ከአገራዊ ለውጡ በኋላ በአማራና በኦሮሞ ማኅበረሰብ መካከል የነበሩ ማህበራዊ ግጭቶች ተከታታይነት ወዳለው ጥቃት እንዲሸጋገር የትህነግና ሸኔ ቡድኖች ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝምና አስተዳደር መምህር ምስክሮችን ጠቅሰው ይፋ አደረጉ። ሁለቱ ድርጅቶች በይፋ አብረው እንደሚሰሩ ማስታወቃቸው ይታወሳል።

በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ስላለው ማህበራዊ መስተጋብር ጥናት ያደረጉት ዶክተር ታምራት ቸሩ ለኢዜአ ሲናገሩ ከአገራዊ ለውጡ በፊት በአማራና በኦሮሞ ማህበረሰብ መካከል በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም፣ በመሬት ግጦሽና በማህበራዊ ግንኙነቶች አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ ግጭቶች ነበሩ። ነገር ግን ከግጭትነት የዘለለ ችግር እንዳልነበረውና በባህሪውም ከወቅታዊነት የማያልፍ እንደነበር ገልጸዋል።

እንደ ዶክተሩ ገለጻ፣ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ቀጠናውን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም በሁለቱ ትላልቅ ሕዝቦች መካከል ቀደም ሲል የነበረው የማህበራዊ ግንኙነት ግጭት ቅርጹን እንዲቀይር በማድረግ ብዙ አካላት ተሳትፈዋል። በዋናነት ግን የትህነግና ሸኔ ሚና እጅግ የጎላ እንደሆነ አመልክተዋል።

እንዲሁም ከአካባቢ አልፎ በሁለቱ ሰፊና ትላልቅ ክልሎች መንግሥታት መካከል ቁርሾና መናቆር እንዲኖር ለማድረግ የትህነግን ተልዕኮ ተቀብሎ የሚያስፈጽመው ሸኔ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እንደተሳተፉ ኅብረተሰቡ ለጥናቱ በሰጡት መረጃ ማረጋገጥ መቻሉን አጥኚው አመልክተዋል።

ቀደም ሲል የነበረውን ግጭት ቅርጽን ለውጦ ከግጭትነት አልፎ ወደ ተከታታይነት ጥቃት እንዲሸጋገር በማድረግ የበርካታ ንጹሐን ዜጎች ሕይወት አልፏል ያሉት ጥናት አቅራቢው፤ ይህም በንብረት ላይ ውድመትና በሁለቱም ኅብረተሰብ ዘንድ ፍርሃት እንዲነግስ ማድረጉንም ገልጸዋል።

“የአማራና ኦሮሞ ማህበረሰብ ለዘመናት ጠንካራ የሆነ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብርና ትስስር ያላቸው ናቸው” ያሉት ዶክተር ታምራት፤ ሕዝብ እንደ ሕዝብ አንዱ በአንዱ ላይ ጉዳት ለማድረስ አስበው አይንቀሳቀሱም። ነገር ግን የራሳቸውን ፍላጎት በሕዝብ ላይ በመጫን በኅብረተሰብ መካከል ያለ መልካም ግንኙነት እንዲሻክር፤ ከዚያ አልፎ በአገር ደረጃ ሰላም እንዳይኖር በማድረግ ረገድ ትህነግና ሸኔ በጥምረት ሰርተዋል። እየሰሩም ነው።

አገራዊ ለውጡ መርህ አልባና የተለያዩ ፍላጎቶች ያለ ሕግ እንዲመሩና የራስን ፍላጎት በሕዝብ ላይ ለመጫን ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር የትህነግና የሸኔ ቡድኖች ዋና ተዋናይ ነበሩ ያሉት ዶክተር ታምራት፤ እንዲሁም ሕገወጥ መሣሪያና የሰዎች አዘዋዋሪ አካላት ምቹ ሁኔታን በመጠቀም ፍላጎታቸውን ኢ ሰላማዊ በሆነ እንቅስቃሴ ለመተግበር የሚያደርጉት ሚና ተጨማሪ አስተዋጾ እንዳላቸው አመልክተዋል።

በየአካባቢው የሚገኙ የመንግሥት መዋቅር ለችግሩ የመፍትሄ አካል ከመሆን ይልቅ እንወክለዋለን ለሚሉት ማኅበረሰብ ወገንተኛ መስሎ በመታየት ችግሩ እንዲባባስ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዳደረጉም ዶክተር ታምራት ገልጸዋል።

ትህነግና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት የሚለው አካል ስምምነት ማድረጋቸው ይፋ መሆኑንን ተከትሎ ከጥቂት አካባቢዎች በስተቀር አብዣኛው ኦሮሞ ጀርባ መስጠቱ ይታወሳል። ውሳኔውን በኦሮሞ ህዝብ ላይ የተፈጸመ ክህደት አድርገው የሚመለከቱም አሉ።

Leave a Reply