የማንነት አስተዳደር ወሰን እና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ የወልቃይት ጠገዴና የራያ የማንነት ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ እየሠራሁ ነው አለ።

የፌዴሬሽን ምክርቤት የማንነት አስተዳደር ወሰን እና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ የ2014 በጀት ዓመት ለመስራት ካስቀመጣቸው እቅዶች ውስጥ በማንነት አስተዳደር ወሰን እና ራስን በራስ ለማስተዳደር የሚቀርቡ አቤቱታዎችን አጣርቶ በመመርመር ለምክር ቤቱ ምክረ ሀሳብን ማቅረብ የሚለው ይገኝበታል።

በዚህም ለምክር ቤቱ ቀርበው ሲጠየቁ የነበሩ የማንነት ይታወቅልኝ እና ማንነታችን ይከበርልን፣ የመካለል ጥያቄ፣ ራስን በራስ የማስተዳደር እና የመዋቅር ጥያቄዎች መረጃን የማጥራት ሥራ ማከናወኑን አስታውቋል።

ባለፈው አንድ ዓመት መረጃን የማጥራት ሥራ መስራቱን የጠቀሰው ቋሚ ኮሚቴው ከዘጠኝ ክልሎች 30 አቤቱታዎች እንደቀረቡለትም ገልጿል።

ከእነዚህ ውስጥ የራያ ጉዳይ እንደሚገኝበትና ለመፍትሔው ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር በመተጋገዝ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቁሟል።

ከቀረቡት ውስጥ ስድስቱ የማንነት ይታወቅልኝ ሲሆኑ የመካለል እና መዋቅር ጥያቄዎች ደግሞ 24 መሆናቸውን ጠቅሷል።

የወልቃይት ጠገዴን ጉዳይ መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ አጀንዳ አድርጎ በመወያየት አቅጣጫዎችን የማመላከት ሥራዎች እየሠራ መሆኑን በመጥቀስም፤ ቀሪ
ሥራዎችን በማጠናቀቅ የውሳኔ ሀሳብ መሉ በሙሉ እንደተጠናቀቀ ለምክር ቤቱ እንደሚቀርብም ነው የገለጸው።

አቤቱታዎችን ለማጣራት እና ለመመርመር ይረዳ ዘንድ ቀድም ብሎ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ተለይተው ለአስተዳደር ወሰን እና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን የተላኩ 27 ልዩ ልዩ ጉዳዮች ኮሚሽኑ የደረሰበትን የጥናት ደረጃ ለመገምገም የጋራ ምክክር መደረጉንም አመላክቷል።

በተጠናቀቀው በጀት አመት የተለዩት 5 የማንነት፣ 18 የመካለል፣ 3 የወሰን ይቁምልን ውዝግብ እና አንድ የውክልና በድምሩ 27 ለኮሚሽኑ የተላኩ ጉዳዮችን መነሻ በማድረግ የጥናት ውጤት ላይ ተመስርቶ ኮሚሽኑ ምክረ ሀሳቦችን ማቅረብ ቢኖርበትም የስራ ጊዜውን ማጠናቀቁን ተክትሎ የጥናቱ ውጤት ለምክር ቤቱ ማስረከቡም ተገልጿል፡፡

በደቡብ ክልል ያሉ የተለያዩ የመዋቅርና የክልልነት ጉዳዮችን እየተመለከተ መሆኑን ያነሳው ቋሚ ኮሚቴው በክልሉ የሚነሱ ሌሎች የተለያዩ አደረጃጀት ጥያቄዎች፥ ሕዝቡ በየትኛው መልኩ ቢደራጅ የተሻለ ተጠቃሚ ይሆናል የሚለውን ውሳኔ ተከትሎ የሚመጣ ነው ተብሏል በሪፖርቱ።

ምክር ቤቱ ይህን እና ሌሎች የቋሚ ኮሚቴውን የሥራ አፈፃፀም ሪፖርተር አድምጦ በሶስት ተቃውሞ እና በአብላጫ ድምፅ ማጽደቁን ፋብኮ ዘግቧል።(አሚኮ)

Leave a Reply