አገራችን ኢትዮጵያ በወቅቱ ህልዉናዋን የሚፈትኑ በርካታ ሳንካዎች አጋጥመዋታል። ስጋቱ ደግሞ ከዉጭና ከዉስጥ የተናበበ ሁኖ እናገኘዋለን። በእኔ እምነት ትልቁ ሀገራዊ አደጋ ሁኖ የመጣዉ ዉስጣዊዉ ችግር ነዉ። ከዉስጣዊዉ ችግሮች መካከል ደግሞ የወልቃይት-ጠገዴ ችግር የሚፈታበት መንገድ ዋነኛዉና ግንባር ቀደሙ የኢትዮጵያን ሀገራዊ አንድነት የሚፈትን ጉዳይ ሁኖ ይገኛል።

ወልቃይት-ጠገዴ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አንድነት ያለዉን ወሳኝ ሚና በተደጋጋሚ ገልጫለሁ። ወያኔ ወልቃይት-ጠገዴን መቸ፤እንዴትና ለምን ዓላማ በጁ እንዳስገባዉ እኔና በርካታ የአማራ ሊህቃን አስረግጠን ተናግረናል። በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ከሰሞኑ አቶ አንዳርጋቸዉ ፅጌ በESAT የሰጡት ማብራሪያ እዉነታዉን የበለጠ ግንዛቤ የፈጠረ ይመስለኛል። ወያኔ በሆነ መንገድ ወልቃይት-ጠገዴን መልሶ በጁ ቢያስገባ ያለምንም ጥርጥር ኢትዮጵያ እንደምትፈርስ ደጋግመን ተናግረናል። እንዲህ አቋሜን አጠንክሬ የምገፋዉ ወልቃይት-ጠገዴ በትግራይ ክልል ስለሚጠቃለል ብቻ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ከሚል አመለካከት ብቻ አይደለም። ይልቁንስ ወያኔ ወልቃይት-ጠገዴን በጁ ካስገባ በሁዋላ በኢትዮጵያ ላይ የሚከተለዉ መከራ ከወዲሁ ፍንትዉ ብሎ ስለሚታየን እንጅ። የኤርትራን ጉዳይም አትዘንጉት።

ነገሩ “ብጥለዉ ገለበጠኝ” ሆነና ይህ ወልቃይት-ጠገዴ ለኢትዮጵያ መፍረስ መንስኤ መሆኑ አይቀርም የሚለዉ የኢትዮጵያዊያን አጀንዳ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በወያኔ ቤት አጀንዳዉን ለመንጠቅና ለራስ ጥቅም ለማዋል ሙከራ እየተደረገ ነዉ። ይችን አጀንዳ ነጠቃም፣ የወልቃይት-ጠገዴ በወያኔ እጅ መዉደቅ ማለት ኢትዮጵያ እንድትፈርስ መፍቀድ እንደማለት ነዉ ብለዉ የሚሟገቱትን ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ ለመንጠቅ የተደረገች ሙከራ ናት።

አጀንዳዋን መጀመሪያ ላይ ቀስ አድርጎ ለመንጠቅ የሞከረዉ ጌታቸዉ ረዳ ነበር። ጌች በቅርቡ ወደ ትግራይ አቅንተዉ ለነበሩት የምዕራቡ አለም ዲፕሎማቶች በወልቃይት ላይ የተሳሳተ አቋም ከያዛችሁ ኢትዮጵያ እንድትፈርስ መፍቀድ ማለት እንደሆነ እንዲያዉቁት ነግረናቸዋል ሲል አድምጠነዉ ነበር።

ወያኔ ኢትዮጵያዊያን ወልቃይት በወያኔ እጅ ከገባች ኢትዮጵያ ፈረሰች ማለት ነዉ በሚል የያዙትን አጀንዳ ቀምቶ እና አዛብቶ ለራሱ በሚጠቅም መልኩ እንዴት ሊጠቀምበት ቆርጦ እንደተነሳ ለመገንዘብ በትላንቱ ዕለት፣ ጌታቸዉ ኦሬንት አድርጎ ያሰማራቸዉና በሚዲያቸዉ ቀርበዉ ሁለት ወያናዊ ሙህራን የሰጡትን ትንታኔ ማጤን ብቻ በቂ ይመስለኛል(ተስፋ አደርጋለሁ የአማራ ፖለቲከኞች በተለይም የፖለቲካ ክፍሉ ይሄንን ዉይይት ተከታትሎት ይሆናል፣ የመልስ ምትም አዘጋጅቶ ይሆናል)።

እንደነዚህ ሁለት ወያናዊ ሙህራን ትንታኔ ወልቃይት በኢትዮጵያዊያን እጅ ከገባች( በነሱ አባባል ወደ አማራ ክልል ከተጠቃለለ) ኢትዮጵያ ያኔ ነዉ “መፍረስ የምትጀምረዉ”። እንደነ ሙህሬ ትንታኔ ወልቃይት ጠገዴ በአማራ እጅ ከገባ፣ ኢትዮጵያን የማፍረሱ ሂደት ወደሌሎቹም ክልሎች በሂደት ይስፋፋል ነዉ። ይሄዉም አማራ የወልቃይት-ጠገዴን ጉዳይ ሴኪዩርድ ካደረገ በሁዋላ ወደሌሎችም ክልሎች መዞሩ አይቀርም ነዉ። ይህ መሰሪ አካሄድ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ነገ በኔ ይደርሳል ብለዉ በመስጋት የወልቃይትን ጉዳይ በዉል እንዳይገነዘቡትና ዛሬም ድረስ በአማራ ላይ ያላቸዉን መጠራጠር አጠናክረዉ እንዲቀጥሉ ያለመ መልዕክት ነዉ።

እዚህ ላይ አንድ ግልፅ መሆን ያለበት ነገር አለ። የአማራ ህዝብ እጠቀማለሁ ብሎ የሚያስበዉ ኢትዮጵያ አንድ ሁና ስትቀጥል ብቻ ነዉ። ወያኔ ደግሞ የትግራይ ህዝብ ዘላቂ ጥቅም የሚረጋገጠዉ ኢትዮጵያ ስትፈርስና የትግራይ ነፃ መንግስት ሲመሰረት ነዉ። ስለዚህ ወያኔና የአማራ ህዝብ በኢትዮጵያ አንድነት ዙሪያ ይሄን ያክል ዘላቂ ጥቅምን መሰረት ያደረገ ልዩነት አላቸዉ። በመሆኑም የአማራ ህዝብ ልክ እንደትላንቱ ኢትዮጵያ ፀንታ ትኖር ዘንድ ይታገላል፣ሊያፈርሷት የሚከጅሉትንም ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር ሁኖ ይታገላቸዋል። የአማራ ህዝብ ኢትዮጵያን በተመለከተ የትላንት፣ዛሬና ነገ አቋሙ ይሄዉ ነዉ።

እዉነት ነዉ ከወሰንና ማንነት ጋር እንዲሁም ከፖለቲካዊ ተሳትፎ ጋር በተያያዘ፣ የአማራ ህዝብ በተለይም ባለፉት 27 አመታት በወያኔ የተዛባ አገዛዝ የተዛቡ ጉዳዮች ስላሉ እነዚህ እንዲስተካከሉ ህጋዊና ተገቢነት ያላቸዉ ጥያቄዎች አሉት። ይሁን እንጅ የአማራ ህዝብ ከወልቃይት-ጠገዴ፣ጠለምትና ራያ አንፃር የሚያነሳቸዉ ጥያቄዎች ከሌሎቹ ጥያቄዎች ጋር መምታታት የለባቸዉም። ወልቃይት-ጠገዴ፣ጠለምትና ራያ በወረራ የተያዙ የአማራ ህዝብ መሬቶች ናቸዉ። በአንፃሩ ወያኔ ሊያስፈራራባቸዉ የሚሞክራቸዉ እንደ መተከል፣ደራ የመሳሰሉት ደግሞ ወደ ቤጉና ኦሮምያ የተካለሉት በወረራ ሳይሆን በወቅቱ በነበረ አሰተዳደራዊ አሰራር ነዉ። የቤጉ ክልልም ሆነ የኦሮምያ ክልላዊ መንግስት፤መተከልን ሆነ ደራን ወደክልሎቻቸዉ ያካተቷቸዉ በወረራና በጉልበት ከአማራ ቀምተዉ አይደለም። በወቅቱ የአማራ ክልልን የመግዛት እድል በነበረዉ መንግስት/ አሰተዳደራዊ ዉሳኔ ነዉ። እዉነታዉ ይሄ ነዉ። ስለሆነም የነ መተከል ጉዳይ የነ ወልቃይት-ጠገዴ፣ጠለምትና ራያን ጥያቄወች ለማዛባት ያለ አዉዱ መነሳት የለበትም።

ስለዚህ በወያኔ ወረራ የተወሰዱትን የነ ወልቃይት-ጠገዴና ራያን አጀንዳ በአስተዳደራዊ ጉዳይ ከተፈፀመ ስህተት ጋር አምታትቶ በማቅረብ የኢትዮጵያዊያንን ቀልብ ከወሳኙ አጀንዳ ለማስወጣት የተያዘዉ የወያኔ አጀንዳ ሊሳካ የሚችል አይደለም። በአጠቃላይ የችግሮቹ አፈጣጠር፣ አያያዝና አፈታትም ልዩነት ይኖረዋል ማለት ነዉ። ገራሚዉ ነገር ሙህራኑ አማራ ወልቃይት ላይ ከተሳካለት፣ነገ ጉራ ፈርዳ፣ሱማሌና ሀረር ወዘተ ተሻግሮም የኔ ነዉ ማለቱ አይቀርም በማለት የተነተኑበት መንገድ ነዉ። የተበላች ቁብ!

ደግነቱ ዛሬ ትላንት አይደለም። ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ስለወያኔ መሰሪነት፣አገር አፍራሽነት ከመቸዉም ጊዜ በላይ ግንዛቤ አግኝቷል። ሌላዉ ቀርቶ ዛሬ ላይ የወልቃይት-ጠገዴ፣ጠለምትና ራያ ጉዳይ ሀቁ ፍንትዉ ብሎ ከመታወቁም በላይ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ አጀንዳ ሁኗል። ስለዚህ በዚህ ዙሪያ ወያኔ የጀመረዉ የማደናገርያ አጀንዳ ብዙም እርቀት ሊወስደዉ አይችልም።

ሌላዉ ቀርቶ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ እንኳን ቢያንስ ልቡ እዉነታዉን አዉቆታል። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነዉ በትላንቱ የወያናዊ ሙህራን ትንታኔ ላይ ጋዜጠኛዋ ለሙህራኑ”ለመሆኑ የአለምአቀፉ ማህበረሰብ የወልቃይትን ሁኔታ እንዴት ነዉ የሚገነዘበዉ? የሚል ጥያቄ አቅርባላቸዉ ነበር። የሙህራኑ መልስ ደግሞ “አማራ የተቀማዉን መሬቱን ለማስመለስ እንደሚታገል ነዉ ግንዛቢያቸዉ” የሚል ነበር( በሞቴ ሙሉ ቪዲዮዉን አድምጡት)። ይህ በራሱ የአማራ ህዝብ ትግል በአለምአቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ሳይቀር ግንዛቤ እያገኘ ስለመምጣቱ ወያኔ መረዳቱን ይነግረናል። አይ ኤርትራ መከራሽ። አንችን ካልረገሙ የፖለቲካ ትንታኔ የሚችሉ አይመስላቸዉም እኮ።

በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ኢትዮጵያ አንድ እዉነታ አይኑን አፍጥጦ መጥቷል። ይሄዉም በአንድ በኩል የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ በሌላ በኩል ደግሞ ወያኔ ወልቃይት-ጠገዴ ለኢትዮጵያ መፍረስና መፅናት ዋነኛ ምክንያት እንደምትሆን ስምምነት ላይ ደርሰዋል። የሁለቱ ወገኖች ልዩነት ኢትዮጵያ የምትፈርሰዉ ወልቃይት በማን እጅ ከገባች ነዉ? የሚለዉ ነዉ። የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ወልቃይት በወያኔ እጅ ከገባች ነዉ ብለዉ አምነዋል። ወያኔ ደግሞ ወልቃይት በኢትዮጵያ መንግስት ወይም በኢትዮጵያዊነት ስሜት ተጠቂ በሆነዉ በአማራ ክልል ከተጠቃለለ ነዉ ብሎ ያምናል። እንግዲህ ልዩነቱ ይሄንን ያክል ነዉ።

ለማጠቃለል ያክል የወልቃይት ጉዳይ በማያወላዳ መልኩ ለኢትዮጵያ መፅናትም ሆነ መፍረስ ወሳኝ ስለመሆኑ በሁሉም ወገኖች ዘንዳ የጋራ አቋም ተይዞበታል። አሁን ቁልፍ ጥያቄ ሁኖ ፊት ለፊታችን ድቅን ያለዉ ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ ወልቃይት በማን እጅ ሁና ትቀጥል ነዉ። ወቅታዊዉ እና አንገብጋቢዉ ጥያቄ ኢትዮጵያን ያላችሁ እስኪ እንያችሁ! የሚል ሁኗል።

ለሁሉም ወልቃይትን መነሻ አድርጎ ስለ ኢትዮጵያ መፅናትና መፍረስ በተጀመረዉ አጀንዳ ዙሪያ ወያኔ አጀንዳዉን ነጥቆ ለራሱ በሚጠቅም መንገድ ለማራገብ ሙከራ ከመጀመሩም በላይ የተካነበትን አደገኛና የተዛባ ትርክት ጀምሯልና ጠንከር ያለ ፖለቲካዊ ስራ ያስፈልገዋል። በተለይ ከአማራ ፖለቲከኞች አንፃር። በተለይም ወልቃይት በወያኔ እጅ ካልሆነ ነገ እያንዳንድሽ ይደርስሻል በሚል ሌሎች ክልሎች ከእዉነት ጎን እንዳይቆሙና ወያኔ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የያዘዉን አጀንዳ በተዘዋዋሪ መንገድ እንዲደግፉት ያለመ ሰራ እየተሰራ እና ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አዉቆ ይሄንን ሴራ ለአገራችን ህዝብም ሆነ ለአለምአቀፉ ማህበረሰብ በደንብ ማጋለጥና እዉነታዉን ማሳየት ያስፈልጋል።

የአማራ ህዝብ ጥያቄ ህጋዊና በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ የሚታይ መሆኑን፣ የወልቃይት-ጠገዴ፣ጠለምትና ራያ ጥያቄ፤ ወያኔ እንደማስፈራሪያ ከሚያነሳቸዉ በተለይም ከነ መተከል እና ሌሎችም አካባቢወች ጋር፣በችግሩ አፈጣጠርና በባህሪዉ እንዲሁም ና በችግሩ አፈታት ዙሪያ ልዩነት እንዳለዉ በሚገባ ማሰረዳት በዋነኛነት የአማራ ፖለቲከኞች ስራ ነዉ። አጀንዳዉ ብልፅግና/አብን መሆንን አይጠይቅም።

Chucu Alebachew

Leave a Reply