ባልደራስ የእስክንድር ነጋን ተተኪ ሊመርጥ ነው- « ከእኛ ጋር ግንኙነቱን ያቆመው ሐምሌ 16 ነው»

በሃሚድ አወል

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በመጪው ነሐሴ 22፤ 2014 በሚያካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ፤ የፓርቲውን ፕሬዝዳንት እስክንድር ነጋን ለመተካት ምርጫ እንደሚያደርግ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ገለጹ። አቶ እስክንድር ነጋ ዛሬ በባልደራስ ይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ያስተላለፉትን መልዕክት እና የፓርቲውን የወደፊት አካሄድ በተመለከተ፤ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ነገ ውይይት እንደሚያደርግም ምንጮቹ ጨምረው አስታውቀዋል። 

ባልደራስ ጠቅላላ ጉባኤውን ለማካሄድ የወሰነው፤ የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ በየሁለት ዓመቱ ጠቅላላ ጉባኤ መደረግ እንዳለበት በመደንገጉ ነው። ከሁለት ሳምንት በኋላ በሚደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባልደራስን ወደ ሀገር አቀፍ ፓርቲነት የሚያሳድገው የውሳኔ ሀሳብ ለጉባኤው ተሳታፊዎች እንደሚቀርብ የፓርቲው ምንጮች አመልክተዋል።

በመጋቢት 2012 የተመሰረተው ባልደራስ፤ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምዝገባ ፍቃድ ያገኘው በአዲስ አበባ ከተማ ፓርቲነት ነው። የባልደራስ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት፤ ፓርቲው በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመንቀሳቀስ እና በምርጫ ለመወዳደር የሚያስችለውን የምዝገባ ፍቃድ ለማግኘት የአባላት ፊርማ ካለፈው ሚያዚያ ወር ጀምሮ ሲያሰባስብ ቆይቷል። 

ባልደራስን ወደ ሀገር አቀፍ ፓርቲነት የማሳደጉን እንቅስቃሴ ከፊት ሆነው ሲመሩ የቆዩት ፕሬዝዳንቱ አቶ እስክንድር ነጋ ነበሩ። አቶ እስክንድር ለቤተሰብ ጥየቃ እና ለስራ ጉብኝት በሄዱበት አሜሪካ አስቀድሞ ከታቀደው ጊዜ በላይ መቆየታቸው እንዲሁም የፊርማ ማሰባሰቡን ሲያስተባብሩ የነበሩት የባልደራስ የድርጅት ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ቸኮል እና የሌሎች የፓርቲው አባላት እስር እንቅስቃሴውን አዳክሞቷል።

አቶ እስክንድር ነጋ በአሜሪካ የነበራቸውን የሁለት ወራት ቆይታ አጠናቅቀው ባለፈው ሐምሌ ወር መጀመሪያ ወደ አዲስ አበባ ቢመለሱም፤ ወደ ሀገር አቀፍ ፓርቲ ለመሸጋገር በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ እምብዛም ለውጦች አልታዩም። ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የፓርቲው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት፤ እስክንድር ከፓርቲው ጋር ግንኙነታቸውን ያቆሙት ከሁለት ሳምንት በፊት ነው።     

“እስክንድር ከሐምሌ 16 ጀምሮ ቢሮ አይገባም ነበር። ስልክም አያነሳም። ግንኙነት ያለውም ከሰሜን አሜሪካ ድጋፍ ሰጪ ኮሚቴ ጋር ነው እንጂ ከእኛ ጋር ግንኙነቱን ያቆመው ሐምሌ 16 ነው። ስለደህነነቱ የምናውቀውም ከሰሜን አሜሪካ በምናገኘው መረጃ ነው” ሲሉ የባልደራስ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባሉ ስለ ፓርቲው ፕሬዝዳንት የሚያውቁትን ተናግረዋል።

See also  በሀገር ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉና የቴሌኮም ማጭበርበሪያ መሳሪያዎች ተያዙ

ዛሬ ሐሙስ በፓርቲው የማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ የተላለፈው መልዕክትም፤ ሰሜን አሜሪካ በሚገኘው የባልደራስ ድጋፍ ሰጪ ኮሚቴ በኩል እንጂ፤ አዲስ አበባ ከሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤት የወጣ እንዳልሆነም ጠቁመዋል። የተቀባይ አድራሻውን ለባልደራስ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያደረገው ይህ ባለ አንድ ገጽ ደብዳቤ የተጻፈበት ቀን ሐምሌ 16፤ 2014 እንደሆነ በፓርቲው የማህበራዊ ትስስር ገጽ ከመልዕክቱ ጋር አብሮ የተያያዘው ፎቶ ያሳያል።   

በእጅ ጹሁፍ በቀረበው በዚህ ደብዳቤ ላይ አቶ እስክንድር፤ “ተረኛው ጨቋኝ መንግስት በባልደራስም ሆነ በሃገር አቀፍ ደረጃ በፈጠረው የለየለት አምባገነናዊ ጫና ሳቢያ፣ በአባልነትም ሆነ በአመራርነት መስራት የማልችልበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁ” በማለት አስፍረዋል። አቶ እስክንድር በደብዳቤያቸው ላይ “ጫና አለብኝ” ማለታቸውን “እንቀበለዋለን” የሚሉት የፓርቲው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል፤ “እስክንድር ጥሎ መሔዱን ግን አንቀበለውም። እዚሁ ሆኖ መታገል ምርጫው ቢሆን እንወድ ነበር” ሲሉ የፓርቲውን ፕሬዝዳንት ውሳኔ ተችተዋል። 

በባልደራስ ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተሰራጨው መልዕክት “የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ያስተላለፈው አይደለም” ያሉት እኚሁ አመራር፤ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ “ዛሬ በወጣው መግለጫ ላይ፤ በእስክንድር ጉዳይ ላይ እና አካሄዳችን እንዴት ነው የሚሆነው በሚለው ላይ ውይይይት ያደርጋል” ብለዋል። የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አምሃ ዳኘው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ነገ በጉዳዩ ላይ እንደሚወያይ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። 

ዛሬ ይፋ የተደረገው የአቶ እስክንድር ነጋ ደብዳቤ ላይ “የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ በየደረጃው ያሉ የፓርቲው አመራሮች፣ መላ አባላትና ደጋፊዎች፣ እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች” የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አምሃ ዳኘውን ሙሉ ለሙሉ እንዲተባበሯቸው ጥያቄ አቅርበዋል። የፓርቲው ፕሬዝዳንት በዚሁ ደብዳቤያቸው ለምክትላቸው “ስራቸው የተቃና እንዲሆን” ተመኝተውላቸዋል። 

የባልደራስን ቀጣይ ውሳኔ ተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል “አንድ የምንወደው እና የምናከብረው [የፓርቲው] መስራች የሆነ ሰው ለቅቋል። እኛ ግን የፖለቲካ ትግሉን እንቀጥልበታለን። እስክንድር አሁን ባለበት ጫና ከፖለቲካ ፓርቲው ራሱን ቢያገልልም፤ እንደ ፓርቲ እንቀጥላለን። እስክንድር ያነሳቸውን cause ይዘን ነው እኛ የተነሳነው” ብለዋል። 

See also  በትግራይ ለ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች እርዳታ ቀረበ- 9 ሚሊየን የኮቪድ19 ክትባት ሊገባ ነው

ፕሬዝዳንት የመምረጥ ስልጣን የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ መሆኑን የገለጹት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባሉ፤ እስከ ጠቅላላ ጉባኤው ድረስ ፓርቲው በምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ አምሃ ዳኘው እንደሚመራ ገልጸዋል። ከሁለት ሳምንት በኋላ በሚካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ከፕሬዝዳንት ምርጫ በተጨማሪ “አላሰራ ያሉ” የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ድንጋጌዎች ላይ ማሻሻያ እንደሚደረግባቸውም እኚሁ የፓርቲው አመራር ጠቁመዋል። 

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የመሪውን ምርጫ ጨምሮ ሌሎችም ጉልህ ለውጦች የሚያደርግበትን ጠቅላላ ጉባኤ በተመለከት ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እስካሁን ምንም አይነት ደብዳቤ አለማስገባቱን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከቦርዱ አረጋግጣለች። የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ፤ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ የሚያካሄድ ከሆነ የቦርዱ ተወካይ በስብሰባው ላይ እንዲገኝ ከ30 ቀናት በፊት አስቀድሞ ማሳወቅ እንዳለበት ደነግጋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር

Leave a Reply