መንግሥት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያጋጠመዉን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንደሚሠራ የፍትሕ ሚኒስትርና የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶክተር) ገለጹ።
በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተፈጠሩ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል ዉይይት በብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እና በማእከላዊ ኮሚቴዉ መካሄዱን የፍትሕ ሚኒስትርና የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶክተር) ተናገሩ።
ዶክተር ጌዲዮን ፓርቲው ሰላማዊ ዉይይት ለማድረግ ዉሳኔ አሳልፏል ብለዋል።
በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተካሄደው ጦርነት መንግሥት ተገዶ የገባበት መኾኑን ያነሱት የፍትሕ ሚኒስትሩ መንግሥት ይህንን ለመፍታት እየሠራ ስለመኾኑም አስረድተዋል ።
ፓርቲዉ ተጨማሪ ደም መፋሰስ እንዳይኖር ታሳቢ በማድረግ ለሰላም ቅድሚያ ይሰጣል ነው ያሉት።
በዚህም መሠረት በፌዴራል መንግስት በኩል የሰላም ተደራዳሪ ቡድን መሰየሙን ለኢፕድ የደረሰው መረጃ ያሳያል። የቡድኑ አባላትም የሚከተሉት ናቸው፤
1ኛ. አቶ ደመቀ መኮንን……..ሰብሳቢ
2ኛ. ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቲዎስ…..አባል
3ኛ. አቶ ተመስገን ጥሩነህ……አባል
4ኛ. አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር….አባል
5ኛ. አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን…..አባል
6ኛ. ሌ/ል ጀኔራል ብርሀኑ በቀለ….አባል
7ኛ. ዶ/ር ጌታቸው ጀምበር………አባል
ዶክተር ጌዲዮን እንዳሉት ፓርቲዉ ባስቀመጠዉ አቅጣጫ መሰረት የሰላም አማራጩ፡-
- ሕገ መንግሥታዊ እና ሕጋዊነትን የሚያስከብር መኾን አለበት፡፡
- የሀገርን ክብር የሚያስጠብቅ መኾን አለበት፡፡
- በሀገር ዉስጥ መፍታት ካልተቻለ በአፍሪካ ሕብረት ጉዳዩ መታየት እንዳለበት በሥራ አስፈጻሚ እና በማእከላዊ ኮሚቴ ዉይይት ዉሳኔ መተላለፉን አንስተዋል።
በተጨማሪም ትንኮሳዎች ካሉ ሕግ አስከባሪዉ እርምጃ እንዲወሰድ ዉሳኔ መተላለፉን ዶክተር ጌዲዮን አንስተዋል። ሕዝቡ ለዚህ ተሳታፊ እንዲኾንም ጥሪ አስተላልዋል።(አሚኮ)
በሰሜን የአገሪቷ ክፍል ያለውን ችግር ለመፍታት በፌዴራል መንግሥት በኩል የሰላም ተደራዳሪ ቡድን ተሠየመ