የግብጹ ፕሬዚዳንት አል ሲሲ፣ የሱዳኑ አል ቡርሃን እና የደቡብ ሱዳኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ሬክ ማቻር በፖለቲካዊ መድረክ መቀራረብና መመሳጠር ከጀመሩ ሰንበትበት እንዳሉ ከዚህም አልፈው ከባልካን ሀገራት እስከ ምሥራቅ አፍሪካ የተዘረጋ ህገወጥ የጦር መሣሪያ ንግድ ሰንሰለት አንደሚያቀነባብሩና እንደሚመሩ  የሚያሳይ ምስጢራዊ መረጃ ሰሞኑን  ይፋ ተደርጓል፡፡

 የቀጣናውን ጂኦፖለቲክስ ጉዳዮች በቅርበት  በሚከታተሉ ምንጮች  የተገኘው ምስጢራዊ መረጃ እንደሚያስረዳው፤ የሶስቱ ሀገራት አመራሮችና ወኪሎቻቸው  በዚህ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እጃቸውን ያስገቡት በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ነው፡፡ በዋናነት በምስራቅ አፍሪካ የተረጋጋ ማዕከላዊ መንግሥት መመስረት ያቃታቸው የሁለቱ ሱዳን አመራሮች በቀጣናው የፀጥታ ችግሮችን በማስፋፋት ግጭትን እንደ ስልጣና ማራዘሚያ ስልት ለመጠቀም በጦር መሳሪያ ዝውውሩ በስፋት የሚሳተፉ መሆኑ ታውቋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ህገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውሩ የሶስቱን አመራሮች  የገንዘብ አቅም በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ ߵߵበአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍߴߴ  የሚል ስውር አላማ እንዳለው ተደርሶበታል፡፡

ሸኔ፣ ህወሓት እና የጉሙዝ ታጣቂዎች  ከግብጽ መንግሥት በቀጥታ  የሚያገኙት የመሣሪያና የሎጀስቲክስ ድጋፍ በዚህ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ሰንሰለት አማካኝነት እንደሚተላለፍም በመረጃው ተጠቁሟል፡፡

መሣሪያዎቹ ለጊዜው ስማቸው እንዲገለጽ ካልተፈለጉ የባልካን  ሀገራት በቀጥታ ተገዝተው በአል ሲሲ ልዩ መልእክተኞች አማካኝነት የሬከ ማቻር ታማኝ ታጣቂዎች ወደሚንቀሳቀሱባቸው የደቡብ ሱዳን አካባቢዎች ከተሸጋገሩ በኋላ ለተለያዩ የሽብር ቡድኖቹም እንዲደርሱ እየተደረጉ መሆኑ ታውቋሉ።  የሸኔ ሽብር ቡድንም በዚህ ሰንሰለት አማካኝነት የሚዘዋወረውን ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ በስፋት ከመጠቀም አልፎ በቀጣናው ለሚንቀሳቀሰው የአልሸባብ የሽብር ቡድን ለማስተላለፍ  ፍላጎት እንዳለው የሚያሳዩ መረጃዎችም መገኘታቸውን ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡

ሰሞኑን ታዋቂው ግብጻዊ  ፖለቲከኛ አይማን አብድልአዚዝ ኑር በአንድ ስብሰባ ላይ ባስተላለፈው መልዕክት  ߵߵኢትዮጵያ ውስጥ ኤምባሲ አያስፈልገንም ይልቁንም የሚያስፈልገን በፖለቲካ እና በደህንነት ጉዳዮች ላይ የሚሰራ ግብረ ኃይል ነው። እኔ እንደማስበው ስጋታችንን ለመቀልበስ በጣም አዋጭና በትንሽ ዋጋ የምንጠቀምበት አማራጭ ይህ ነው፤ በኢትዮጵያዊያን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ሀገሪቱን ማተራመስ አለብንߴߴ   ማለቱን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት  መዘገቡ ይታወሳል፡፡

የዚህ አይነት ይዘት ያለው ሃሳብ በተደጋጋሚ ከግብጽ ፖለቲከኞች የሚሰነዘር ሲሆን፤ የሀገሪቱ መንግሥትም አቋም ከዚህ የተለየ እንዳልሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄዱ የንጹሀን ግድያዎች በአሸባሪዎቹ ሸኔ እና ህወሓት ቢፈጸሙም በዋናነት ከእነዚህ ሴራዎች ጀርባ የውጭ ሀገራት እጅ እንዳለበት፤ በተመሳሳይም ሱዳን የፈጸመችው የድንበር ወረራና ትንኮሳ የሶስተኛ ሀገር አጀንዳን ለማስፈጸምም እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡

Leave a Reply