አስር ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ እንዲሆኑ ተውሰነ

በመጪው መስከረም ራስ ገዝ የሚሆነውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ሳይጨምር በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታትም 10 ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ለማድረግ መንግሥት አቅጣጫ ማስቀመጡን ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት 10 ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ እንዲሆኑ መንግሥት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

ትግበራው ለትምህርት ጥራት፣ በተቋማቱ መካከል የትብብር እና የፉክክር መንፈስ በማምጣት ልሕቀትን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ጠቁመው፤ በዚህ ምክንያትም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲን ዕውን ለማድረግ ይረዳል ብለዋል፡፡

እንደ ዶክተር ሳሙኤል ገልጻ፤ ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ሲሆኑ ተወዳድረው ከውጭም ሀብት ያገኛሉ፡፡ ከአገር

ውስጥ ከንግዱም ማኅበረሰብ በምርምርና በማማከር ገቢ ያስገባሉ። ብቁ ተማሪ ስለሚያወጡ ከመንግሥትም ተጨማሪ በጀት ያገኛሉ። ውድድሩ ልህቀት ያመጣል። የትምህርት ልህቀት በአገር ውስጥ አይገደብም። በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ተቋም መፍጠር ይቻላል።

ለመምህራኖቹ የተሻለ የደመወዝ ክፍያ እና ጥቅማ ጥቅም አሟልተው እንዲቀጥሩ የሚያስላቸው እንደሚሆን ጠቁመው፤ ለሚቀጥሯቸው መምህራን እንደ አቅማቸው የሚከፍሉበት ዕድል ይሰጣቸዋል። ምሁራኖቹ በምርምር፣ በማኅበረሰብ አገልግሎት፣ በማስተማር፣ የጥናት ጽሑፎች በማዘጋጀት ከውጭ በሚያስገኙት ሀብት መሠረት አድርገው እንደልፋታቸው እንዲከፈላቸው ያስችላል ሲሉ ገልፀዋል።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደርግ ከንጉሡ ሲረከበው ነፃ ተቋም ነበር። ንጉሡ ካልፈቀዱ ፖሊስ ወደ ጊቢው ለመግባት አይችልም ነበር። 1969 ዓ.ም ደርግ ስልጣን ከያዘ ጥቂት ዓመታት በኋላ የከፍተኛ ትምህርት ኮሚሽን የሚል አዋጅ ወጥቶ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኮሚሽኑ ስር መግባቱን ተከትሎ አሠራሩ መቀየሩን አስታውሰዋል። መሪውን የሚወስነው መንግሥት እንደነበረም ነው የጠቆሙት።

አሁን ወደነበረበት ልምዱ ሲመለስ ሰፊ ትምህርት ይወሰድበታል ያሉት ዶክተር ሳሙኤል፤ በቀድሞው ነፃነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሩ ፕሮፌሰሮች ጡረታ የወጡ በሥራ ላይ ያሉትንም በመጠቀም እስከ መስከረም 2015 ዓ.ም ዩኒቨርሲቲውን ነፃ በማድረግ ልምዱን በመቀመር ወደሌሎቹ ዩኒቨርሲቲዎች እናሰፋለን ብለዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው አገላለጽ፤ አሠራሩ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብቻ የሚተገበር አይደለም። መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት 10 ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ ሆነው እንዲወጡ ይደረጋል።

‹‹በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ ተቋም መፍጠር ያስፈልጋል። ዩኒቨርሲቲን በሰፈር አጥረነው መቀጠል የለብንም። ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ በመሆኑም ራስ ገዝነት በጣም ወሳኝ ነው›› ብለዋል።

የሥርዓት ግንባታ የትምህርት ሥርዓትንም እንደ አዲስ ሊመለከተው እንደሚገባ ይታመናል። ትምህርት ተቋማት በራሳቸው ብቃት እንዲኖራቸው ደግሞ ነፃነት ወሳኝ ነውያሉት ዶክተር ሳሙኤል፤ በዚህ ሃሳብ መሠረት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሀብትን በማስተዳደር፣ የራሳቸውን የወደፊት አቅጣጫ የመወሰን ነፃነት እንዲኖራቸው ራስ ገዝ ሆነው ይቀጥላሉ ሲሉ ገልጸዋል።

የትምህርት ተቋማት ፕሮፌሰሮችና ዶክተሮች ያሉበት መሆኑን ያስታወሱት ዶክተር ሳሙኤል፤ ሚኒስትር ዴኤታ የሚባሉ ካድሬዎች ብቻ እየመሯቸው አገር የሚያሻግር ትልቅ ነገር መፈጸም ስለማይችሉ በአገራዊ ፖሊሲው መሠረት ራስ ገዝ ተቋማትን መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።

ነፃ ተቋማት ሲፈጠሩ የትምህርት ጥራትን ለማምጣት ይጠቅማል። ተቋማቱም የከፍተኛ ትምህርት ተፈትነው ውጤት ይዘው ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡትን እንደገና ፈትነው ሊቀበሏቸው የሚያስችል ነፃነት እንደሚኖራቸውም አመልክተዋል።

በዘላለም ግዛው – ኢፕድ ዜና

Leave a Reply