“የክልልነት ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኙ ከመንቀሳቀስ ይልቅ ጉዳዩን የአመጽና የሁከት መነሻ ለማድረግ በሚሞክሩ አካላት ላይ እርምጃ ይወሰዳል-የፌዴራል የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል

“የክልልነት ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኙ ከመንቀሳቀስ ይልቅ ጉዳዩን የአመጽና የሁከት መነሻ ለማድረግ በሚሞክሩ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ የፌዴራል የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡

የፌዴራል የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ መንግሥት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በተለያዩ ጊዜያት የሚነሱ የክልልነት ጥያቄዎችን በሀገሪቱ ሕግና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየሠራ ይገኛል፡፡

ነገር ግን አንዳንድ አካላት ይህንን ሂደት በሚቃረን መንገድ ሕጋዊ ጥያቄዎችን ሽፋን በማድረግ ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር በህቡዕ ዝግጅት ማድረጋቸውን የጋራ ግብረ ኃይሉ ባደረገው ክትትል ስለተደረሰበት ተገቢው እርምጃ ይወሰዳል ነው ያለው፡፡

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግሥት በስሩ የሚገኙ ዞኖችን በአዲስ መልክ ለማዋቀር እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

ጌዲኦም በአዲስ መልክ ከሚዋቀሩ ዞኖች አንዱ ሲሆን÷ የኅብረተሰቡን ተሳትፎ በተጨባጭ ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ ሰሞኑን የማወያያ ሰነዶች ተዘጋጅተው የዞኑ ነዋሪ እየመከረበት መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

ይሁንና የጌዲኦ ዞን የክልልነት ጥያቄ መፍትሔ የማይሰጠው ከሆን ጥያቄያችንን በኃይል እናስፈጽማለን የሚሉ አካላት በህቡዕ ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የፌዴራል የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል በተጨባጭ መረጃዎች መረጋገጡ ነው የተገለጸው፡፡

በህቡዕ የተደራጁት አካላት የጥፋት እቅዶቻቸውን ለማሳካት ሀሰተኛ የማህበራዊ ትስስር ገጾች በመክፈት የተዛቡና የፈጠራ መረጃዎችን እያሰራጩ መሆኑን ያመለከተው የጋራ ግብረ ኃይሉ መግለጫ÷ ማኅበረሰቡንም በተሳሳቱ መረጃዎች ለማደናገር እየሞከሩ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

እነዚህ አካላት ያደራጇቸው ግለሠቦችና ቡድኖች ቤት ለቤት ጭምር እየተንቀሳቀሱ ቅስቀሳ እያደረጉ እንደሚገኙ ይህም በደኅንነትና በጸጥታ አካላት እንደተደረሰበት አመልክቷል፡፡

የጋራ ግብረ ኃይሉ ለዚህ እኩይ ዓላማ የተደራጁና የተሰለፉ ግለሠቦችንና ቡድኖችን በደኅንነትና በጸጥታ መዋቅሩ አማካኝነት ለይቶ ክትትል እያደረገባቸው መሆኑን በማስገንዘብ÷ ከጥፋት ተልዕኳቸውም እንዲቆጠቡ በጥብቅ አሰስቧል፡፡

ይህን ተላልፈው በሚገኙ ላይም ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፡፡

አብዛኛው የዞኑ ኅብረተሰብ የጥፋት ተልዕኮ ያነገቡ አካላት ህቡዕ እንቅስቃሴ ተገቢ አለመሆኑን በማመን ለጸጥታና ደኅንነት አካላት ጥቆማ በመስጠት የሁከትና ብጥብጥ ተልዕኮው እንዲከሽፍ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን መግለጫው አንስቷል፡፡

በቀጣይም ከእንደዚህ አይነት የጥፋት ሴራ እራሱን በማቀብ አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከት ለመንግሥት አካላት መረጃ በመስጠት የአካባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ የጋራ ግብረ ኃይሉ ጠይቋል፡፡

OBN

Leave a Reply