በአማራ ክልል የተጀመረው መካናይዜሽን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ግብርና ቢሮ አስታውቋል።

መካናይዜሽን የእርሻ መሳሪያዎችንና ቴክኖሎጅዎችን ተጠቅመን ምርትና ምርታማነትን የምናሳድግበት ዘዴ ነው ብሏል ቢሮው።

በክልሉ ከባለፉት ዓመታት በተሻለ መንገድ በዚህ አመት ለመካናይዜሽን የተሰጠው ትኩረት የሚደነቅ መኾኑንም ቢሮው ገልጿል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ብዙ የደከመበት ሥራ ከሆኑት አንዱ መካናይዜሽን እንደሆነ እና በተለይ የፋይናንስ ስርዓቱን ለማስተካከልና ምቹ ለማድረግ በተደረገው ጥረት 30 ሚሊዮን ዶላር ለመካናይዜሽን ተመድቧል።

ከሰሞኑ የቢሮው አመራሮችና ባለሙያዎች የክረምት የግብርና ስራዎች ሲገመግሙ አንዱ የትኩረት ማዕከል መካናይዜሽን ነበር።

“በአማራ ክልል የመካናይዜሽን አብዮት ተጀምሯል፤ መዳረሻችን ደግሞ ቴክኖሎጅ የሚጠቀም አርሶ አደር ፈጥረን፤ ምርትና ምርታማነትን አሳድገን በምግብ ራስን መቻል ነው” ያሉት የግብርና ቢሮ ኀላፊ ኀይለማርያም ከፍያለው (ዶ/ር) አሁን ያለውን መልካም አጋጣሚ መጠቀም በየደረጃው ያለ አመራርና ባለሙያ ድርሻ ነው ብለዋል።

ለሚቀጥሉት አምስት አመታት በባለሀብቱ፣ በድርጅቶች፣ በማህበራት፣ በመንግስትና በአርሶ አደሩ የሚሟሉ ተብለው የታቀዱትን ከፌደራል ጀምሮ እስከ ታች ቀበሌ ድረስ ባለድርሻ አካላትን ማወያየታቸውንም ዶ/ር ኀይለማርያም ጠቁመዋል።

በቀጣይ አምስት አመት ከ26ሸ በላይ የእርሻ ትራክተር እና 300 ኮምባይነር ለማስገባት እንደታቀደ ገልፀዋል።

ከሶስት ወር በኋላ ደግሞ አንድ ሽህ ትራክተር ወደ ክልሉ እንደሚገባ ዶ/ር ኀይለማርያም ከፍያለው ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ለሚቀጥለው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የሚሆን ከ6ሽ በላይ ሞተር ፓምፕ እንደሚመጣ ገልፀዋል።

ቢሮው በማህበራዊ ትስስር ጉጹ ባወጣው መረጃ፤ እነዚህን ሁሉ መልካም አጋጣሚዎችና ዕድሎች መጠቀም ያስፈልጋል ያሉት ኀላፊው፤ የተጀመረው የመካናይዜሽን ማስፋፋት ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል በመኾኑ የአርሶ አደሩን የቁጠባ ባህል ማሳደግና ፍላጎት መፍጠር ወሳኝ ተግባር ስለመሆኑ አስገንዝበዋል።

(አሚኮ)

Leave a Reply