ትህነግ አማራ በተጨፈጨፈ ማግስት አዲስ አሳብ ያልያዘ ስልታዊ የድርድር መግለጫ ሰጠ

ከትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ጋር በገሃድ ግንባር የፈጠረው የኦነግ ሸኔ ሰራዊት ከ700 በላይ የአማራ ተወላጆችን መጨፍጨፉን ይፋ ከሆነ በሁዋላ የትህነግ ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው በቪኦኤ አማካይነት ግልጽ ያልሆነና አዲስ ሃሳብ የሌለው መግለጫ ሰጡ። ድርድር አለመኖሩን ዜና አድርጎ ያሰራቸው ቪኦኤ ነው። ይህንኑ ጉዳይ አስመክተው ዶከተር ደብረጽዮን ከገለጹት የተለየ ይዘት የሌለው መረጃ እንዲተላለፍ የተደረገው በሰሞኑ ጭፍጨፋ የተፈጠረውን ሃዘን “አማራ እየሞተ ብልጽግና ከትህነግ ጋር በስውር ይደራደራል” በሚል ለማጋም እንደሆነ ታዛቢዎች አስታውቀዋል።

ቪኦኤ አቶ ጌታቸውን ጠቅሶ እንዳለው የተጀመረ የሰላም ድርድር የለም። ይሁን እንጂ የሰላም ድርድር እንዲጀመር ሶስተኛ ወገኖች ጥረት መጀመራቸው ተመልክቷል። እኒሁ ወገኖች ወደ መቀለ መመላለሳቸውን ልክ የናይጀሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ ህብረት ተወካይ ባሉት መልኩ ነው አቶ ጊታቸው ደግመው ያስታወቁት። አቶ ጌታቸው በነሱ በኩል ለሰላም ዝግጁ መሆናቸውን ቀደም ሲል ዶክተር ደብረጽዮን ደጋግመው እንዳሉት ብለዋል።

የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ከሰባት ጊዜ በላይ መመላለሳቸውንና ትናንትም የአውሮፓ ኅብረት ተወካዮች መቀሌ እንደነበሩ፣ ክልሉ ውስጥ አለ ያሉትን ሰብዓዊ ቀውስ ልዑካኑ እንዲያውቁ መደረጉን፣ አይደር ሆስፒታልንም እንደጎበኙ ቪኦኤ አቶ ጌታቸውን ጠቅሶ አመልክቷል። ኦባሳንጆ ቀደም ሲል ለሰባት ጊዜ ወደ ትግራይ መመላለሳቸውን መግለጻቸውን ያስታወሱ ዜናው አዲስ ሳይሆን ሆን ተብሎ ከአማራ ጭፍጨፋ ዜና በስተጀርባ መንግስት ከትህነግ ጋር እየተደራደረ እንደሆነ በማስተጋባት የህዝብን ሃዘን ወደ ቁጣ ለመለወጥ የታሰበ ቅንብር እንደሆነ ዜናውን የተከታተሉ ገልጸዋል።

“የትግራይን ህዝብ ህልውናና ደኅንነት ለሚያረጋግጥ የሰላም አማራጭ ቅድሚያ እንሰጣለን ካልሆነ ግን ወደ ሌላ አማራጭ እንሄዳለን” ሲሉ አቶ ጌታቸው አስታውቀዋል። አቶ ጌታቸው ቀደም ሲል ወደ ባህርዳር ለመሄድና አዲስ አበባ ለመግባት የሚያግዳቸው አንዳችም ምድራዊ ሃይል እንደሌለ ሲያስታውቁ እንደነበር ይታወሳል። አቶ ጌታቸው መንገድ እያማረጡ አዲስ አበባ እንደሚይዙ ሲናገሩ፣ ዶከተር ደብረጽዮን በበኩላቸው ” የመከላከያ ሰራዊት አባላት እጃችሁን ለትግራይ ሰራዊት ስጡ” እየሉ ጥሪና ማስፈራሪያ ሲያስተላልፉ እንደነበር አይዘነጋም።

አቶ ጌታቸው በዝርዝር ባይናገሩም፣ ቪኦኤም እንዲያብራሩ ባይጠይቅም በሃይል አማራጭ ለማስመለስ “ሌላ አማራጭ” እንደሚጠቀሙ ያስታወቁት ወልቃይት ጠገዴን ነው። በቅርቡ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶከተር ከፍያለው ” ወልቃይት ቀይ መስመራችን ነው” ሲሉ መናገራቸውና ቀደም ሲል ” በሃይል የተነጠቀ መሬት በሃይ ተመልሷል። የተዘጋ አጀንዳ ነው” ሲሉ አካባቢውን እየመሩ ያሉት ክፍሎች በተደጋጋሚ መናገራቸው ይታወሳል።

ከሺህ በላይ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ከመቀለ እንዳይወጡ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን ቢያስታውቅም አቶ ጌታቸው ስለዚህ ቅሬታ ያሉት ነገር የለም። ይልቁኑም የዕርዳታ አቅርቦት መሻሻሉን አመልክተው ዕርዳታውን ለማሰራጨት የነዳጅ ችግር መኖሩን አስታውቀዋል። በዚሁ ሳቢያ

30 ሺህ ሜትሪክ ቶንስ እህል ለህዝቡ ማድረስ እንደተሳናቸውና እርዳታው መጋዘን ውስጥ እንደተከማቸ አመልክተዋል።

“በነዳጅና በመድኃኒት እጥረት ምክንያት ህዝቡ እየተሰቃየ መሆኑን ልዑካኑ በአካል ተገኝተው ማየታቸውንና መጠለያ ውስጥ ስላሉና ችግር ውስጥ ስለሚገኙ የምዕራብ ትግራይ ተፈናቃዮችም ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል” ሲሉ አቶ ጌታቸው መናገራቸውን ያመለከተው ዘገባ፣ የእርዳታ አቅርቦትን በሚመለከት የአውሮፓዊያኑ ልዑካን ያላቸው አቋም ጠንካራ መሆኑን እንደገልፁላቸው መግለጻቸውን አስታውቋል።

ምንም ዓይነት አዲስ የድርድር አሳብ ያልተካተተበት የአቶ ጌታቸው መግለጫ “የፌዴራሉ መንግሥት እውነት ይሁን አይሁን ባናውቅም፤ የሰላም ፍላጎት እንዳለው በፓርላማ ጭምር አሳውቋል” ሲሉ የመግለጫውን ዋና ዓላማ በጨረፍታ አመላክተዋል። በዚህም ” ህዝብ እያለቀ መንግስት ከትህነግ ጋር በጓሮ ይደራደራል” የሚለውን ስሜት ለመፍጠርና ከኦነግ ሸኔ ጋር ያሰሉትን ሂሳብ በራሳቸው አንደበት ማሳበቃቸውን የገለጹ አሉ።

መንግስት በቅርቡ የተጀመረ ድርድር አለመኖሩን ጠቅሶ፣ ድርድርም ካለ በይፋ ለህዝብ እንደሚነገር፣ በድርድር ሊቀርቡ የሚጋባቸው ነጥቦች ምን እንደሆኑ የሚያጠና ኮሚቴ ማቋቋሙን ማስታወቁና ሲያልቅ በቅርቡ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ማስታወቁ ይታወሳል።

አቶ ጌታቸው የኤርትራን መንግሥት “የሰላም ዕድልን በማደናቀፍ” ሲከሱ የኤርትራ ኃይሎች እስካሁን የያዟቸው የትግራይ አካባቢዎች መኖራቸውንም በመጠቆም ነው። አቶ ጌታቸው “በሰላም ካልወጡ በኃይል እንዲወጡ ይደረጋል” ሲሉ ኤርትራ ላይ ሃይል እንደሚጠቀሙ ቀደም ሲል ሲሉ እንደነበረው አስታውቀዋል። አቶ ጌታቸው በኤርትራ ተይዘዋል ያሏቸው አካባቢዎች በአልጀርሱ ይግባኝ የሌለው ስምምነት መሰረት ለኤርትራ የተወሰነውንና የኢህአዴግ ማእከላዊ ኮሚቴ በሰላም ለኤርትራ እንዲሰጥ ውሳኔ ያሳለፈበትን አካባቢ ይሁን ሌላ በግልጽ አላስታወቁም።

በቅርቡ ለህዝባቸው ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጦርነት ከተጀመረ የፍሳሜ እንደሚሆን ማስታወቃቸው አይዘነጋም። በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ከሰባ ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን መሞታቸው፣ ከዚህ ሁሉ መስዋዕትነት በሁዋላ ባድመን ለሻእቢያ ለማስረከብ አቶ መለስ መስማማታቸው በታሪክ የተመዘገበ ታላቅ ክህደት እንደሆነ በርካታ ምስክሮች መሳፋቸውና ማሳተማቸው የሚታወስ ነው።

ትህነግ ምዕራብ ትግራይ የሚለው የወልቃይት ጠገዴ አካባቢ የወንጀልና የግፍ መዓት የተፈጸመበት፣ በርካታ የአማራ ተወላጆች እንዲፈናቀሉ የሆነበት ፣ ሃያ ከመቶ የሚሆነው ሕዝብ የት እንደጋባ የማይታወቅበት መሆኑንን የጎንደር ዩኒቨርስቲ ባካሄደው ጥናት ማስታወቁ ይታወሳል።

ፎቶ – ፋይል

Leave a Reply