ቲድሮስ ጥሩ ዘፋኝ፣ ጥሩ የፈጠራ ሰው፣ ምስጉን ባለሙያ ነው። ክርክር ያለው ጉዳይም አይደለም። በተለይም ቀን፣ ወቅት፣ ጊዜና ኩነት ጠብቆ የሚሰራቸው ስራቸው በከፍተኛ ደረጃ መነጋገሪያ ናቸው። እንደ ጥቁር ሰው፣ ያስተሰርያል፣ ኢትዮጵያ ያሉት የድንገተኛ ስራዎቹ ይጠቀሱለታል። ከኦሎምፒክ ማግስት በአንድ ቀን ለህትመት የበቃውን ዘፈኑንን [ ሮጬ ላሯሩጣቸው፤ ወይም ቀነኒሳ አንበሳ] የሚለውን ዜማ ከሪፖርተር ስፖርት ዓምድ የተባ ብዕር፣ ባለቤቱ በወጉ ከምታውቀው ሰው ላይ ወስዶ እውቅና ባለመስጠቱ ከምወቅሰው በቀር አድናቂው ነኝ። ወይም ለዛሬ ጽሁፌ አድናቂው ነበርኩ።

እዚህ ላይ እሱ አሳቡን ባሻው መልክ፣ ቀንና ወቅትም እየጠበቀ እንደሚገልጽ ሁሉ እኔም ስሜቴን በጨዋነት መግለጼ ባለቤቱን፣ አድናቂዎቹንና ወዳጆቹን ቅር ሊያሰኝ እንደማይችል ሙሉ እምነቴ መሆኑንን ቅድሚያ ማስታወቅ እወዳለሁ።

“ጊዜ እየጠበቀ ዜጎችን ለሞት ከሚዳርገው ረሃብ ለመታደግ ደኖቻችንን መንከባከብ፣ መትከል፣ መጠበቅ የዜግነት ግዴታችን ነው”

በግል ቅኔና ስውር ንግግር ብዙም ስለማይመስጠኝ “አረንጓዴ አሻራ” ወይም ችግኝ በሚተከልበት ቀን ቴዲ ያወጣውን “ናዕት” የተሰኘ አዲስ ዜማ ግጥም በግጥም ለመመርመር አልወደድኩም። ብሞክርም አይሆንልኝም። ስለዚህ በቀጥታ አራት ጥያቄዎችን ላንሳና “አረንጓዴ መሬት” ስለትባለው የአምለሰት ሙጬ ዶክመንታሪ ፊልምና ” ሚካኤል ችግኝ ነው። የስድስት ወር ልጅ ነው። ችግኝ ይተክላል” ሲል ቴዲ ለባለቤቱ ልጃቸው ችግኝ ሲተክል የሚያሳየውን ፎቶ ሲያበረክት የነበረውን እንደምታ በማንሳት አቋጫለሁ።

አራቱ ጥያቄዎቼ

  • የሰሜን ዕዝ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በክህደት ሲታረድ ቴዲ አፍሮ በገሃድ ወጥቶ ምን እንዳለ ሰምቼ አላውቅምና የሰማችሁ ያንን ክፍ ክህደትና ዘግናኝ ጭፍጨፋ ለጉድ የተረፉ ጀግንቾ እያነቡ፣ ድርጊቱን ፈሳሚዎቹ “መብረቃዊ ጥቃት” በሚል ሲተርኩት ቴዲ የት ነበር?
  • በዳግም ወረራ አማራ ክልል ወደ ዓመድነት ሲቀየር፣ በቃላት ሊገለጽ የማይችል አስደንጋጭ፣ ሊታመን የማይችል ግፍ፣ዝርፊያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ የጅምላ ጭፍጨፋ ሲፈጸም፣ አፋር ክልል ሲወደምና ጀግኖቹ የኢትዮጵያ ተምሳሌቶች ሲገደሉ፣ ገዳዬቹና ጨፍጫፊዎቹ በገሃድ ይታወቁ ነበርና ቴድሮስ ምን ብሎ ነበር?
  • ወረራውን ለመቀልበስ ሕዝብ ሲተም፣ ሃኪሞች፣ ነርሶች፣ የጤና መኮንኖች፣ ጡረተኞች ወደ ግንባር ደረታቸውን ሰጥተው ሲተሙ፣ የኪነትና የፈጠራ ባለሙያዎች ግንባር ገብተው የመከላከያን በስነ ልቦና ሲያነሳሱ፣ በወኔ ሲሞሉና እዱር እያደሩ አገራዊ ግዳጃቸውን ሲወጡ ቴዲ ምን እየሰራ ነበር? የዘመተበት፣ የወረደበትና የወጣበት ተራራ ካለ እባካችሁን ወዲህ በሉኝ።
  • የመጨረሻው ጉዳይ ለመልሶ ማቋቋም የሌሎቹን ልተወውና አሁንም ባልደረቦቹ በሙያቸው ሲቀኙ፣ ሃብት ሲስያሰባስቡ፣ የፈረሰ ቤተሰባና ስነ ልቦና ሲያክሙ፣ እርዳታ ሲያሰባስቡ ቴድሮስ ካሳሁን ምን ሰራ? በሶማሌ ሊታረድ የነብረን የትግራይ ልጅ ገንዘብ ከፍሎ ያዳነው ልቡ አማራ ክልል በደቦ ለተደፈሩ እህቶች በምን ምክንያት ሊጨክን ቻለ። የቲዎድሮስ አገር ልጆች በግፍ መዓት ሲወድሙ እንዴት መቀኘት አቃተው? ለዚህና ከዚህ ጋር ተያያዥነት ላላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ባገኝ ለህሊናዬ እረፍት ለጥያቄዬም ምላሽ አገኛለሁን እባካችሁን እነሆ በሉኝ።
ቪዲዮውን በግምት ስድስት ደቂቃ ይመልከቱ

ቪድዮው በዲሰምበር 30, 2014 ይፋ የሆነ ሲሆን ዓላማው የቴዲ ባለቤት አምለሰት ሙጪ ያዘጃችውን “አረንጓዴ መሬት” የሚለውንና በሷ እገላለጽ “ጥናት አድርጌ” ስትል የገለጸችውን ዘጋቢ ፊልም ለማብራራት ይመስለኛል። አልምለሰት እንዳለችው አመላካከት ለመቀየር።

በፊልሙ መጀመሪያ ጠኔ የመታት ላም፣ እንዲሁም የተራቆተ መሬትና ድርቅ የጎዳቸውን ህጻናት በማሳየት በሚጀምረው ቪዲዮ ውስጥ ሁና አምለሰት “ጊዜ እየጠበቀ ዜጎችን ለሞት ከሚዳርገው ረሃብ ለመታደግ ደኖቻችንን መንከባከብ፣ መትከል፣ መጠበቅ የዜግነት ግዴታችን ነው” ስትል ትታያለች። ተሰማለች።

አስከትላም ጥናት ስታደርግ ጉዳዩ አሳሳቢ እንደሆነ መረዳቷን ጠቁማ አስፈላጊውን ያህል ትኩረት እንዳልተሰጠው በመጠቆም የደን ልማትን አስፈላጊነት ታብራራለች። “አሳሳቢ ነው እንዴ” ብሎ ሕዝብ እንዲጠይቅ ለማድረግ አለማ ዘጋቢ ፊልሙን ለማዘጋጀት እንደተነሳች ታወሳለች። የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይን ” የምነውቃቀስበት ነገር ሳይሆን አገራዊ ጉዳይ እንደሆነ ቃል በቃል ታስተምራለች። በቪዲዮው ግርጌ እንደሚታየው አምለሰት የዜግነት ግዳጅዋን በዚህ ታላቅ የሃላፊነት ስሜት ካስታውቀች ብዙም ጊዜ አልፈጀም።

በሰዎች ጭንቅላት ውስጥ ስለ አካባቢ ጥበቃ በጎ አላማን ለመትከል በኮሌጆች፣ በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ በዩኒቨርስቲዎች፣ በትምህርት ቤቶች የመስራት ስንቅ መሰነቋን ያስታወቀቸው አምለሰት፣ ይህን ዓላማዋን ስታስተዋውቅ ባለቤቷ ቴዎድሮስ ስለሰታት [ ከላይ በምስሉ የሚታየውን ፎቶ] አስመልክታ ስሜቷን እንድታቻውተው ጆሲ ሲጠይቃት ” በህይወቴ ሁሉ በዚህ ደረጃ ተደስቼ አላውቅም” ብላለች። የስድስት ወር የአብራኳ ክፋይ፣ በቴዲ ቋንቋ “ራሱ ችግኝ፣ ራሱ ችግን ተካይ”

ብዙ ጊዜ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ከአፋቸው የማይጠፋው ምዕራባውያን፣ ኢትዮጵያ ለምታካሂደው አረንጓዴ ዐሻራ የገንዘብ ድጋፍ ሲጠየቁ ” ግብጽ ተቃውሞ ስላላት እንቸገራለን” ነው ያሉት። ግብጾች አረንጓዴ ዐሻራን የኢትዮጵያን አፈር ለማስቀረት የተጀመረ ዘመቻ ነው ብለው ነው የሚወስዱት። ግድቡን ማስቀረት ባይችሉ እንኳን በደለል እድሜውን ወይም ዐቅሙን ማሳጠር አንዱ ዓላማቸው ነው። ትግሉ ብዙ መልክ ነው ያለው።.
ዳንኤል ክብረት

“የፈጠራ ሰው በብዙ ነገር ጭንቅላቱ የተያዘ ነው። እስከ አገር ይደርሳል” ስትል ስሜቷንና የደስታዋን መጠን ያስታወቀችው አምለሰት ” የአካባቢ ጥበቃ ከቤት ይጀምራል” ስትልም እያንዳንዱ ዜጋ ለዚህ በጎ ተግባር የተሰጠና ሃላፊነት ያለበት እንደሆነ ጠቁማለች።

ላጠቃል – በፖለቲካ አመለካከትም ሆነ በድርጅት ድጋፍ የምንንም የግል እምነትና ፍላጎት አከብራለሁ። የኔም እንዲከበር እፈልጋለሁ። በጨዋነት አመለካከት ላይ መከራከርን እወዳለሁ። በዚህ እምነቴ ውስጥ ሆኜ በክብር ቴዲ አፍሮ ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሆነ ፓርቲያቸውን፣ መንግስታቸውንም ሆነ ደጋፊዎቻቸውን ቢያወግዝ መብቱ ነው። ባሻው ደረጃ ሊያበሻቅጣቸው ካሰበም ወሳኙ እሱ ነው። የስድስት ወር ልጁን “ችግኝ” ብሎ የጠራና ባለቤቱ የሰራችውን “አረንጓዴ ምድር” ዘጋቢ ፊልም በዚያ ደረጃ ያወደሰ፣ ችግኝ መትከልን ከአብራክ፣ ከምህጸን የተገኘውን ዘሩን ከችግኝ ጋር ያዋደደው ቴዲ እንዴት ችግኝ በሚተከልበት ቀን፣ ችግኝ መትከልን የሚይክል የአገር አጅንዳ ሊያራክስ ወሰነ?

” ሚካኤል ችግኝ ነው። የስድስት ወር ልጅ ነው። ችግኝ ይተክላል” ቴዲ

አምለሰት በዲሰምበር 2014 ስለ አረንጓዴ ምድር ድርቅ በመታቸው የሌሎች ችግኞች/ ህጻናት ልጆች፣ ከብቶችና ምድር መካከል ቆማ ” ጊዜ እየቆጠረ ዜጎችን በረሃብ…” ፊልሙን እስከ አምስት ደቂቃ እዩልኝ።

በሌሎች ጉዳዮች፣ በሌላ ጊዜ ሁሉን ማለት እየተቻለ ችግኝ መትከልን በደም በሚለውስ ዝማሬ ማራከስ ከቴዲ የሚጠበቅ አይመስለኝም። ለባለቤቱ አድናቆት ያስቸረው የችግኝ አጀንዳ በቢልዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በፎቶ ሳይሆን አፈር በመዛቅ፣ ቆሻሻ በማጽዳት ለተከሉትና እያስተከሉ ላሉት አብይ አህመድ መንፈግ ምክንያቱም ሊገባኝ አልቻለም። ማወደስ ቢያቅት በዚህ ልዩ አጀንዳ፣ለይቼ ባነሳሁት በችግኝ ተከላ አግባብ እሳቸውን አምቶ “አረንጓዴ አሻራን” በደም መለወስ አድሮ የሚቆጭ ይመስለኛል። እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረስኩት ለዚህ ጽሁፍ ማጣቀሻ የተጠቀምኩበትን ምስል ደጋግሜ ካየሁ በሁዋላ “ዳር ቆሞ” ከመውቀስና በጅምላ ጭቃ ከመቀባት መታቀብ በራሱ አዋቂነት እንደሆነ ለማመላከትና ለማሳሰብ ነው። ቴዲ በአሜሪካ በቅርቡ በምታደርገው ኮንሰርት መልካም እመኛለሁ።

ሰለሞን ካሳዬ ከአሜሪካ

ፎቶ ከቪዲዮው ላይ የተወሰደ – ከላሚቷ የድርቅ ገጽታ ስር የሚታየው ጹሁፍም አምለሰት የተናገረቸው ነው። አምለሰት ሞዴሊስት ተዋናይና የመልካም ሰው መገልጫ አድርጌ ከምወስዳቸው እህቶች መካከል ነበረች።

Leave a Reply