በኢትዮጵያ ሰማይ ስር የተመዘገበ ሌላኛው አንፀባራቂ የድል

“የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይ ኃይል ማመንጨት በኢትዮጵያ ሰማይ ስር የተመዘገበ ሌላኛው አንፀባራቂ የድል ብስራት ነው።”
አቶ ግዛቸው ሙሉነህ የአብክመ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ

ታላቁ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የሕዳሴ ግድብ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የግንባታው መጀመር ብስራት የሆነው የመሠረት ድንጋይ ጉባ ላይ ከተቀመጠበት ጊዜ አንስቶ በሀገራዊ ወኔ በመነሳሳት በመንግሥት ቁርጠኝነት፣ ሕዝባዊ ድጋፍና ተሳትፎ ግድቡን ዳር ለማድረስ ፈተናዎችን ሁሉ ተቋቁመን የስኬት ማማ መዳረሻ ላይ እንገኛለን፡፡

በመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ ክንድ የግንባታው የውሃ ሙሌት በ3 ዙር ተከፋፍሎ ላለፋት ሦስት ዓመታት በስኬት በመጓዝ በአሁኑ ወቅት የሁለተኛው ተርባይን 270 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት ችሏል።

ይህ ታላቅ ፕሮጀክት ለኢትዮጵያ ያለው ፋይዳ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ በአገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ዕድገትና ብልፅግና ከፍተኛ ሚና መጫወት እንዲችሉ ዕድል የፈጠረ ነው።

መላው የሀገራችን ብሎም የክልላችን ሕዝብ የፋይናንስ፣ የፐብሊክ ዲፕሎማሲና የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ላይ በሚያደርገው ያልተቋረጠ አስተዋፅኦ የግንባታ ሥራውን ለማጠናቀቅ ሌት ተቀን ከፍተኛ ርብርብ በመደረጉ ሁለቱ ተርባይኖች በድምሩ 540 ሜጋዋት ኃይል በማመንጨት የሃገራችንን የኃይል አቅርቦት ደረጃ ማሻሻል ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያንን በፈተናዎች ሁሉ አይበገሬነት እውን ማድረግ አስችሎናል፡፡

የሕዳሴው ግድብ የሃገራችን ብሔሮችና ብሔረሰቦች ባለፉት ዓመታት ለፕሮጀክቱ ስኬት ተሳትፏቸውን በተለያዬ መልክ የገለፁበት እና ግንባታው ለአፍታ እንዳይገታ የባለቤትነት ስሜታቸውን በቁጭት ያንፀባረቁበት ታሪካዊ አሻራችን ነው፡፡

የሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት መጠናቀቅ በራሳችን አቅምና ገንዘብ፤ ፈተናዎቻችንን ድል በማድረግ የግድቡ ግንባታ ከእለት እለት በስኬት እውን ሁኖ ለሚፈለገው ዓላማ መጠቀም እንደምንችል በተግባር ያሳየ ነው።

መላው የክልላችን ሕዝብ፦ የሕዳሴው ግድብ የዓድዋን ድል የደገምንበት፣ የዲፕሎማሲ የበላይነትን ያረጋገጥንበት፣ የኢትዮጵያውያን ቁርጠኝነትና ጀግንነት ማረጋገጫ ሀቃችን በመሆኑ ግድቡ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ወደ ሙሉ ትግበራ እስኪደርስ ድረስ መላው ህዝባችን ለአፍታም ሳይዘናጋ የሚያደርገውን ድጋፍ ይበልጥ በማጠናከር የሀገራችንን የብልጽግና ጉዞ ለማረጋገጥ ከመንግሥት ጎን መሰለፍ ይጠበቅበታል።

See also  የመረጃና ደህንነት አገለግሎት አርማ ያለባቸው የዋሌት ምርቶች ለማጭበረበሪያነት እየዋሉ ነው፤ ማስጠንቀቂያ ተሰጠ

የግድቡ ግንባታ ለአሁኑ ትውልድ ትልቅ ጀግንነት ሲሆን ለቀጣዩ ትውልድ ደግሞ የጽናትና የአልበገርም ባይነትን ወኔ የምናወርስበት ታሪካዊ ክስተት ነው፡፡

ስለሆነም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን የኃይል ማመንጨትም የነገን ተስፋ ያለመለመ ብቻ ሳይሆን ለተጨማሪ ድሎች የሚያነሳሳ ተግባር ነው፡፡

ዛሬም ሆነ ነገ የኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ በውሸት የሚናፈሱ አጀንዳዎችንና የእናት ጡት ነካሾችን እኩይ ፍላጎት ያከሸፈ ሁኖ ይቀጥላል።

የአማራ ክልል ሕዝብ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ክብርና ጥቅም ላይ የማይደራደር ሕዝብ ነው። ለግድቡ እዚህ ደረጃ መድረስ የድርሻውን መወጣቱን ዛሬም ሆነ ነገ በጽናት የሚቀጥል መሆኑን እየገለጽን በቀጣይም በተቀናጀ የተፋሰስ ሥራና ችግኝ ተከላ የግድቡን ጤንነት የመጠበቅ፤ የግንባታ ሥራዎችን የማከናወን፤ የተፈጥሮ ፀጋችንን ፍትሐዊ በሆነ አግባብ የመጠቀም መብታችን ተጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡

መላው የክልላችን ሕዝብ ከመላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በመሆን ግድባችንን ዳር ለማድረስ በቦንድ ግዥም ሆነ በሌሎች ተግባራት በመረባረብ ታሪካዊ አሻራቹህን ማሳረፍ በመቻላችሁ እንኳን ደስ አላችሁ፡፡

የክልላችን ሕዝብ ግድቡን ለማጠናቀቅና ለሚፈለገው ዓላማ ለማድረስ ያሳየውን ተነሳሽነትና ተሳትፎ ከምንጊዜውም በላይ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን እንገልጻለን።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
ነሐሴ 2014 ዓ.ም.
ባሕር ዳር

Leave a Reply