በኢትዮጵያ እኩይ ዓላማን አንግበው በሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ዘርን፣ ብሔርን፣ ፖለቲካን፣ ሃይማኖትና ሌሎችንም ምክንያቶች መነሻ በማድረግ በሚፈጥሩት ጥቃት ንጹሐን ወገኖች ለሞት እና መፈናቀል እየዳረገ ይገኛል። በተለይም ማንነትን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ ክልሎች ከትናንት እስከ ዛሬ በአማራዎች ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ግድያና ውድመት ታሪክ የሚዘነጋው አይደለም።

ጽንፈኛ የኾኑ አንዳንድ ፖለቲከኞች እጃቸውን ባስገቡበት ኹሉ የንጹሐን ደም ፈስሷል፣ የሕጻን አዛውንቱ የማያባራ “የአትግደሉን” ተማጽኖ ሰሚ ጆሮ አጥቷል።

በአማራ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎችም ለዓመታት እኩይ ዓላማን ያነገቡ አካላት በሚሸርቡት ሴራ ሕዝብን ከሕዝብ ሲያባሉ ኖረዋል። ምንም የማያውቁ ንጹሐን ስደት፣ ስቃይ እና ሞት ተፈርዶባቸው የክፉዎች ሰለባ ኾነዋል።

የኹለቱን ሕዝቦች መከራ ለመቀነስ ከከፍተኛ አመራሩ እስከ ታችኛው ሕዝብ የደረሰ ተደጋጋሚ የሰላምና የእርቅ ውይይቶች ተካሂደዋል። "መልካም ውጤት የታየበት የእርቅና ሰላም መድረክ- በአዊ"

በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና በመተከል ዞን አዋሳኝ ወረዳዎች የሚፈጠርን ግጭት ለማስቆም የጋራ ሰላምን በጋራ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የሕዝብ ለሕዝብ ውይይት መድረኮች ተካሂደዋል። በእርግጥም የሰላምና የእርቅ ውይይቶች ተስፋ ያለው ውጤት ማስመዝገባቸው እየተነገረ ነው።

ዛሬም በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዞን የጓንጓ ወረዳ እና በመተከል ዞን የድባጤ ወረዳ ነዋሪዎች የሕዝብ ለሕዝብ የሰላም መድረክ በጓንጓ ወረዳ አዲስ ዓለም ቀበሌ ላይ አካሂደዋል።

መድረኩ የተዘጋጀው ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የኹለቱንም ክልሎች የጋራ ሰላም ለማስፈን የሚያስችሉ ውይይቶች ለማካሄድና የጋራ እቅድ በመያዝ መኾኑን የጓንጓ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አቶ ቴዎድሮስ እንዳለው ተናግረዋል።

መድረኩ ኹለቱን ወረዳዎችና አካባቢያቸውን ወደ ነበረበት ሰላም መመለስ የሚያስችል ነው ብለውታል።

ከዚህ ቀደም በቢዛከኒ፣ በመንታ ውኃ፣ በየጨረቃ ቀበሌዎች የእርቀ ሰላም መድረክ ተካሂዶ መልካም ውጤቶችን ማምጣት እንደተቻለም ነው የተናገሩት። እኩይ ተልዕኮ ይዘው ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ አካላትን መታገል የሚቻለው ለጋራ ሰላምና ደኅንነት በጋራ መሥራት ሲቻል ነው ብለዋል።

የኹለቱም የጸጥታ ኀይሎች ባደረጉት የሰላም ማስፈን ተግባር አንጻራዊ ሰላም ማረጋገጥ ተችሏል ነው ያሉት።

የድባጤ ወረዳ ዋና አሥተዳደሪ ሙሉዓለም አውያ በበኩላቸው ሕዝብ ከሕዝብ ተጋጭቶ አያውቅም፤ የእስካሁኑ የግጭት ምክንያቶች ኹሉ የጠላቶች የፖለቲካ ሴራ ውጤት ነው ብለዋል።

የኹለቱን ሕዝቦች የቀደመ አብሮነትና የጋራ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን ማዘጋጀት ላይ በትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑም ነው የተናገሩት። ለዚህም የፖለቲካ አመራሩ አስቀድሞ የጋራ የምክክር መድረኮችን በማከናወን ሕግ የማስከበርና የኹለቱን ሕዝቦች ሰላም የማረጋገጥ ሥራ ላይ ያለልዩነት መሥራት እንደሚገባ ውሳኔ ላይ ተደርሷል ነው ያሉት። "የግጭት ምንጮችን ማድረቅ ለቀጣይ አብሮነት"

በውይይት መድረኩ የታደሙ አስተያየት ሰጭዎች “የኢትዮጵያ ጠላቶችና ተላላኪዎች ሀገራችንን የመከራ ምድር እንዲያደርጓት መፍቀድ የለብንም፤ የፖለቲካ መሪዎች የሰላም፣ የእርቅና የልማት መንገድ በር ከፋች መኾን አለባቸው” ብለዋል።

የሚያጣላ እና የሚያጋጭ የክፉዎች ተንኮል እንጂ የጥቅም ጉዳይ አገናኝቶን፤ መሬት ጠቦን አይደለም ነው ያሉት።

ችግሩን በውይይት የሚፈታ፣ ወንድማዊ መተሳሰብና ባሕል ያለን ነን ያሉት አስተያየት ሰጭዎቹ የኢትዮጵያ ጠላቶች ሀገሪቱን የመከራ ምድር እንዲያደርጓት በፍጹም መፈቀድ የለበንም፤ በቃ ማለት ያስፈልጋል ብለዋል።

ልማት የሚያገናኘው፣ አዋሳኝ የእርሻ ቦታ የሚያገናኘው፣ ማኅበራዊም ኾነ ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ያለው ሕዝብ በጠላት ወጥመድ ተጠልፎ እየወደቀ በየምክንያቱ ንጹሐንን ሰለባ ማድረግ መቆም ይገባል ነው ያሉት።

ከግጭት ሞት፣ ከግጭት ውድመት ነው ያተረፍነው ያሉት ታዳሚዎቹ ይህ አይነቱ የሰላምና የእርቅ የውይይት መድረክ ተጠናክሮ መቀጥል አለበት ብለዋል።

ከጎረቤቶቻቸው ጋር የነበራቸውን የቆየ ማኅበራዊ ግንኙነት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ነው የተናገሩት። “በሀገራችን የንጹሐን እንባና ደም የሚፈስበት ጊዜ ሊያበቃ ይገባል” ብለዋል። "ይቅርታ- እርቅ- ፍቅር የሰላም በሮች መክፈቻ"

የአማራ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የሰላምና የልማት ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መላኩ አልጋመር በመድረኩ ባሰተላለፉት መልዕክት የሰላም እና የእርቅ መነሻው ያለፈን ይቅር ማለት ነውና ባለፈው በደረሰ ግጭት የተከፈለን እልቂት እያሰቡ መቆዘም፣ በቂምና ጥላቻ ስሌት የጥፋት በትር ማንሳት አይገባም ብለዋል።

ኀላፊው እንዳሉት እነዚህ ግጭት አድራቂ የሰላምና እርቅ መድረኮች የፍቅር በር መክፈት አለባቸው።

የዚህ መድረክ ዓላማም በጠላት በተሸረበ የፖለቲካ ሴራ ዋጋ ያስከፈሉ የቁርሾ ምክንያቶችን በመተው የቀደመ የጋራ የልማት የሰላምና የአብሮነት መስተጋብሮችን መመለስ ማስቻል እንደኾነም ነው የተናገሩት።

የሰላምና እርቅ መድረክ አዘጋጆቹ የጓንጓ ወረዳ እና የድባጤ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪዎችም የሰላም ውይይቱ ፍሬ አፍርቶ የኹለቱ ሕዝቦች ወደ ቀደመ የጋራ አብሮነትና ወንድማማችነታቸው እንዲመለሱ የግጭት ምንጭ የሚኾኑ ምክንያቶችን ለማድረቅ በጋራ እየሠሩ መኾኑን አስገንዝበዋል።

ለሰላምና ደኅንነት መረጋገጥም ሰላም ወዳዱ ሕዝብ ከጎናቸው በመኾን እኩይ ተልዕኮ ይዘው የሚንቀሳቀሱ አካላትን እንዲታገልም አሳስበዋል።

መድረኩ በአካባቢው ባሕል መሠረት ሰላምን ለማስፈንና የእኩይ አካላት ተባባሪ ላለመኾን በሚያስችለው “ቃለ-መሃላ” ተቋጭቷል።

ዘጋቢ:- ጋሻው አደመ

(አሚኮ)

Leave a Reply