“በብሄር ወስደውታል፤ የሚለውን ወሬ አምነው ቁጠባቸውን ያቋረጡ እንዳሉ ሁሉ፤ የጸኑ የዛሬው ባለእድል ለመሆን በቅተዋል”

የተለያየ የሃሰት ፕሮፓጋንዳዎችን አምነው ቁጠባቸውን ያቋረጡ እንዳሉ ሁሉ፤ ታጋሾች ፅኑዓን ለዛሬው ባለእድለኝነት በቅተዋል!!
ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአሁኑ ሰአት የላለፉት አመታት ሲያስገነባቸው ከቆዩት ቤቶች ውስጥ በዛሬው እለት በ20/80 18,648 ቤቶችን፣ በ40/60 3ኛ ዙር 6,843 በአጠቃላይ 25,491 የጋራ መኖሪያ በእጣ ማውጣት ስነስርዓቱ እያካሄደ ይገኛል፡፡

በዚህ ስነስርዓት ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደገለፁት ለረጅም ዓመታት ገንዘባችሁን እየቆጠባችሁ የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን በጉጉት እየተጠባበቃችሁ ለከረማችሁ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

እንደ ከንቲባ አዳነች አቤቤ‹‹አገራችን ኢትዬጵያ በበርካታ ችግሮችና መሰናክሎች ውስጥ የቆየችና ያለች ብትሆንም፤ ለአፍታም ቢሆን ከልማታችን ሳንዘናጋ በአንድ እጃችን ልማታችንን፤ በሌላው ደግሞ ሰላማችንን እና ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን ለማስጠበቅ ጠንክረን ለመስራት በገባነው ቃል መሰረት በፅናት እየተጋን እንገኛለን፡፡›› ብለዋል፡፡

እንደ ከንቲባዋ አገላለፅ ከ2011 ጀምሮ በግንባታ ላይ የነበሩ ከ139ሺ በላይ ቤቶች ሲሆኑ ከ21.57 ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ መሰረታዊ ስራዎች በማጠናቀቅ 96.918 ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ቁልፍ ለማስረከብ ከዚህ ውስጥ ለ54ሺ በላይ ባለዕድለኞች ቁልፍ እንዲረከቡ መደረጉን ገልፀው የቀሩትም መጥተው ቁልፋቸውን እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች በዚህ ወቅት እንደገለፁት እነዚህን ቤቶች እዚህ ደረጃ ለማድረስ ብዙ ውጣ ውረዶችን መታለፉንና፤‹‹ መታገስ አቅቷቸውና በማህበራዊ ሚድያ ዘመቻ ፕሮፓጋንዳዎች ቤቶቹ አመራሩ ተከፋፍለዋል በብሄር ወስደውታል፤ የሚባለውን ወሬ አምነው ቁጠባቸውን ያቋረጡ እንዳሉ ሁሉ፤ ታጋሾች አመዛዛኞችና ፅኑዓን ለዛሬው ባለእድለኝነት በቅተዋል፡፡ ይህ ለወቅቱ የሃገራችን ሁኔታ ጥሩ መማርያ ይሆናል፡፡›› ሲሉም ገልፀዋል፡፡

አስተዳደሩ የቤት ክፍተቱን ለመሙላት የተለያዩ አማራጮችን እየተጠቀመ መሆኑን ገልፀው፤-የ5ሺህ ተገጣጣሚ ቤቶችን ፤የ10ሺህ ምንም ገቢ የሌላቸው ዜጎች የሚሰሩ ቤቶችን ጨምሮ የመኖሪያ ህብረት ስራ ማህበራትን በማደራጀ፣ በመንግስትና በግል ባለሀብቶች አጋርነት (Public Private Partnership)፣ . በሽርክና የመኖሪያ ቤት ማልማት (Joint Venture)፣ በሪል ስቴት እና በግል ቤት አልሚነት የተለያዩ የቤት ልማት አማራጮችን በመጠቀም የከተማውን ነዋሪ ባስቀደመ መልኩ መጠነ ሰፊ ስራዎች በመካሄድ ላይ እንደሚገኙም ገልፀዋል፡፡

See also  የኩሪፍቱ ሪዞርት ባለቤት "ያፈነኝ የለም፣ ሰላም ነኝ" አሉ

የሚተላለፉትን ቤቶች ከአድልዎ ነጻ ለማድረግና የቤት እጣ ማውጫ ሲስተም በአዲስ ተግባራዊ መደረጉን የገለፁት ከንቲባ አዳነች ከእጣ አወጣጥ ስነስርዓቱ በኋላ ምንም አይነት ጥቆማ ካለ ኦዲት የሚደረግና በገለልተኛ አካል የሚጣራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ያስሚን ወሃቢረቢ በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት አመታት በቤት ፕሮግራም ከ300ሺህ በላይ ቤቶችን ሰርቶ ማስረከቡንና ይህም በስራ እድል ፈጠራና የተጎሳቆሉ አካባቢዎችን በመቀየር የራሱ ሚና እንደነበረው ገልፀዋል፡፡

የባለሶስት መኝታ ቤት በተመለከተም ባለፈው ዙር ዋጋውን እስከ 1500 ቁጠባ ድረስ በማውረድ በማስተናገድ የቤቶች ቦርድ ፕሮግራሙን መዝጋቱን አስታውሰው ፤በዚህ ዙር ለማስተናገድ አጠቃላይ ሲስተሙን የሚያዛባ በመሆኑ በቀጣይ በልዩ ሁኔታ የሚታይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አቶ ሽመልስ ታምራት የአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው በ20/80 የቤት ልማት ፕሮግራም 27,195 እና 40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም 52,599 በአጠቃላይ 79,794 ተመዝጋቢዎች ለዕጣ ብቁ ሆነው በዚህ ዙር ዕጣ እንዲካተቱ መደረጉን ገልፀው በ20/80 ፕሮግራም የሚካተቱት የ97 ተመዝጋቢዎች ብቻ መሆናቸውንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

Mayor office

Leave a Reply