በመቄት ወረዳ በጦርነት ወቅት ጉዳት የደረሰባቸው ቤቶችን መልሶ ለመገንባት የተደረገው ጥረት በቂ ባለመሆኑ በዝናብ ወቅት መቸገራቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በወረዳው ደብረ ዘቢጥ፣ ዳንዴ በር እና አርቢት ቀበሌዎች የሚገኙ ቤታቸው በጦርነት የፈረሰባቸው ነዋሪዎች ጉዳት የደረሰበት ቤታቸውን ለመሸፈን የሚያገለግል የሸራ ልባስ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።

ይህ ግን የቤታቸውን ጣሪያ ለመሸፈን ከክረምቱ ዝናብና ነፋስ ጋር ተያይዞ አመች እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ቤታቸው ሙሉ በሙሉ የፈረሰባቸው ነዋሪዎች ደግሞ ከሞቀ ኑሯቸው ወጥተው አቅማቸው የሚፈቅድላቸው በኪራይ ቤት የማይፈቅድላቸው ደግሞ በጥገኝነት ውስጥ እንደሚኖሩም ገልጸዋል።

በ2013/2014 የምርት ዘመን በጦርነቱ ምክንያት ሳያመርቱ መክረማቸው አሁን ላይ ካለው የቤት ክዳን ቆርቆሮ ዋጋ መጨመር ጋር ተዳምሮ በራስ አቅም ቤታቸውን ለመጠገን አስቸጋሪ እንደሆነባቸውም ተጎጅዎች አንስተዋል።

ቤታቸው ውስጥ ዝናብ እየገባ ክረምቱ ፈታኝ እንደሆነባቸው የገለጹት ተጎጅዎች መንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ተቋማት እና ሀገር ወዳድ ባለሃብቶች ከጎናቸው እንዲቆሙ ጠይቀዋል።

የመቄት ወረዳ አስተዳዳሪ አሰፋ ይልማ በወረዳው ውስጥ ከ6 ሺሕ 200 በላይ የግለሰብ ቤቶች በጦርነት ምክንያት ቀላልና ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።

በጦርነት የፈረሱ ቤቶችን መልሶ የመገንባት ሥራው በበቂ ሁኔታ እየተካሄደ እንዳልሆነም ተናግረዋል። ቤታቸው ከፈረሰባቸው ሰዎች መካከል በራሳቸው አቅም እና በሀገር ወዳድ ግለሰቦች እገዛ ጥገና ያደረጉ ቢኖሩም አብዛኛው የጉዳቱ ሰለባዎች ግን አሁንም ድረስ ቤታቸው ሳይጠገን በመቅረቱ በክረምት ወቅት የመጠለያ ችግር እንደገጠማቸው ገልጸዋል።

መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ባለሃብቶችም በደረሰው ጉዳት ከማዘን በዘለለ በቂ የሆነ ተግባራዊ የእርዳታ እንቅስቃሴ አላሳዩም ማለታቸውን አሚኮ ነው የዘገበው።

Leave a Reply