ለግፍ ሰለባዎችን ፋይዳ ቢስ ባዶ ተውኔት

ይህን አጭር ጽሁፍ ያዘጋጀሁት አቶ ገመቹ ሂርጳ በዚህ ድረገጽ የጻፉትን ሃሳብ ተንተርሼ ነው። ዋናው ዓላማዬ ግለሰቦችን መተቸት ሳይሆን ለተጎዱት ወገኖች የሚተቅመውን ጉዳይ ቅድሜያ ሰጥቶ በብልጠት ማከናወን የግባል ከሚል እምነት ነው። በግል ከፌደራል ይልቅ የኦሮሚያ ክልል ሊጠኡእቅ ይገባል የሚል እምነትና ማብራሪያ አለኝ።

በማንነታቸው ተለይተው የተጨፈጨፉት ወገኖች ጉዳይ እረፍት የሚነሳ ሃዘን ነው። በልቡና ውስጥ ረመጥ ሆኖ የሚቆይ ህመም ነው። ሃዘኑ “ሰው ነኝ” ለሚል ሁሉ የሚያንገበግብ፣ ነብስን የሚተናነቅ የጨለማ ተምሳሌት ነው። ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ያሰቡ፣ ያደራጁ፣ ያመቻቹና ያስፈጸሙ ሁሉም ታሪካዊ ውርደትን ለብሰዋል። ይህን ታሪካዊ የውርደት ማቅ ካባ ዝም ብሎ አውልቆ መጣል አይቻልም። ታሪክ ይህን ግፍ በሚያስቀምጠው አካል ላይ አስቀምጦታል። ዛሬ ብቻ ሳይሆን ተደጋግሞ የተፈጸመ ነውና ይህን ውርደት ደራባችሁ የተሸከማችሁ በአንድ የታሪክ ወቅት ታወራርዱታላችሁ። በዚህ ግፍ ለመቆመር የምትራወጡም በተመሳሳይ ወራዶች ናችሁ።

ኦሮሚያ በተለይም የተወሰኑ አካባቢዎች ላይ በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈጸመው፣ ሲፈጸም የቆየው፣ ወደፊትም ሊፈጸም እንደሚችል የሚገመተው ግፍ የሚፈጸመው በኦሮሞን ነጻ ማውጣት ስም በተደራጁና በገሃድ ከትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ጋር በህብረት በሚሰራው ኦነግ ነው። በጃልመሮ መሪነት የሚንቀሳቀሰውና ትህነግ ዕቅድና ብር የሚሰፍርለት ቡድን ነው። ይህ ቅጥረኛ ቡድን ኦሮሞን በጥቅል ሊወክል እንደማይችል በዚሁ ገጽ ላይ የተጻፈውን ካነበብኩ በሁዋላ ስሜቴን ስገልጽ፣ በሃዘኑ ውስጥ የማይሆን ትዕይንት የሚተውኑትንም ትንሽ ጎሸም ለማድረግ ሃሳብ መስጠት ወደድኩ።

እውነታ አንድ – ትህነግና የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር ሰራዊት ነኝ የሚለው ነፍጥ ያነገበ ድርጅት ስምምነት መፍተራቸውና ተስማምተው መንግስት ለመገልበጥ፣ አማራና ኦሮሚያ ክልልን ለማፍረስ እየሰሩ መሆናቸውን በገሃድ አስታውቀዋል። ትህነግ በሚፈጽመው ወንጀል ውስጥ ኦነግ አለ። ኦነግ ሸኔ በተላላኪነት በሚፈጽመው ወንጀል ውስጥ ትህነግ አመራር ሰጪና ዕቅድ ነዳፊ፣ እንዲሁም በሰፈራ ኦሮሚያ ያሉ አባሎቹ በቀጥታ ተሳታፊ ናቸው። ጥቁር ኢንጪኒ ድረስ ኦሮሚኛ ተናጋሪ ትህነጎች እንዳሉ እኔ ምስክር ነኝ።

በግል እንደ አንድ ኦሮሞ በርካታ መረጃዎችና በግል የማውቃቸው ሚስጢሮች አሉኝ። ቀደም ባሉት ጊዜያት ኦነግ በሚያራምደው ፖለቲካ አምን ነበር። እስር ቤቶች ሁሉ መግባቢያ ቋንቋቸው በሆነበት ዘመን ከአንዴም ሁለቴ ታስሪያለሁ ተግርፌያለሁ። ዛሬ ላይ አቶ ገመቹ ሂርጳ እንዳሉት ኦሮሞን መሳሪያ አስጨብጦ ጫካ የሚያስገባ ምድራዊ ምክንያት፣ ንጽሃንን በመጨፍጨፍ የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ አለ ብዬ ቅንጣት አላምንም። ካሁን በሁዋላም ቢሆን አይታሰብም።

በዚህ መነሻ የቀደሙትን አስተያየት ሙሉ በሙሉ ስለምጋራ ከላይ በሊንክ ስላሰፈርኩ አልደግመውም። ግን ቃል በቃል ” በስሜ አትግደሉ” ስል ድምጼን በግፍ ለተጨፈጨፉ ሁሉ አሰማለሁ። በማያውቁት ምክንያት በጥይት ለሚረሸኑ ንጽሃን እናቶች፣ አባቶች፣ ሕጻናት … “በቃ” እንድንል ለመላው ኦሮሞ ቤተሰቦቼና ህዝብ ጥሪ አቀርባለሁ።

ከዚህ በመቀጠል በህግ በማይፈቀድ ደረጃ ሆን ተብሎ የሚዲያና የህዝብ ቀልብ ለመሳብ፣ ለጉዳቱ ሰለባዎች የማይፈይድ ተውኔት መተወኑን አግባብ እንዳልሆነ ለመጠቆም እወዳለሁ።

አጀንዳ ካለ በአማካሪ ኮሚቴ በኩል መጀመሪያ መነጋገር የህግ አግባብ እንደሆነ የሚያውቁት ዶክተር ጫኔ ሊፈጥሩ የፈለጉት አተካራ ጉንጭ አልፋ፣ ራሳቸው አባል የሆኑበት የአማካሪ ኮሚቴው ህግ የማይፈቅድለት፣ ተራ የዩቲዩብ ቁርስና ቀለብ ከመሆን፣ በደመነፍስ የተባለውን ከሚያሰራጨው ማህበራዊ ሚዲያ አክተርነት የዘለለ ቁብ የለውም።

ስብሰባ ረግጦ መውጣት አንድ አቋምን ማስታወቂያ አግባብ ቢሆንም በዚህ ደረጃ ህግ በመጣስ አክተር ለመሆን መሞከርና አቶ ክርስቲያን የሚባሉት ተጣድፈው ” ይህ ታሪክ ሲዘክረው የሚኖር ጀብድ ነው” ሲሉ ከጀርባው ያለውን እሳቤ እንደመሰከሩት አይነት ተራ ተውኔት ለማራም ሆነ ለተጎጂዎች አይጠቅማቸውም።

ይህን ስል በህግ አግባን በዘር ቅድሚያ ተወስዶ ሳይሆን በሃላፊነትና በሰውነት መስፈርት ፓርላማው ይህን በወንጀል የታጨቀ ጭፍጨፋ አቋም ይዞ ሊያወግዘው አይገባም፣ ቅድሚያ ሊሰጠው አይገደድም ለማለት አልደፍርም። ብደፍርም እኔም ከነብሰ ገዳዮቹ እንደ አንዱ እሆናለሁ። እናም ፓርላማው ” አሸባሪ” ከማለት በዘለለ ማድረግ የሚገባውን ሁሉ ሊያደርግ ህዝባዊ አደራው ያስገድደዋል። የግድ ጎጃም መወለድ አይስፈልግምና።

ለትዝብት ሂደቱ ይህ ነበር። ከዚህ ሂደት በሁዋላ ነው አምስቱ የአብን ተወካዮች ፎቶ ተነስተው “አንግሱን፣ ሼር አድርጉት” ሲሉ ያሰራጩት። በነጋርችን ላይ አብን ላወጣው በሳል መግለጫ ክብር እንዳለኝ፣ አጋብብብነት ያላቸው ጥያቄዎች መነሳታቸውን በግሌ ልመስክር እወዳለሁ።

በፓርላማ ደረጃም ሆነ በግል ይህ ተደራራቢ አማራን የለየ ጥፋት መቋጫው ምን ይሁን? መፍትሄውስ ምንድን ነው? መቆሚያውስ ምን ሊሆን ይችላል? የሚሉትን ጉዳዮች ከተራ ተውኔት በመራቅ አግባብ ካላቸው ጋር ሁሉ በመምከር ማፈላለጉ በህይወት ለተረፉት የአማራ ልጆች ይበጃል ባይ ነኝ። አይን እያፈጠጡ ማቅራራት የግል ቲፎዞና የጅምላ ውዳሴ ከማጋበስ የዘለለ ጥቅም እንደሌለው አገር እናናጋለን ያሉ ጀብደኞች መጨረሻ ብዙ አስተምሮናልና እነ ክርስቲያንም ከዛ ቢማሩ የተሻለ ይሆናል። ከስር አፈ ጉቤው ታገሰ ጫፎና ዶክተር ጫኔ የተቀያየሩትን ቃላት ለግንዛቤ ከ@tikvahethiopia ተውሼ አትሜዋለሁ።

ታከለ አለማየሁ ቃሊቲ – ዝግጅት ክፍሉ ይህ ጽሁፍ የተላከው አቶ ገመቹ ሂርጳ በጻፉት ጽሁፍ ላይ ተንተርሶ ነው”” ለዚህ የግል አስተያየት ምላሽ ላላችሁ መድረኩ ክፍት መሆኑንን ለመግለጽ እንወዳለን።

የህ/ተ/ም/ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፦

” … በዛሬው ዕለት የተያዙ አጀንዳዎች አንደኛ የምክር ቤቱ አንደኛ ዓመት የስራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለጉባኤ መርምሮ ማፅደቅ ፤ 2ኛ የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች የ2013 በጀት ዓመት የሂሳብ፣ ፋይናንስ እና ህጋዊነት ኦዲት እና የክንዋኔ ኦዲት ሪፖርት ማዳመጥ ናቸው ፤ …የሚቀርቡ ማስተካከያዎች እና እርማቶች ካሉ “

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔን ” እ… “

አቶ ታገሰ ጫፎ ፤ ” ቃለ ጉባኤ ላይ ነው ? “

ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ፤ ” ቃለ ጉባኤው ላይ ሳይሆን “

አቶ ታገሰ ጫፎ ፤ ” አይቻልም “

ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ፤ ” አጀንዳው ላይ ቀዳሚ አጀንዳ እንዲያዝልን ለመጠየቅ ነው “

አቶ ታገሰ ጫፎ ፤ ” አይቻልም ፤ ባለተያዘ አጀንዳ አንወያይም። “

ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ፤ ” የተከበሩ አፈጉባኤ …አንድ ደቂቃ እድል እንዲሰጠኝ ጥያቄ ለማቅረብ “

አቶ ታገሰ ጫፎ ፤ ” ስነስርዓት ፤ ድምፅ ማሰማት አይቻልም ስነስርዓት “

ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ፤ ” ቀዳሚ አጀንዳ እንዲያዝልን ጥያቄ ለማቅረብ ነው “

አቶ ታገሰ ጫፎ፤ ” ማይክራፎኑን ይዝጉት “

ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፤ ” ቀዳሚ አጀንዳ አለን የአብን ተወካዮች እሱ እድል ይሰጠን “

አቶ ታገሰ ጫፎ፤ ” ማይክራፎኑን ይዝጉት፤ አጀንዳ ካለ በአማካሪ ኮሚቴ አባል ስለሆኑ በአማካሪ ኮሚቴ እንነጋገራለን “

ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፤ ” አስቸኳይ ነው ዛሬ ም/ቤቱ እንዲያይልን የምንፈልገው “

አቶ ታገሰ ጫፎ፤ ” ቃለ ጉባኤ ላይ ሚቀርቡ እርማቶች እና ማስተከከያዎች ካሉ …”

ከዚህ በኃላ ዶ/ር ደሳለኝን ጨምሮ 4 አብን ተወካዮች ስብሰባውን ረግጠው ወጥተዋል። አቶ ክርስቲያን የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆናቸው አልወጡም።

You may also like...

Leave a Reply