የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የዜጎችን ደኅንነት የማስከበር ተቀዳሚ ኀላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ኢሰመጉ ጥሪ አቀረበ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ሰኔ 1/2014 ዓ.ም ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሚዥንጋ ወረዳ ሴነ ቀበሌ ውስጥ በሚገኙ መንደሮች በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሸኔ ታጣቂ ቡድን በመቶዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ አሰቃቂ ግድያ መፈጸሙን ማረጋገጡን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ገልጿል፡፡

በጥቃቱ በብዛት ሴቶች እና ሕጻናት ህይወታቸው ማለፉን የገለጸው ኢሰመጉ ከተጎጂዎች መካከል ጥቃቱን በመሸሽ መስጊድ ውስጥ ገብተው በነበሩ ሰዎች ላይም ጥቃት ተፈጽሞ በርካታ ሰዎች መገደላቸው ነው ያብራራው፡፡

ኢሰመጉ ጥቃቱ አሰቃቂ እና ጭካኔ የተሞላበት መኾኑንም ነው ያገኘውን መረጃ ዋቢ አድርጎ የገለጸው፡፡ በጥቃቱ የአካል ጉዳት፣ እገታና ንብረት ውድመት መከሰቱንም አስረድቷል፡፡ ጥቃቱን በመሸሽ በርካታ ሰዎች ህይወታቸውን ለማትረፍ በየጫካው ተበታትነው እንደሚገኙ አስረድቷል። ብዙ ቁጥር ያላቸው አስክሬኖችም በአንድ አካባቢ ላይ በጅምላ እንደተቀበሩ ኢሰመጉ ከአካባቢው ባገኘው መረጃ ለመረዳት ችሏል፡፡

ኢሰመጉ እንዳለው በጥቃቱ በአካባቢው የሚገኙ መኖሪያ ቤቶች በእሳት መቃጠላቸውን እና ጥቃቱ ከባድ መሳሪያ ጭምር በመጠቀም የተፈጸመ ነው፡፡ በዚህም በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት ምክንያት ኾኗል ነው ያለው፡፡

በአካባቢው የመንግሥት የጸጥታ ኀይል የተሰማራ ቢኾንም ተጨማሪ ኀይል በወረዳው በሚገኙ ቀበሌዎች ላይ ካልተሰማራ እና የሰዎች ደኀንነት ካልተጠበቀ ተጨማሪ ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል ኢሰመጉ ከአካባቢው ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችሏል፡፡

ኢሰመጉ በታጣቂዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶችን መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ዘላቂ መፍትሔን እንዲያበጅ በተደጋጋሚ ጥሪ ያቀረበ ቢኾንም የፌዴራል መንግሥት እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠቱ አሰቃቂው ድርጊት እንዲፈጠር ምክንያት መኾኑን ኢሰመጉ ለመረዳት ችሏል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ የደረሰውን ጥቃት ኢሰመጉ አውግዞ ባስተላለፈው ጥሪ እንዳለው

• የፌደራል መንግሥት እና የክልል መንግሥታት የዜጎችን ደኅንነት የማስከበር ተቀዳሚ ኀላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስቦ በአካባቢው ከሸኔ ጋር በሚደረጉ ውጊያዎች ሁለቱም ወገኖች በምንም ሁኔታ በግጭቱ ቀጥተኛ ተሳትፎ የማያደርጉ ሰዎችን ከማጥቃት እንዲቆጠቡ፡፡

• በተደጋጋሚ በአካባቢው የሚደርሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመቆጣጠር የአካባቢውን ሰላም እንዲያረጋግጥ፡፡

• በጥቃቱ ላይ ተሳትፎ ያላቸውን ማንኛውንም አካላት ተገቢውን ምርመራ በማድረግ በሕግ ተጠያቂ እንዲያደርግ፡፡

• በአካባቢው በቂ የጸጥታ አካላትን በማሰማራት መሰል ጥቃቶች ዳግም እንዳይፈጸሙ እንዲከላከል፡፡

• የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ ሲቪክ ማኅበራት እና የሚመለከታቸው ሁሉ መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት የማስከበር ኀላፊነቱን በቂ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ በመጠየቅ የበኩላቸውን ኀላፊነት እንዲወጡ ኢሰመጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ኢሰመጉ በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ የምርመራ ሥራን በማከናወን ለሕዝብ እና ለመንግሥት መረጃ እንደሚያደርስ ገልጿል፡፡

(አሚኮ)

Leave a Reply