በጥቅሉ ከመርዙ ባህር ባለቤት የተጨለፈላችሁን ክፉ ተግባር የምታስፈጽሙ ተቀጣሪ ነብሰ ገዳዮች፣ በክፍያ ዘር ነጥላችሁ የከፋያችሁን ዓላማ ለማሳካት ንጽሃንን የምትገድሉ ሁሉ ኦሮሞን አትወክሉም። እኔን የዚህ ጽሁፍ አቅራቢን አትወክሉም። በስሜ ነጹናንን መጨፍጨፍ አቁሙ። ዛሬ ላይ ኦሮሞ ንጽሃንን እየጨፈጨፈ የሚያስፈጽመው አንዳችም ምድራዊ የፖለቲካ አጀንዳ የለውም።

ሕዝብ የሚያምንበት ጥያቄ ካላ መታገል መብት ነው። በህዝብ ፍላጎት መሰረት ለመታገል ድርጅትና አታጋይ አመራሮች ያስፈልጋሉ። ይህ በየትኛውም አግባብ ልክ ነው። በሕዝብ ፍላጎት ላይ ያልተመሰረተ ነገር ግን በአንድ ህዝብ ስም የሚደረግ ትግል ልክ አይሆንም። በአንድ ሕዝብ ስም ራስን በመሰየም ንጹሃንን በመጨፍጨፍ የሚካሄድ ትግል ደግሞ የሚወገዝና ጸረ ሕዝብነት ነው።

ይህ ጥቅል አሳቡ ሲሆን በቅርቡ በይፋ፣ ቀደም ሲል በህቡዕ ከትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ትህነግ ጋር በገሃድ የዓላማ አንድነትና የጋራ ግንባር የፈጠረው የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር ሰራዊት ፈጸመው የተባለውና ከ260 በላይ ንጹሃን ያለቁበት አስጨናቂ ሃዘን የተከናወነው በኦሮሞ ህዝብ ስም ነውና ኦሮሞ የሆነ በሙሉ ድርጊቱን በያለበት ሊቃወም ይገባል።

ምንም ይሁን ምን፣ ማናቸውም የፖለቲካ ፍላጎቶች ይኑር፣ ሰላማዊ ሰዎችን፣ በተለይም አዝውንቶችን፣ አረጋዊያንን፣ ህጻናትንና ሴቶችን በጅምላ በማንነት መርጦ መጨፍጨፍ በምንም መስፈርት ተቀባይነት የለውም። እንዲህ ያለ አጥንት ዘልቆ የሚገባ ሃዘን የተፈጸመ በኦሮሞ ስም በሚንቀሳቀስ ድርጅት ስም ነውና ” በስሜ አትግደል” በሚል በገሃድ ኦሮሞ የተባለ ሁሉ ሊያወግዝ ይገባል። ከማውገዝም አልፎ ሊታገላቸው ግድ ይላል።

ናዚ በጅምላ በሚጨፈጭፍበት ወቅት ” በስሜ አትግደል” ያሉ የጀርመን ዜጎች ነበሩ። እነዚ ዜጎች የናዚን ጭፍጨፋ ደፍረው መኮነናቸው ዛሬ ላይ ከናዚ እርኩሰት ጀርባ በበጎ የሚነሱ የዘመኑ ወርቅ ተምሳሌቶች መሆን ችለዋል።

በታሪክም ሆነ በግብር የሚታውቀው የኦሮሞ ህዝብ ከጥቂቶች እጅግ ጥቂቶች በስተቀር በአዛውንቶች፣ በህጻናት፣ በአዋቂዎችና በአቅመ ደካሞች ላይ በሚፈጸም የጅምላ ግድያ አይደሰትም። ድርጊቱንም በምንም መስፈርት አያደንቅም። ይህ ብቻ ግን በቂ አይደለም። ከሞት የተረፉ ንጹሃን በፍርሃት ቆፈን፣ በድንጋጤ ምጥ ውስጥ ሆነው ራሱን ” የኦነግ ሰራዊት” የሚለው ሃይል ባልደረቦቻቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውን፣ ጎረቤቶቻቸውን እንደጨረሰ በግልጽ ተናግረዋል። አስከሬን የለቀሙና የቀበሩ፣ ለቅመው ያልጨረሱ በግልጽ መስክረዋልና ድርጊቱን ማን ፈጸመው የሚል ብዥታ የለም። ምስክርነቱ የተሰጠው መንግስትን በሚጠሉ የውጭና የአገር ውስጥ ገለልተኛ ነን በሚሉ ሚዲያዎች ነውና ጨፍጭፎ በመግለጫ ጋጋታና በድጋፍ ሰጪ ሚዲያዎቻቸው አማካይነት ማንም ላይ ማላከከ አይቻልም። ከሰላቦቹ በላይ በቂና ታማኝ ምስክር የለም።

በአማራ ስም የተደውራጀን ነን፣ አማራን በአክቲቪዝም እንታደጋለን የሚሉ እፉኝቶችም በየቀኑ በሚዘሩት መርዝ በሰላም የሚኖረውን አማራ በያለበት ጥርስ እንዲነከስበት እያደረጋችሁ ነውና ከጅምላ ፍረጃ፣ ከጥላቻ ወሬና ከማይሆን ተራ ቀረርቶ መራቅ ይገባችኋል። ጉዳዩ ንግድ ነውና ራስን ለማረቅ ቢያቸግርም የዚህ አስተያየት አቅራቢ በንጹሃን ደም ይማጸናችኋል።

በተላላኪነት አማራውን ከኦሮሞ ጋር በማናከስ፣ ታቅደው በመናበብ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ስር በምረመጥመጥ ቤንዚን የምትረጩ ሆድ አማላኪዎች እየበላችሁ ያለው የአዛውንትን፣ የህጻናትን፣ የአረጋዊያን ስጋና ደም ነውና በየትኛውም ዘመን ከፍርድ እንደማታመልጡ ልታውቁት ይገባል። በዚሁ ነብስን የመማገድ የተላላኪነት ተግባራችሁ ልጆቻቸሁን የምታስጌጡት በተጨፈጨፉ ወገኖች የተሰራ ሸማ ነው። ልጆቻቸሁ እየበሉ የሚያብረቀርቁት የዚህኑ ደም ቡኬት ምግብ ነው። ሚስቶቻቸሁ ተኳኩለው የሚወጡት በጨቅላዎች ደም የተለውሰ ማስዋቢያ እንደሆነ እወቁት። ከቤተሰቦቻችሁ ጋር ፎቶ እየተነሳቹህ የምትለጥፉት፣ ሰብታችሁ የምትታዩት በግፍና በደም በተጨማለቀ ግብራችሁ በምትለቅሙት ሳንቲም ነውና እናንተ ብቻ ሳትሆኑ ልጆቻችሁ፣ ሚስቶቻቸሁ ዋጋ ይኖርባቸዋል።

ኦሮሞ የሆኑ ሁሉ ” በስሜ አትጭፍጭፍ” በማለት በገሃድ በማቸው የተደራጁትን መቃወም አለበት ስል፣ የማይቃወሙ በጭፍጨፋው ተባባሪ መሆናቸውን እንዲያውቁት በማሳሰብ ነው። በተመሳሳይ በአማራ ተቆርቋሪነት ካባ አማራን የምታስጨርሱ ከነ ሙሉ ቤተሰቦቻችሁ ከፍርድ እንደማታመልጡ ማስታውስና ማሳሰብ እወዳለሁ።

በጥቅሉ ከመርዝ ባህር የተጨለፈላችሁን ክፉ ተግባር የምታስፈጽሙ ተቀጣሪ ነብሰ ገዳዮች፣ በክፍያ ዘር ነጥላችሁ የከፋያችሁን ዓላማ ለማሳካት ንጽሃንን የምትገድሉ ሁሉ ኦሮሞን አትወክሉም። እኔን የዚህ ጽሁፍ አቅራቢን አትወክሉም። በስሜ ነጹናንን መጨፍጨፍ አቁሙ። ዛሬ ላይ ኦሮሞ ንጽሃንን እየጨፈጨፈ የሚያስፈጽመው አንዳችም ምድራዊ የፖለቲካ አጀንዳ የለውም።

እናንተ በሁለት ቢላዋ የምትበሉትም ብትሆኑ እኔን በግል፣ ኦሮሞን በጋራ የምታሰድቡ ተላላኪዎች ወደ ቀልባችሁ ተመለሱ። ኦሮሞን ከአማራ ጋር ለማባለት ንጹሃን እንዲታረዱ በመግስት መቀመጫ ላይ ሆናችሁ የምታሴሩ የቀን ጉዳይ ካልሆነ አታመልጡምና ይባቃችሁ።

ነብስ ይማር!! ነብስ ይማር ከማለትና ሃዘን የገባውን ህዝብ ከማጽናናት በዘለለ አሁንም “በሰበር ዜና” ስም የጥፋት አታሞ የምትመቱ ሳንቲም ለቃሚ ሚዲያዎች ከደም ንግድ ውጡ። ዛሬ ያለው ፈተና ከርስን በመቆለፍ፣ ስከን ብሎ በማለም፣ አርቆ በማስተዋል የሚታለፍ እንጂ አራጆቹ ባሰቡት መንገድ መንጎድ ተጨማሪ ኪሳራ ከማስከተሉ ውጭ አንድም ፋይዳ አይኖረውም። አብዛኞች የአንጎል ጨዋነት ችግር ያለባቸው መሆናቸው ቭግሩን የሚያባብሰው ቢሆንም ሆን ብለው በደም የሚነግዱትን ህዝብ ሊታገላቸው ይገባል።

ገመቹ ሂርጳ ሃያ ሁለት ማዞሪያ

Leave a Reply