በ1947 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል በአሰላ ከተማ የተወለዱት ፕሮፌሰር የዓለምፀሐይ መኮንን ታሪክ በኢትዮጵያ የመጀመሪዋ ሴት ፕሮፌሰር አድርጎ መዝግቧቸዋል።

በአባታቸው የፖሊስ መኮንነት ሙያ ምክንያት በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወሩ ያደጉት ፕሮፌሰር የዓለምፀሐይ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በደሴ እና በጎጃም ፍኖተ ሰላም ተከታትለዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአዲስ አበባ ዳግማዊ ሚኒሊክ ትምህርት ቤት ነበር ያጠናቀቁት።

ፕሮፌሰር የዓለምፀሐይ በተማሪነት ዘመናቸው ለሳይንስ ትምህርት ከፍተኛ ፍቅር የነበራቸው ሲሆን ከክፍላቸው ከፍተኛውን ውጤት የሚያስመዘግቡ ቁንጮ ነበሩ።
ሁለት የክፍል ደረጃዎችን ጭምር በአንድ ዓመት በማጠናቀቅ በ16 ዓመታቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ለመቀላቀል መብቃታቸውን የህይወት ድርሳናቸው ያሳያል።

የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አጠናቀው በረዳት መምህርነት እዚያው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሲያስተምሩ ቆይተው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በእንስሳት ጥናት/zoology/ በትምህርት ዘርፉ በድህረ ምረቃ ፕሮግራሙ የመጀመሪያዋ ሴት ተመራቂ በመሆን አጠናቀዋል።

ቀጥሎም ጀርመን ወደ ሚገኘው ሃይደልበርግ ዩኒቨርሲቲ በማቅናት በፊዚዮሎጂ ትምህርት ዘርፍ በተለይም የሆርሞኖች ስነ ህይወት ላይ በማተኮር የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።

ወደሀገራቸው በመመለስም በስነ ህይወት ትምህርት ክፍል ውስጥ በረዳት ፕሮፌሰርነት እና በተባባሪ ፕሮፌሰርነት ሰርተዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በነበራቸው ቆይታ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በማጤን በጥር 2001 ዓ.ም የሙሉ የፕሮፌሰርነት ማዕረግን ሰጥቷቸዋል።

በአሁኑ ጊዜ በዩኒቨርሲቲው የሥነ ህይወት ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር የዓለምፀሐይ መኮንን፣ የዛሬ 14 ዓመት በትምህርትና በተመራማሪነት ያገኙት የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ከኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ያደርጋቸዋል።

በቤተሰባዊ ህይወታቸው የሁለት ልጆች እናት እና የሁለት ልጆች አያት የሆኑት ፕሮፌሰር የዓለምፀሐይ ፣የተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍን ለወንዶች የሚያስቀድመውን ዘልማድ የተሻገሩ ጠንካራ ሴት ናቸው።

ከፕሮፌሰር የዓለምፀሐይ መኮንን አበርክቶዎች ዋና ዋናዎቹ፡-

🏆በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ውጤት በጣም ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ከቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ እጅ የክብር ሽልማት ተቀብለዋል።

🏆በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሴቶች ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማህበረሰብ እንዲጠነሰስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

🏆ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የወርቅ ሜዳሊያ እና ሰርተፍኬት ተሸላሚ

🏆በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስነ ህይወት ትምህርት ክፍል ኃላፊ

🏆የአክሊሉ ለማ ፓቶባዮሎጂ ተቋም ዳይሬክተር

🏆በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የስነ-ጾታ ቢሮ ኃላፊ

🏆በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለ36 ዓመታት በመምህርነት፣ በትምህርት ክፍል ኃላፊነት እና ተመራማሪ

🏆የ2007 ዓ.ም ምርጥ ሴት ሳይንቲስት የአፍሪካ ህብረት የክዋሜ ንክሩማህ ሳይንሳዊ ሽልማት አሸናፊ

🏆የተለያዩ ሳይንሳዊ ተቋማት አባል፣ መምህር እና ኃላፊ ከዓለም አቀፉ የገጠር መልሶ ግንባታ የላቀ አፈፃፀም ተሸላሚ

🏆የአሌክሳንደር ቮን ሀምቦልድ ፋውንዴሽን ተሸላሚ

🏆በእርሻ ሳይንስ እና በቴክኖሎጂ ልማት ከሰሀራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት አስተባባሪ

🏆የኢትዮጵያን ሳይንስ አካዳሚ መስራች እና የቦርድ አባል ሆነውም አገልግለዋል።

በኢትዮጵያ እና በዓለምአቀፍ ደረጃ ከተለያዩ የሳይንስ ተቋማት ጋር በመተባበር 92 ሳይንሳዊ የምርምር ጹሁፎችን በማበርከት እና መሰል ተመሳሳይ የላቀ አበርክቷቸው ተምሳሌት የሚሆኑ ተመራማሪ ናቸው ።

(በኢቢሲ ሳይበር ሚዲያ፤ሰኔ 16፣2014)

Leave a Reply