም የሚል የጸና አቋም ተይዟል።

የትግራይ ሕዝብ!

በሕዝብ ደረጃ የትግራይ ሕዝብ አቋም ይህ ነው ብሎ መናገር ያስቸግራል። ነገር ግን ሕዝቡ መልካም ጎረቤት አልባ መሆኑ መልካም ስሜትን እንደማይፈጥርለት ግልጽ ነው። ከኤርትራ፣ ከአማራና ከአፋር ህዝብ ጋር ተጋጭቷል። ትህነግ የመከላከያ ሰራዊትን ሲያርድ፣ ይህንንም ተከትሎ በተነሳ ጦርነት ተጎድቷል። እንደ ሕዝብ የትግራይ ሕዝብ ያሳዝናል። የትግራይ ሕዝብ ከአካባቢው አዋሳኝ ክልል ህዝብ ጋር በመልካም ጉርብትና እንዲቀጥል የሚፈለግ አይመስልም። የመጀመሪያ ሳያንስ ዳግም ወረራ በመፈጸም በተለይ በአማራ፣ ሲቀጥል በአፋር ክልል ህዝብ ንብረት፣ ማንነት፣ ልማት፣ ሃብትና ህይወት እንዲሁም ክብር ላይ የተፈጸመው ወንጀልና ግፍ የትግራይን ህዝብ ዋጋ አስከፍሎታል።

በርካታ የህግና የሞራል ጥያቄዎች፣ የቆየ ቂም፣ የተጠራቀመ ብሶት፣ አዝሎ የኖረውን የሊሎች ክልል ነዋሪዎችን እምባ የትግራይ ህዝብ ቀደም ሲል በወጉ አልተረዳም ነበር። እንደ አሁኑ ሚዲያ ክፍት ስላልነበር ምን አልባትም መረጃ እጥረቱም አንዱ ችግር ነበር። የኦሮም እናት ልጇ ሲገደል፣ አማራ በጅምላ ተፈርጆ ግፍ ሲጋት ” በስሜ አታድርጉት” ያሉ የትግራይ ተወላጆች ጥቂት ወይም በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ። ከዚህ አንጻር ችግሩ አርግዞ የቆየ፣ መዋለጃ ጊዜው አልፎ የቀነጨረ ነው። ይህ የበደል ክምር የትህነግን መሪዎች አልፎ ሕዝቡ ላይ አርፈና አሁን ለተደረሰበት መከራ አደረሰ። የትግራይ ህዝብ ከዚህ ጣጣ እንዴት ይውጣና ነጻ ይሁን? ከድርድሩ በላይ አሳሳቢው ጉዳይ ነው።

ትግራይ ነጻ አገር

ከላይ በተዘረዘረው ምክንያትና ህዝብ በግልጽ እንደሚረዳው በትህነግ አማካይነት የተገነባው የግፍ ግንብ ድርድሩን እውን ሊያደርግ አይችልም የሚሉ እንዲበረክቱ አድርጓል። የትህነግን ሰዎች በፈጸሙት ወንጀል ለህግ እንዲቀርቡ ህዝብ ይፈልጋል። መከላከያን ያረዱ ሃይሎች በህግ እንዲቀጡ ይፈለጋል። በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት የንጹሃን ደም በትህነግ አመራሮች ላይ እየጮኸ ነው። የምርመራ ቡድኖች ሁሉንም በደለ በቻሉት መጠን ሰንደው ለህግ ለማቅረብ ዳር ላይ ናቸው። በትግራይ የተፈጸመውም በተመሳሳይ ሙሉ በሙሉም ባይሆን ተሰርቷል። ስለዚህ ድርድር ቢኖርም ከህግ ማምለጥ እንደማይቻል እየተሰማ ነው።

ይህ እውነታ እያለ “የትግራይ መንግስት ምስረታ” በሚል ትግራይን አገር ለማድረግ ከቻፍ እንደተደረሰ እየተገለጸ፣ በሌላ በኩል ወደ ቀድሞ መልክ ለመመለስ ጥያቄ እያቀረቡ ነው። ትህነግ ” በኢትዮጵያና ኤርትራ ፍርስራሽ ላይ ታላቋን ባለውደብ ትግራይ እመሰርታለሁ” በሚል ቅዠት ህዝቡን እያታለለ ዛሬ ቅርቃር ውስጥ ሊወድቅ ግድ ሆኗል። በቂ ሙያ ያላቸው እንደሚሉት ትግራይ እንኳን አገር ጥሩ ክልል የመሆን ትግሏ በራሱ ዓመታትን ይፈጃል። ስለዚህ ቅዠቱን ትተው ከሁሉም ወገናቸው ጋር ያለውን የአገራቸውን ሃብት ተቋድሰው እንዲኖሩ ቢሰሩ እንደሚሻል ይመክራሉ። ቅዠት የሚያስከትለውን ጣጣ በተግባር ያዩ ወደ ልቦናቸው ሊመለሱ እንደሚገባም ይናገራሉ። እናም አገር እንሆናለን የሚለው ትርክት ለጊዜው አይሰራም።

ምን ይሁን

መንግስት ከላይ ያሉትንና ህዝብ የሚያውቃቸውን የትህነግን ታሪክ ተሸክሞ ሲደራደር በተከመረው የግፍ ኩያሳ ላይ እንዳይቆም ሊጠንቀቅ ይገባል። ወንጀለኞች ለህግ የማይቅርቡበት ፍትህ ዳግም ችግር ያመጣልና ለህግ የበላይነት ይትጋ። ታንክና መድፍ አላወርድም ካለ ሃይል ጋር የሚደረግ ስምምነት ከህዝብም ከታሪክም እንዳያጣላ ጥንቃቄ በመውሰድ ስንዴ ምርት ላይ ትኩረት ማድረግና የድርድር አቋምን፣ እስከ ሃይል አማራጭ ይበልጥ ማጎልበት የጊዜው ብልሃት ነው።

ምንም እንኳን ጦርነት እንዲካሄድ ፍላጎት ባይኖረም፣ ትህነግ አሁን ባለበት ደረጃ መቀጠል ስለማይችል አንድ ነገር መፈንዳቱ አይቀርምና ወገብ ማጥበቅ ግድ ነው። ለዚህም ዕቅዱ አንድ ፊት ድርድር እያለ በሌላ ጎን በፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ላይ ነው። ሃይል ሎእመበታተን የጀመረውን ቅሰቀሳ መልኩን እየቀያየረ ተያይዞታል። ማታ ማታ እየጮሁ አንድነትን፣ ህብረትን፣ አገራዊ ትሥስርን ለማላላት በ”ጋዜጠኛነት” ስም የሚጮሁትን ህዝብ ማንጠር ሊጀምር ግድ ነው። በሳንቲም ለቀማ የተሰማሩ፣ ኪሳቸውን ለማሳበጥ ለሚተጉ፣ በልመና መሰበሰቡት ሳንቲም እየተዋቡ ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር ቢች ዳር ፎቶ እየተነሱ ለሚለጥፉ፣ በልመና ሳንቲም እየተቀናጡ እነሱ በሚረጩት መርዝ ለሚያልቀው ህዝብ ፎቷቸው እየለጠፉ ለሚያላግጡ፣ በአሜሪካና አውሮፓ ሃብት እያከማቹ ለብር ሲሉ የህዝብን ቤትና ንብረት እንዲነድ ለሚያራግቡ ጆሮ ዳባ ማለት አንዱና ዋናው ትህነግን የመዳከሚያ መንገድ ነው።

በድርድሩ ኢትዮጵያ አሁን ላይ የምታገኘው አንድም ነገር የለም። ብቸኛው የድርድሩ ውጤት ሰላምና ተኩስ አቁም ቢሆንም ይህ የሚሆን አይመስልም። ስለዚህ “No war No peac” በሚለው የራሱ የትህነግ መርህ ለማንናውም ጥቃት ዝግጁ ሆኖ ፊትን ወደ ልማት ማዞር የመጨረሻው አማራጭ ይሆናል። ስንዴ ማምረት፣ ዳቦ መገመጥ። ቤንዚኑን ቶሎ ማስጀመር … ነዳጅና ስንዴ ካለ ጡንቻ ፈረጠመ ማለት ነውና

ምንም ባይሆንስ?

ምንም ጠብ እንደማይል ግልጽና ግልጽ ነው። ከትህነግ ባህሪ አንጻር የሰላም ድርድር አይታሰብም። አስልተው የሚፈልጉትን እሳት ለመለኮስ እየሰሩ ነው። በግል እየታዬ የሚሆነው ነገር ” ምንም አይሆንም” የሚለው ባዶ የሰላም ተስፋ ነው። ታዲያ ለባዶ የሰላም ተስፋ መንግስት ለምን ይሮጣል? ኦባሳንጆ እንዳሉት ” አዝጋሚውና በረዥም ጊዜ የሚመጣ መተማመን፣ እንዲሁም የተኩስ አቁም ይፋዊ ፊርም?” ለሁሉም የምደመድመው የሚሆነው ” ምንም አይሆንም” የሚለው ብቻ ነው!!

በሰለሞን ቦጋለ የኔነህ – ግንፍሌ ( ይህ ጹህፍ የጸሃፊው እምነት ብቻ ነው)

Get new recipes delivered to your inbox.

Leave a Reply