አሸባሪው ትህነግ ሕዝብ እየሰበሰበ ለዳግም ጦርነት እየተዘጋጀ በመሆኑ ቡድኑን ለማሳፈርና ለማንበርከክ በተጠንቀቅ መጠበቅ እንደሚገባ የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት አስገነዘበ።

የአማራ ክልል ሚሊሻ ያካሄደውን የግዳጅ አፈፃፀምና የቀጣይ የግዳጅ ተልእኮ ዝግጅት በተመለከተ ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ የሚሊሻ መሪዎች በባሕርዳር መክረዋል። ምክክሩ አንድ የጋራ ግንዛቤ በመፍጠር ለቀጣይ ለሚኖር ተልዕኮ ለመዘጋጀት እና ተልዕኮን በአግባቡ ለመወጣት ያለመ ነው።

ምክክሩን የመሩት የአማራ ክልል ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኮሎኔል ባምላኩ ዓባይ አሸባሪው ሕወሃት በከፈተው ጦርነት ሚሊሻው ሰፊ ተጋድሎ ማድረጉን ገልጸዋል። አሁን ለዳግም ወረራ እየተዘጋጀ በመኾኑ ሚሊሻውን ዝግጁ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑ ድጋሜ ወረራ ቢፈጽም ለመደምሰስና እልባት ለመስጠት ሚሊሻው ዝግጁ ነው ብለዋል። ሚሊሻው ቤትና ንብረቱን ጥሎ ግንባር በመዝመት ጀብድ ፈጽሟል፣ ጠላትን ደምስሷል ነው ያሉት። ነፃ ባልወጡ ወረዳዎች ዜጎች ከፍተኛ በደል እየተፈፀመባቸው መኾኑንም አንስተዋል። ጠላት በተደጋጋሚ ትንኮሳ እያደረገ በሚሊሻውና በሌሎች የፀጥታ ኀይሎች እየተመታ እንደኾነም ነው የተናገሩት።

ሚሊሻው በክልሉ እየተካሄደ ባለው የሕግ ማስከበር ሥራ ከፍተኛ ሥራ እየሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል።

የሚሊሻው አደረጃጀት የጠበቀና መንግሥት የሚሰጠውን ግዳጅ ለመወጣት ዝግጁ መኾኑንም ገልጸዋል።

ጠላት ሕዝብ እየሰበሰበ ለዳግም ጦርነት እየተዘጋጀ መኾኑን ያነሱት ኮሎኔል ባምላኩ ይህን አሸባሪ ቡድን ለማሳፈርና ለማንበርከክ በተጠንቀቅ መጠበቅ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

መንግሥት ለሰላም ቅድሚያ እንደሚሰጥ የተናገሩት ኮሎኔል ባምላኩ የሽብር ቡድኑ ለሰላም ዝግጁ ስላልኾነ ጦርነት ከከፈተ በተጠንቀቅ መቆም ይገባል ነው ያሉት።

የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኮማንደር አዳሙ ይሁን የሚሊሻ ኀይሉ ሀገርና ሕዝብ በፈለገው ጊዜ ተነስቶ መስዋእትነት በመክፈል ሀገር ማጽናቱን ገልጸዋል። በቀጣይም ለሚጠበቅበት ግዳጅ ዝግጁ መኾኑን ነው የተናገሩት። ሚሊሻው በብሔረሰብ አስተዳደሩ በሚገባ ሕግ እያስከበረና ሥርዓት አልበኝነትን እያስቆመ መኾኑን ነው የገለጹት። ሊፈጠር ለሚችል ትንኮሳ መልስ ለመስጠት ሚሊሻው በቂ ዝግጅት አድርጓልም ብለዋል።

የዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሙሉ ማሞ በብሔረሰብ አስተዳደሩ የሚሊሻውን አቅም ከፍ በማድረግ ከሌሎች የፀጥታ ኀይሎች ጋር እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ካለፈው ትምህርት በመውሰድ ሊቃጣ የሚችልን ጥቃት ለመመከት ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት። ለጠላት ስንቅ የሚያቀብሉና ከጠላት ጋር የሚላላኩትን በመያዝ ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን የሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዘውዱ መኮንን ሚሊሻው በስልጠና ታግዞ ዝግጅት ማድረጉን አስረድተዋል። ሚሊሻውን መምራት የማይችሉ መሪዎችን ማስተካከል እና ብቁ እንዲኾኑ የማድረግ ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል። የሕግ ማስከበር ሥራም በዞኑ እየተከናወነ እንደኾነ አንስተዋል። የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት በመጠበቅ ረገድ የሚሊሻው ሚና ላቅ ያለ እንደኾነም ገልጸዋል።

(አሚኮ)

Leave a Reply