በትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በጥብቅ ዲሲፕሊን እንዲማሩ ለማስቻል የቁጥጥር አሰራር ማሻሻያ ማድረጉን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። ልጆች በእድገታቸው ከወላጆቻቸውና ከማኅበረሰቡ የሚያገኙት መሰረታዊ የሕይወት ክህሎት እንዳለ ሆኖ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ትልቅ መሰረቶች ናቸው።

በመሆኑም ትምህርት ቤቶች የጥሩ ትውልድ መገንቢያ ማዕከላት እንዲሆኑ ተማሪዎች በዲሲፕሊን መመራታቸው ግድ ይላል። ለዚህም ሲባል በትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በጥብቅ ዲሲፕሊን እንዲማሩ ለማስቻል የቁጥጥር አሰራር ማሻሻያ ማድረጉን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ፤ አሁን ላይ በተለይም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በተማሪዎች ላይ ከፍተኛ የስነ- ምግባር መጓደል እየተስተዋለ መሆኑን ገልጸዋል።

በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች የቡድን ጸብ፣ ከመምህራን ጋር ግጭት መፍጠርና ዩኒፎርም እንደለበሱ በአልባሌ ሥፍራዎች መገኘት እየተባባሰ መጥቷል ብለዋል።

በትምህርት ቤት ውስጥ ተማሪዎች የእጅ ስልክ ይዘው መግባትና የተለያዩ መልዕክቶችን በመለዋወጥ የሁከትና ሌሎች ጥፋቶችን ሲፈጽሙ እየተስተዋለ መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል።

በመሆኑም በትምህርት ቤቶች እነዚህንና ሌሎችንም ያልተገቡ ድርጊቶች በመቆጣጠር ተማሪዎች በጥብቅ ዲሲፕሊን እንዲማሩ ለማስቻል የቁጥጥር ማሻሻያ ማድረጉን ገልጸዋል።

ለዚህም ወላጆች፣ መምህራን፣ አጠቃላይ የትምህርት ቤት ማኅበረሰቡና ተማሪዎች የዲሲፕሊን መከበር ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ከትምህርት አሰጣጥ ሂደቱ ጎን ለጎን የስነ-ልቦና ማማከር አገልግሎት በመስጠት ተማሪዎች ስለ ትምህርት ያላቸው ግንዛቤ እንዲዳብር ይደረጋል ነው ያሉት።

የስነ-ልቦና ማማከር አገልግሎት ለመስጠት በየትምህርት ቤቱ የተቋቋሙ ማዕከላትና ሙያተኞች መኖራቸውን ገልጸው፤ ይህንንም ለማጠናከር ከስነ-ልቦና ሙያተኞች ማህበር ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ሃላፊውን ጠቅሶ ኢዜአ አስታውቋል።

Leave a Reply