የችግኝ ተከላ ተቃውሞ ተናብቦ የመሥራት የሰኔ ፕሮጀክት ይሆን ብለን እንድንጠይቅ ገፋፍቶናል? እርሱ ከባለቤቱ ጋር “የአረንጓዴው መሬት” ሃሳብን ሲያራምዱና ችግኝ ሲተክሉ፣ ችግኙ ሚካኤልም እንዲሁ ችግኝ ሲተክል ሕዝብ ይጨፈጨፍ ነበር። የቴዲን የዚያን ጊዜውን ሃሳብ ማንም አልተቃወመም። “ሚካኤል ችግኝ ነው። … ችግኝ ይተክላል” ያለው ቴዲ የሕዝብ ሰቆቃ ድምፅ ነኝ በሚል “ሳር ያለመልማል ዛሬም በእልፍ አእላፍ ሬሳ” ብሎ ቀን ጠብቆ በችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ ዕለት ነጠላ ዜማ መልቀቁን ግን ሚዛን ደፊውን ቴዲ ሚዛን ተደፋብህ አስብሎናል።

ቴዲ አፍሮን የሚወዱት ሰዎች እጅግ በርካታ የመሆናቸውን ያህል ጥቂት የማይባሉ ደግሞ አምርረው ይጠሉታል። ደጋፊዎቹ በተለይ በዘመነ ትህነግ በድፍረት የሚያዜማቸውን እያነሱ “የአንድ ሰው ሠራዊት” ይሉታል። የሚጠሉት ደግሞ ቴዲ “ሰላም፤ እንደምን አደራችሁ?” ቢል እንኳን “ይሄ የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ፣ …” በማለት የስድብ ናዳ ያወርዱበታል።

ቴዲ በትህነግ ዘመን ግልጽ ግፎች ደርሰውበታል። የሙዚቃ ኮንሰርቶቹ ያለ ምንም ካሣና ቅድመ ማስታወቂያ ቲኬት ከተሸጠ በኋላ በተደጋጋሚ ተሰርዘውበታል። የጎዳና ተዳዳሪ ገድለሃል በሚል ክስ ለእስር በተዳረገበት ጊዜ ፍርድ ቤት በቀረበ ቁጥር ያለማቋረጥ እያለቀሰ ንጹሕ መሆኑን ለማሳመን ሞክሯል። ከእስር የተለቀቀበት አግባብም በራሱ ብዙ ሊያስብል የሚችል ነው።

በአገራችን የለውጥ መዓበል በተነሳበት ወቅት ጃዋርን ጨምሮ አክራሪና ጽንፈኛ ኦሮሞዎች ከአገር ውስጥ እስከ ውጪ የተጠናከረ የቢራ ፖለቲካዊ ዘመቻ በከፈቱበት ጊዜ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ እንደሚዲያ ተግባሩን በማውገዝ ተሟግተናል። ይህ ብቻ አይደለም፤ ቴዲ “ምኒልክ ጥቁር ሰው” በሚለው ሙዚቃው በድፍረት የሄደበትን መንገድ፤ ያውም በዘመነ ትህነግ፤ አድንቀናል፤ አወድሰናል። የሚቃወሙትም እስከ ጥግ ሄደው ብዙ ብለዋል።

ቴዲ አፍሮ ዘመን ተሻጋሪ በሆኑ የሙዚቃ ሥራዎቹ የሚታወቅ ነው፤ ሁኔታዎችን ዓይቶ የሚወስደው እርምጃና የሚለቀው ነጠላ ዘፈን በአንዳንዶች ዘንድ “ጥቅመኛ” የሚል ስያሜ የሚያሰጠው ቢሆንም ድፍረቱ ግን ታዋቂነቱንና የደጋፊውን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጨምርለት ያደረገ ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ የትግራይ ተወላጅ ሙስሊም ወጣት በሶማሊያ የተበየነበትን ፍርድ ቴዲ በሺዎች ብር ከፍሎ፣ ነጻ አስወጥቶ፣ ከቤተሰቡ እንዲቀላል ያደረገበት የሚረሳ አይደለም።

ታላቁ የአደባባይ ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ከሚታወቁባቸው መለያዎች ዋነኛው እውነትን ቁልጭ አድርገው በመናገራቸው ወይም በመጻፋቸው ነው፤ ለዚህም በርካታ እንግልት ደርሶባቸዋል። በቅርብ ጓደኞቻቸው ተከድተው ብቸኛ ሆነዋል። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ሲመረጡ ሕዝቡ የመጀመሪያ ሴት የአገራችን መሪ ሆነው ሲያይ ደስ አለው። የኔታ መስፍን ግን የተቃውሞ ድምጻቸውን ካሰሙት ቀዳሚው ሆነው ሲታወሱ ይኖራል።

ግን ደግሞ ፕሮፍ ጭፍን ተቃዋሚ ብቻ አልነበሩም። ባህርያቸው የፈለገ ክፉ ቢሆን መንግሥትንም ሆነ ግለሰብ የቱንም ያህል የሚቃወሙት ቢሆን መልካሙን ሥራውን ግን ይጠቅሳሉ። ለምሳሌ የፓርቲ ፖለቲካና ውይይትን በአገራችን ያስጀመረው ወያኔ ነው በማለት ፕሮፍ ተገቢውን ምስጋና ይቸራሉ። ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምን በንቁ አድማጭነቱ ያደንቁታል፤ ለሌሎችም እንዲሁ ተግባራቸውን ቢጸየፉ እንኳን በጭፍንና በጅምላ ወይም እንደ መድረክ ሰው የሕዝብን ጭብጨባ ለማግኘት ሲሉ ብቻ ሰውን አይነቅፉም፤ በመንጋ አስተሳሰብ አይመሩም። እንዲያውም “ጭብጨባ ሲበዛ ጭንቅላት ያብጣል” ይሉ ነበር።

ትህነግ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሕዝብን ጠፍንጎ በያዘበትና በተለይም የአማራን ሕዝብ ለማጥቃት ብሎ ግፉንና መከራውን ባከረረው ጊዜ፤ የወልቃይት ሕዝብ መግቢያ አጥቶ በጅምላ ሲጨፈጨፍ በነበረበት ጊዜ፤ ለአገር የሚያስቡ ሰዎች አልጠፉም ነበር። የአገራችን የወደፊት በረሃነትና የሕዝቧ መከራ ያሳሰባት አምለሰት ሙጬ ከባለቤቷ ጋር “አረንጓዴ መሬት” ብላ ችግኝ የመትከልን ተግባር በወጣቱ ዘንድ እንዲስፋፋ ፕሮጀክት ነድፋ ነበር። ዘጋቢ ፊልም ሠርታ ተሸልማበታለች፣ ተሞግሳበታለች። ቴዲም ለዚሁ ፕሮጀክቷ ዘፍኖላታል። በፊልሙ ላይ መቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ (የቀድሞ የኢህአዴግ ፕሬዚዳንት)፣ የ“ለም ኢትዮጵያ” መሥራች የሚባለውና የትህነግ ተሟጋች ቆስጠንጢኖስ በርኼ (ዶ/ር ነኝ የሚል ግን ዲግሪዎቹ በሙሉ የሐሰት የሆኑ)፣ አዜብ ግርማይ ከENDA ግብረሰናይ ድርጅት፤ እና ሌሎችም ታዋቂ ሰዎችና የሙያው ባለቤቶች ተሳትፈውበታል።    

የዛሬ ሰባት ዓመት አካባቢ የዞን ዘጠኝ ልጆች በትህነግ እስር ቤት ሲማቅቁና በካንጋሮ ፍርድ ቤት ሲንገላቱ፤ የእስር ቤቱ ቋንቋ ኦሮምኛ በነበረበት ጊዜ፣ ቀይ ባሕርን አቋርጠው ወደ አረብ አገር ከተሳካላቸውም ወደ አውሮጳ ሲሰደዱ የአዞ ምሳ ሆነው ሲቀሩና በአንድ ቀን ብቻ 70 የሚሆኑ ሲሞቱ፤ ትህነግ በባሕር ዳር አማራዎችን ሲያርድና መነኮሳትን ሲገድል፣ቤተእምነትን ሲያረክስ፤ በጉራ ፈርዳ አማሮች ለዓመታት ሲያርሱት የነበረውን መሬታቸውን ተነጥቀው አቤት የሚልላቸው ጠፍቶ አንገታቸውን ሲደፉና ያለ ጥሪት ሲቀሩ፤ ወዘተ በዚያኑ ጊዜ የአገርን ወደፊት ያሰቡና የተጉ ለሠሩት ተግባር በሒልተን ሆቴል ሽልማት ሲደረግላቸው ነበር

በታኅሳስ 2007ዓም በሒልተን ሆቴል በተካሄደው ሥነሥርዓት ላይ ቴዲ አፍሮ ይናገራል፤ ያመሰግናል። ተሸላሚዋና ተመስጋኟ ሚስቱ አምለሰት ነች። “አረንጓዴ መሬት” ዘጋቢ ፊልም የሠራችውና ያዘጋጀችው ባለቤቱ አምለሰት ሙጬ ወደ መድረክ ተጠርታ ባሏ ያዘጋጀላትን ግን ያላሰበችውን ሥጦታ እንድትቀበል ቴዲ ይጠራታል። ትልቅ ፎቶ ነው ሽልማቱ። አላሰበችውምና ተደነቀች፣ እጅግ ተደሰተች። ሚካኤል ቴዎድሮስ ገና ጨቅላ ሕጻን ነበር፤ የስድስት ወር ልጅ። በፎቶው ላይ ችግኝ ሲተክል ይታያል። ቴዲም ሽልማቱን ለሚስቱ ሲሰጥ ይህንን አለ፤ “ሚካኤል ራሱ ችግኝ ነው፤ የስድስት ወር ልጅ ነው። ችግኝ እየተከለ ነው”።

በደርግ ጊዜ የአካባቢ ጥበቃና የደን ልማት በሰፊው ይካሄድ ነበር። በወቅቱ የመሥሪያ ቤቱ ኃላፊ የነበሩት ከዚህ በፊት ለጎልጉል የተናገሩት የማይረሳ ነው። በእርሳቸው አመራር 1 ሚሊዮን ችግኝ ከአዲስ አበባ እንጦጦ እስከ ሰሜን ሸዋ ባለው እንዲተከል አድርገው ነበር። “አረንጓዴ አሻራ” ከመተግበሩ በፊት እንጦጦ ላይ የምናያቸው ዛፎች በእርሳቸው አመራር የተተከሉ ነበሩ። ያኔ በመተከላቸው ዘመናትንና ትውልድን ተሻግረው በርካታዎችን ጠቀሙ፤ አገርን አለሙ፤ አካባቢን ጠበቁ።

ደርግን ይጠሉና ይቃወሙ የነበሩ ኢህአፓዎች ግን ጸረ ችግኝ ነበሩ። ደርግን የጎዱ ይመስል በወዶ ፈቃደኝነት ለችግኝ ተከላ ሲዘምቱ ወይ ቀድሞ የተተከሉትን ወይም ራሳቸው የሚተክሉትን ችግኞች እየገለበጡ ይተክሉና በአገር ላይ ኪራሣ ያስከትሉ ነበር ብለው ኃላፊው ነግረውናል። ችግን ተከላን መቃወም ጤና ቢስነት ነው።

ትህነግ ሠሜን ዕዝ ላይ በራሱ ቃል “መብረቃዊ ጥቃት” አድርሶ ወታደሮቻችንን ሲያርድና የአገር መከላከያን ሲያፈርስ ሁላችንም ተቆጣን። ታዋቂ የኪነጥበብ ሰዎችና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ከዳር እስከ ዳር ቁጣቸውን ገለጹ። ዝምታን የመረጡም ነበሩ። የአገር ተቆርቋሪነቱ ጥያቄ ውስጥ የማይገባው ቴዲን ብዙዎች ነጠላ ይለቅና የወታደሩን ሞራል ያነሳሳል ብለው ጠብቀውት ነበር። ተስፋ እንዲያደርጉ ምክንያት የሆናቸው “ጥቅመኛ” ነው ተብሎ እስኪወቀስ ድረስ ልዩ ክስተት ሲፈጠር በፍጥነት ዘፈን በማውጣት ቴዲን የሚስተካከለው ባለመኖሩ ነበር። ግን አልሆነም።

በትህነግ ዳግም ወረራ አማራ ክልል ወደ ዓመድነት ሲቀየር፣ በቃላት ሊገለጽ የማይችል አስደንጋጭ፣ ሊታመን የማይችል ግፍ፣ ዝርፊያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ የጅምላ ጭፍጨፋ ሲፈጸም፣ አፋር ክልል ሲወደም፤ ቤተ እምነቶች ሲረክሱ፣ መነኮሳት ሲደፈሩ፣ የምነና ቆባቸውን ጥለው ማቅ ሲለብሱ፣ ጀግኖቹ የኢትዮጵያ ተምሳሌቶች ሲገደሉ፣ ገዳዮቹና ጨፍጫፊዎቹ በገሃድ እየታወቁ የቴዲ ዝምታ ሌላው ጥያቄን የጫረ ጉዳይ ነው።

ወረራውን ለመመከት ከልሒቅ እስከ ደቂቅ፤ ከምሑር እስከ ተማሪ፤ የሕክምና ባለሙያዎች፣ አርቲስቶች፣ በግምባር ለመፋለም ብቻ ሳይሆን ሠራዊቱን ለማነቃቃት በግምባር እየተገኙ ስለ ኢትዮጵያ ሲያዜሙ፣ ወታደሩን ሲያደፋፍሩ፣ ደሙን ሲጠርጉ፣ ቁስሉን ሲያጥቡ፣ ቀለቡን ሲያዘጋጁ፣ ቴዲ “ፍቅር ያሸንፋል” ብሎ ይመስላል ዝምታን ነበር የመረጠው።

ከወረራው በኋላም የግፍ ገፈት ቀማሾችን መልሶ ለማቋቋም ርብርብ ሲደረግ፣ ገንዘብ ሲሰበሰብ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ሕዝብ ሲረዳዳ፣ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች ሳይቀሩ በነጻ ተፈናቃዮችን ወደ አካባቢያቸው እንመልሳለን ብለው ወገናዊነታቸውን ሲያሳዩ ሠንደቋን የሙጥኝ ብሎ በየመድረኩ የሚታየው ቴዲ አንዲት ኮንሰርት አድርጎ ለተፈናቃዮች መርጃ የሚውል ገንዘብ ሲያሰባስብ አለመታየቱ የቴዲ “ኢትዮጵያ” በነጠላ ዘፈኑና በመድረክ ላይ ብቻ ትሆን ያለችው አስብሎናል። አዲስ ያወጣው ዘፈን “ናዕት” ሲያልቅ “መታሰቢያነቱ ላለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች አለአግባብ በግፍ ለተገደሉ፣ አካላቸው ለጎደለ እና ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ንጹሐን ዜጎች በሙሉ ይሁን” ይላል። “መታሰቢያነቱ” ነው የሚለው እንጂ “ገቢው” አላለም!!

“ናዕት” የሕዝብ ጩኸት ነው፤ የሕዝብ ድምፅ ነው የሚሉ እጅግ ብዙዎች ናቸው። እንደ አርቲስትና እንደ ኢትዮጵያዊ ቴዲ የሕዝብን ድምፅ በዚህ መልኩ ማሰማቱ ችግር የለውም። አረንጓዴው አሻራ በሚጀመርበት ቀን መለቀቁና በተለይ ችግኝ ተከላን በግልጽ በመቃወም የተሰነቀረው “ሳር ያለመልማል ዛሬም በእልፍ አእላፍ ሬሳ” የሚለው ስንኝ ግን በርግጥ ዓላማው የሕዝብ ድምፅ መሆን ነው ወይስ በሕዝብ ድምፅ ስም ሌላ ዓላማ ይኖረው ይሆን ብሎ የሚያስጠይቅ ነው። የንጹሐንን በግፍ መገደል መቃወምና መንግሥትንም ተጠያቂ ማድረግ ፍጹም ትክክል ቢሆንም በዚያ ሰበብ ችግኝ ተከላን መቃወም “ሚካኤል ችግኝ ነው። … ችግኝ ይተክላል” ተብሎ በአደባባይ የተወሳውን ጨቅላ ህጻን ከንቱ የመድረክ መጠቀሚያ ማድረግ አይሆንም?

በደርግ ጊዜ ከተከናወኑና እጅግ ከሚያስመሰግኑ ተግባራት ቁንጮውና ዘመን የማይረሳው ድንቅ ተግባር በመሃይመነት ላይ የታወጀው ጦርነት ነው። “መሃይምነት ጥቁር መጋረጃ ነው” በማለት ከገጠር እስከ ከተማ የተሠራው ድንቅ ሥራ ጥቂት የማይባሉ ዜጎችን ለኮሌጅ ሲያበቃ በጣት ይፈርሙ የነበሩ ሚሊዮኖች ግን ስማቸውን በብዕር እንዲጽፉ ያስቻለና ሰብዓዊ ክብራቸውን የመለሰ ነው። ይህ የተደረገው ሕዝብ በጦርነትና በረሃብ እንደ ቅጠል በሚረግፍበት ጊዜ ነው። ቴዲ ለዓቅመ ዘፋኝነት በዚያን ጊዜ ቢደርስ ኖሮ “መሃይምነት ይጥፋ ይላል ዛሬም በሕዝብ ሬሣ” ብሎ ይዘፍን ይሆን? በማለት የሚያስጠይቅ ነው። እንኳንም ያኔ ህጻን ሆነ ያስብላል።    

በመጨረሻም፤ “የአረንጓዴው መሬት” ሃሳብ ባለቤትና የሃሳቡ አቀንቃኝ እስካሁን በተካሄዱት “የአረንጓዴ አሻራ” ችግኝ ተከላዎች በአንዱም እንኳን ሲሳተፍ አለመታየቱ የጤና ነው? ብለን እንድንጠይቅ አድርጎናል። ቴዲ “ሳር ያለመልማል” በማለት በናዕት ውስጥ የሰነቀራትን ስንኝ ከላይ ከጠቀስነው የኢህአፓ ተግባር ጋር በንጽጽር እንድናየው አስገድዶናል። ይህንን የእርሱን አንዲት ስንኝ ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያ የተጀመረውን የችግኝ ተከላ ተቃውሞ ተናብቦ የመሥራት የሰኔ ፕሮጀክት ይሆን ብለን እንድንጠይቅ ገፋፍቶናል? እርሱ ከባለቤቱ ጋር “የአረንጓዴው መሬት” ሃሳብን ሲያራምዱና ችግኝ ሲተክሉ፣ ችግኙ ሚካኤልም እንዲሁ ችግኝ ሲተክል ሕዝብ ይጨፈጨፍ ነበር። የቴዲን የዚያን ጊዜውን ሃሳብ ማንም አልተቃወመም። “ሚካኤል ችግኝ ነው። … ችግኝ ይተክላል” ያለው ቴዲ የሕዝብ ሰቆቃ ድምፅ ነኝ በሚል “ሳር ያለመልማል ዛሬም በእልፍ አእላፍ ሬሳ” ብሎ ቀን ጠብቆ በችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ ዕለት ነጠላ ዜማ መልቀቁን ግን ሚዛን ደፊውን ቴዲ ሚዛን ተደፋብህ አስብሎናል።

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply