የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሶስተኛ ሰበር ችሎት ሐሰተኛ ቃለ-መሐላ አቤቱታ ያቀረቡ ባለጉዳይን በችሎት መድፈር እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላለፈ፡፡

አቤቱታ አቅራቢ ባለጉዳዩ ሐምሌ 27 ቀን 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት ጥፋተኛ ናቸው በማለት በአንድ ወር ከአስራ አምስት ቀን ቀላል እስራት እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በእስራት እንዲቀጡ የወሰነባቸው አቶ ኃይለማርያም ወዳጆ በደሀ ደንብ መስቀልኛ የሰበር አቤቱታ ለማቅረብ የዳኝነት ለመክፈል ምንም ሀብት እና ንብረት የሌላቸውና በቀበሌ ቤት የሚኖሩ መሆኑን በቃለ-መሐላ በማረጋገጥ አቤቱታቸውን በሀሰተኛ መንገድ በማቅረባቸው ነው ተብሏል፡፡

ሆኖም ግን የግለሰቡ ተከራካሪዎች ለችሎቱ ባቀረቡት አቤቱታ ግለሰቡ በስር ፍርድ ቤት እስከ ክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ የዳኝነት ከፍለው ሲከራከሩ የነበረ መሆኑን እና አሏቸው ያላቸውን ሀብትና ንብረት ጠቅሰው በችሎቱ እንዲጣራላቸው ጠይቀዋል።

ግለሰቡ ቀድሞ ባቀረቡት የቃለ-መሐላ አቤቱታ መሠረት በስማቸውም ሆነ በባለቤታቸው ስም የተመዘገበ ምንም ዓይነት ሀብትና ንብረት እንደሌላቸው ለችሎቱ ማረጋገጣቸውን ችሎቱ በግለሰቡ ላይ ከሰጠው የጥፋተኝነት ውሳኔ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ስለግለሰቡ ሀብትና ንብረት አጣርቶ እንዲያቀርብ የታዘዘው የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከላይ በተመለከተው አግባብ ግለሰቡ በስማቸው የተመዘገበ መኖሪያ ቤት ያላቸው መሆኑን እና በመጠጥ ችርቻሮ ንግድ ስራ ላይም በመስራት ላይ የሚገኙ ስለመሆኑ ለፍርድ ቤቱ ማረጋገጡን የችሎቱ ውሳኔ ያስረዳል፡፡

ግለሰቡ ሀብትና ንብረት ያላቸውና በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ቢሆንም ምንም ዓይነት ንብረት እንደሌላቸው በቃለ-መሐላ አቤቱታ አረጋግጠዋል።

ግለሰቡ ችሎት ቀርበው በተጠየቁበት ወቅት በተመሳሳይ ሁኔታ መናገራቸው ሆን ብለው ሀሰተኛ ፍሬ ነገርን ለችሎት መግለጻቸውን የሚያረጋግጥ መሆኑም በውሳኔው ላይ ተመልክቷል፡፡

ይህ ደግሞ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህግ ቁጥር 481 እና የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 452 መሰረት የወንጀል ክስ ማቅረብ ሳያስፈልግ በቀጥታ በወንጀል ሊያስቀጣ የሚችል መሆኑም ተመልክቷል።

ለመልካም ችሎት አመራር ተቃራኒ የሆነ በፍትህ ስራ ላይ ሊደረግ የሚገባው በእውነተኝነት እና በታማኝነት ተግባር ላይ የሚፈፀም የወንጀል ተግባር መሆኑንም ችሎቱ በውሳኔው ላይ ዘርዝሯል፡፡

ግለሰቡ ጥፋተኛ በተባሉበት የወንጀል ህግ አንቀፅ ስር ያለው ቅጣት ከአንድ ዓመት የማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ድርጊቱ የተፈፀመው በወንጀል ክስ ሂደት በሆነ ጊዜ ከሶስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣ ተገልጿል፡፡

ከተፈፀመው ድርጊት አኳያ ግለሰቡንም ሆነ ሌሎች መሰል ድርጊት ለመፈፀም ሀሳብ ያላቸውን ሰዎች ያስተምራል ያስጠነቅቃል በማለት ለችሎቱ ሐሰተኛ ቃለ-መሐላ አቤቱታ ያቀረቡት አቶ ኃይለማርያም ወዳጆ በአንድ ወር ከአስራ አምስት ቀን ቀላል እስራት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል፡፡

(ኢዜአ)

Leave a Reply