የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት :-
– በንጹሐን ዜጐች ላይ የደረሰውን ጭፍጨፋ በጽኑ አውግዟል
– ሕግ የማስከበሩ እርምጃም ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስቧል

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ሰሞኑን በምዕራብ ወለጋ እና በሌሎች አካባቢዎችም በአሸባሪው ሸኔ እና ሌሎች መሰል ተላላኪ ጽንፈኛ ኃይሎች አማካኝነት፣ በንጹሐን ዜጐች ላይ የደረሰውን ጭፍጨፋ በጽኑ አውግዟል፡፡

በአንጻሩም መንግስት የጀመረውን ሕግ የማስከበር እርምጃ አጠናክሮ እንዲቀጥል፤ ምክር ቤቱ በአጽንዖት አሳስቧል፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጭፍጨፋውን ያወገዘው እና ሕግ የማስከበሩ ተግባር እንዲጠናከር ያሳሰበው፤በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሀገሪቱን ፀጥታ ከሚመሩ እና ከምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በስፋት በተወያየበት ወቅት ነው።

የምክር ቤቱ አባላትም በምጣኔ-ሀብታዊ፣ ፖለቲካዊ እንዲሁም በሰላም እና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ በጥልቀት መክረዋል፡፡

በቅርቡ በተለያዩ የሀገራችን ስፍራዎች ማለትም በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በደቡብ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በሌሎችም አካባቢዎች፤ ዜጎች ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ከሞት የተረፉትም ተፈናቅለዋል፤ ለአካል እና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት ተዳርገዋል። ሀብት ንብረትም ወድሟል፡፡ ይህንንም ዕኩይ ተግባር ምክር ቤቱ በጽኑ ያወግዛል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም፤ የምክር ቤቱ አባላት የየራሳቸውን ድርሻ እንደሚወጡ በምክክር መድረኩ አረጋግጠዋል፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፤ በቀጣይ ትኩረት በሚፈልጉ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆነው ችግሩን ለመፍታት እንደሚሠሩም አስታውቀዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችንም በአንድነት ቆመን መሻገር አለብን ብለዋል፡፡

ለሕዝባችን ሕልውና ቀን እና ማታ ከሚለፉ የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የሚሠሩ ተግባራትንም በተመለከተ፤ ሁሉም የምክር ቤቱ አባላት ከሌሎች የመንግስት አካላት ጋር በመሆን በቁርጠኝነት ለመንቀሳቀስ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከውስጥ እና ከውጭ ኃይሎች የተጋረጠብንን የሕልውና ጥያቄ ለመመለስ፤ በመንግስት በኩል የተያዘውን የለውጥ መንገድ ማገዝ እንደሚገባም አስምረዋል።

ለተግባራዊነቱም በትጋት እንደሚረባረቡ የጋራ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡
ስለሆነም በቀጣይ፡-

  1. የዜጎችን የሰላም ችግር በዘላቂነት መፍታት፤
  2. የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እና ብልሹ አሠራሮችን በትጋት መታገል፤
  3. የሕብረተሰቡን የኑሮ ውድነት ችግር ለመፍታት ምርት እና ምርታማነትን ለማረጋገጥ መረባረብ እና ከባለድርሻ አካላት ጋር መሥራት እንዲሁም የክረምት ሥራዎችን በትኩረት ማከናወን የሚሉት ዐበይት አቅጣጫዎች ሆነው ተነድፈዋል፡፡

በተጨማሪም፤ “የተጋረጠብንን የውስጥ እና የውጭ ጥቃት እና ሴራ ለማክሸፍ እና ለማለፍ፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት ቆመናል” ሲሉ የምክር ቤቱ አባላት በአቋም ገልጸዋል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ለጐረቤቶቿ ብሎም ለመላው አፍሪካ የሚተርፍ ብዙ የታሪክ እና የባሕል ብሎም የመልካምነት ትውፊት ባለቤት ናት፡፡ ለጎረቤት ሀገራትም የፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትብብር ተምሳሌት ሆና ቆይታለች፡፡ ይህም የሆነው፤ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን በወንድማማችነት፣ በአብሮነት እና በአንድነት በጽኑ ስለሚያምኑ ነው፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደምትገኝ የምክር ቤቱ አባላት አስታውሰዋል፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ለውጡን መቀልበስ የሚፈልጉ የውስጥ እና የውጭ ኃይሎች ግንባር ፈጥረው የተለያዩ ተግዳሮቶችን ሲፈጥሩ መቆየታቸውንም እንደዚሁ፡፡

ሀገራችን በእነዚህ ጊዜያት በርካታ ፈተናዎች ቢገጥሟትም፤ መንግስት በወሰዳቸው ጠንካራ እርምጃዎች የተነሳ፤ ዓለም-አቀፋዊ እና የሀገር ውስጥ ጫናዎች ያልበገሩት አዎንታዊ ዕድገት በሁሉም መስክ መመዝገቡን አባላቱ በመልካም ጎኑ ገምግመዋል፡፡

ኢኮኖሚው በብዙ ጫናዎች ውስጥ ሆኖም አዎንታዊ ዕድገት ማስመዝገቡን የፓርላማው አባላት አውስተዋል፡፡ እንደዚሁም ገቢ የመሰብሰብ ዓቅማችን መጨመሩ፣ ከወጪ ምርት የምናገኘው የውጪ ምንዛሪ ማደጉ፣ በበጋ ስንዴ ምርት አበረታች ውጤት መመዝገቡ እና የመሳሰሉት መልካም ውጤቶች ቀጣይነት ኖሯቸው እንዲጠናከሩም አበክረው አሳስበዋል፡፡

እንደ ሀገር አሁን እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችን በድል ለመሻገር በተባበረ እና በኢትዮጵያዊ አንድነት መንፈስ መቆም ብቸኛው እና የተሻለው አማራጭ መሆኑን የምክር ቤቱ አባላት አጽንኦት ሰጥተው ተወያይተዋል።

(ኢ ፕ ድ)

Leave a Reply